Saturday, May 2, 2015

የተሰጠ መግለጫ ቀን ፡ ሚያዝያ 20, 2007ዓ.ም ዘመኑ ለኢትዮጵያውያን የፈተና ዘመን ነው ሰደት ፣ሰቆቃ እንዲያበቃ የወያኔ አገዛዝ ያብቃ!! ብዙውን ጊዜ በዓለማችን በተፈጥሮ አደጋና በተላላፊ በሽታ ከሚያልቀው ሕዝብ ይልቅ በጥቅም ተናንቆ የሚያልቀው ቁጥር ሚዛኑ ይደፋል። ያለፉት ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ያሳዩት ይኽኑ ዕውነታ ነው። አንዱ ጥጋበኛና አምባገነን መንግሥት (አገር) ሌላኛውን አገር በጦርነት ወሮ የተጠቂውን አገር የተፈጥሮ ሐብት መዝረፍ፣የሕዝቡን ነፃነት መግፈፍና ለባርነት መዳረግ ያለንበት ዘመን ተጨባጭ ሁኔታ ባይፈቅድም ስልቱና መልኩ ተቀይሮ አሁንም ስቃይ መከራ እንዲቀበሉ የተፈረደባቸው ሕዝቦች አሉ። አገራችን ኢትዮጵያም የዚህ ግፍና በደል ሰለባ ሆናለች። የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን የሚያራምዱ ኃያላንና ከበርቴ አገሮች የአድዋ ድል የእግር እሳት ሆኖባቸው ለአገራችን የመልከአ ምድር ካርታ በማዘጋጀት ደካማና ጥገኛ ትናንሽ መንግሥታት በመፍጠር የቆየ ዓላማና ግባቸውን ለማሳካት እየሠሩ እንደሆነ ይታያል። በአገራችን የተፈጠሩ የብሔር ድርጅቶች የግንጠላ ርዕዮት እያራመዱ የሚንቀሳቀሱት ከነዚሁ የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች በሚያገኙት የፋይናንስ ፣ የጦር መሳሪያ፣ የሞራልና ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሆነ ያየነውና እየተፈጸመ ያለ ሐቅ ነው።በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በመንግሥት ስም የተቀመጠው የወያኔ ቡድን በሕዝብ ውክልና ሳይሆን በባዕዳን ቅጥረኝነት ስለሆነ የሕዝብና የአገር ሉዓላዊነት ተደፍሯል፣ዳር ድንበር ተጥሷል፣ለም መሬቶቻችን እየተሸነሸኑ አገሬው እየተነቀለ ለባዕድ አገር ከበርቴዎች ተቸብችበዋል፣ ዜጎች የእኔ ነው የሚሉት ስንዝር መሬት ወይም ተንቀሳቃሽ ንብረት ፣ ለመተዳደሪያ የሚሆን የስራ ዕድል ሰለ አጡ አገር ጥለው በመውጣት እግር እንዳረሰ ስደትን መረጡ። በአገር ውስጥም ወገኖቻችን ተስፋቸው ጨልሞ ለበሽታና ረሃብ ተጋልጠዋል፤ በሰላም ውሎ ማደር ዋስትና የላቸውም፤ ለዚህም ነው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሰደት ምርጫ የሆነው።በዚህ ላይ መሸጥ የለመደ እናቱን ያስማማል እንዲሉ ወያኔ አሰሪና ሠራተኛን አገናኝ የሚል የዘመናዊ ባሪያ ፍንገላ ተቋም ( ኤጄንሲ) አደራጅቶ ዜጎችን እንደቁም ከብት ይቸበችባል። በመድረሻ አገራቸው የሚደርስባቸውን ችግር ዞር ብሎ የሚያይ ዓይን ግን የለውም። የዓለም ደቻሳንና በሳኡዲ አገር በዜጎቻችን ላይ የደረሰውን ግድያ ያስታውሷል። በሕጋዊም ሆነ በሕገወጥ መንገድ ከአረብ አገሮች በቁጥር የበዙ ኢትዮጵያውያን ይኖሩበት የነበረው አገር ሳኡዲ አረቢያ ነው። ባለፈው ዓመት ከአገሬ ውጡልኝ በሚል ሰበብ በወገኖቻችን ላይ የሳኡዲ መንግሥት የፈጸመው ኢስብአዊ እርምጃ ዘግናኝ ፣አስጸያፊና አሳዛኝ ከመሆን አልፎ በቁጪት እንድናወግዘው አስገድዶናል።