“ለማንኛው ላልቅስ”?
የሃሳብ ፍልስፍና ዝብርቅርቁ ሲወጣ፣
የፍጡራን ጸጋ ሕይወት ክብር ዋጋ ሲያጣ፣
መከራ ሲበዛ ጽዋው ሞልቶ ሲፈስ፣
ለካስ ያደንዛል! ትርጉም ታጣለች ነፍስ።
እንባም ለካ ይገዳል፤ የተሰበረ ልብ ጠጋኝ ፈሳሸ ያጥራል፣
አምላክም አይቶ እንዳላየ ዝም ሲል — ለማንስ “ኤሎሄ” ይባላል?
የቀቢጸ-ተስፋ ሕይወት — ኢትዮጵያዊ ስንት ዘመንስ ይኖራል?
ለማን ላልቅስ...?
በሞቃድሾ ጎዳና... አስክሬኑ ለተጎተተው...?
በምድረ-ግብጽ - ሲናይ .. እንደ ቅርጫ ለተመተረው?
በሳዑዲ አረቢያ በረሃ .. አናቱ ለተፈለጠው..?
በደቡባዊት አፍሪቃ - በነበልባል እሳት ለተቃጠለው?
በሜድትራንያን ባሕር ላሳነባሪ ለተጣለው...?
በአረመኔዎች በሊቢያ ለማተቡ ለተሰየፈው?
ባረብ ሃገራት ግርድና በስቃይ ሕይወት ለመረራት...?
ልጇ ባለቀሰባት ያረብ እመቤት.. የፈላ ውሃ ለተደፋባት...?
በጋጠ-ወጦች ተደፍራ .. ህሊናዋን ለሳተች...?
በግፍ ተቀጥቀጣ ..ከፎቅ ለተወረወረች...?
ለነጻነት ያልታደለ - ሳይነጋ የመሸበት፣
የሰቆቃ ኑሮ ሕይወት - ዕጣ-ፈንታው የሆነበት፣
በቤቱም በውጭም - የስቃይ ሞት ያልቀረለት፣
የመከራ ዘመን ትውልድ - ኢትዮጵያዊ የፈረደበት።
ለማን ላልቅስ..?
...ከአሰፋ ማሩ.. እስከ ህጻን ነብዩ.. በወያኔ ገዳዮች ለተረሸኑት..?
...ባራቱም ማዕዘናት ሰማቸው ሳይነሳ ላለፉት...?
በጋምቤላ ደን ውስጥ እንደ አውሬ ታድነው ለተገደሉት...?
በኦጋዴን በረሃ ከነቤታቸው ለተቃጠሉት...?
አስከሬን እንኳ ክብር አጥቶ እንደ እንጨት ለተከመሩት...?
...አርሲ፣ ሐረር፣ አሶሳ...ወደ ገደል ለተጣሉት...?
...ጉራፈርዳ..ቤኒሻንጉል.. የጣር ዋይታ ላሰሙት...?
ከኢሉባቦር እስከ አፋር... ከመቀሌ.. እስከ ባሌ.. የግፍ ጽዋ ለቀመሱት?
ለኢትዮጵያ ውድ እናቶች -የደም እንባ ለሚያለቅሱ?
የሕይወት ዘመናቸውን - የሃዘን ማቅ ለሚለብሱ?
ባገሪቱ..እስር ቤቶች.. በሰቆቃ ስቃይ ላሉት...?
ለህጻናት ልጆቻቸው.. እናት/አባት-አልባ ለሚያድጉት..?
ለማን ላልቅስ...?!
...
የመለኮት ጸጋ ምስጢር - ይፈጸም ዘንድ ህያው ቃሉ፣
ለዘላለም ዓለም እረፍት - እነሱስ ተገላገሉ፤
ይብላን ለኛ ለቀረነው - ለሚበላን ሰቀቀኑ፣
ለምስቅልቅል ሕይወት ኗሪ - ላጎበጠን ሃዘኑ!
ጌታቸው አበራ
ሚያዝያ ፪ ሺ ፯ ዓ/ም
(ኤፕሪል 2015)
No comments:
Post a Comment