ወያኔ ግን ኢትዮጵያውያንን በፔትሮ ዶላር ለውጦ የሳኡዲ መንግሥት መብቱ ነው ይበላቸው ዓይነት አንድምታ ያለው መግለጫ ሰጠ። በዚህ ሳያበቃም ሁኔታው ያስቆጫቸው ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ የሳኡዲ አረቢያ ኤምባሲ ሄደው ተቃውሞአቸውን ለመግለጽ ሲሞክሩ በፌዴራል ፖሊስ አስቀጥቅጦ በተናቸው። ከቆዳቸው ቀለም ፣ አማርኛ ቋንቋ ከመነገርና ከስማቸው ተመሳሳይነት በቀር ድርጊታቸዉ ሁሉ ኢትዮጵያዊ የማይመስሉ ጉዶች። ሁለተኛው የኢትዮጵያ ሰደተኞች መናኸሪያ የመን ነች። ወደ የመን የሚሰደዱት ኢትዮጵያውያን አገሪቱን እንደመሸጋገሪያ ተጠቅመው ወደ ሌሎች አገሮች ለመድረስ እንደሆነ ይነገራል። ለመኖርም ፣ ወደ ሌላ አገርም ለመሻገር የመን የምትመች እንዳልሆነ ከመገናኛ ብዚኃን እየተነገረ የምናውቀው ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ በአሁኑ ወቅት በየመን የሚታየው አስከፊ የርስ በርስ ጦርነት ወትሮውንም ላልደላቸው ኢትዮጵያውያን ቀርቶ ለየመኖችም አስከፊ ሆኗል፤ ለኢትዮጵያውያን ግን የባሰ ገሃነም ነው። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን የድረሱልን ጩኸት እያሰሙ ነው። ወያኔ ለዚህ የወገን ጩኸት በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኩል በፌስ ቡክ የማስመሰል መልዕክት ለጥፎ የለበጣ አባባል አስነብቧል። ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየውም የሳኡዲን የአየር ድብድባና ጣልቃገብነት አወድስዋል። ወያኔ በማያገባው ገብቶ በሶማሊያ እንዳደረገው ሁሉ። ሁኔታው ለዜጎቻችን የበለጠ የጥቃት ሁኔታን እየፈጠረ ነው። 1 2 2 ሱዳንን ጨምሮ ሌሎች አገሮች ዜጎቻቸውን በባህር ፣ በየብስና በአየር ሲያጓጉዙ የኛ ዜጎች ለአደጋ ተጋልጠው ይገኛሉ። ዘመኑ ለኢትዮጵያውያን የፈተና ዘመን ነው የምንለው ከላይ የጠቀስናቸው ችግሮች እንዳሉ ሆነው ሌሎች ችግሮች ስለተጋረጡብን ነው።በገር ውስጥ በክብርና በኩራት የመኖር ጸጋችን ተገፎ ተሰደን በዓለም ሁሉ ተበትነናል። ከጎሮቤት አገሮች ርቀን ደቡብ አፍሪካንም መድረሻ ካደረግን ቆየ። በዚች በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን ሰደተኞች መኖርና መሥራት ንብረት ማፍራት ችለዋል። ባልተጠበቀና በማይታሰብ አረመኔያዊ አፈጻጸም የደርባን ነዋሪዎች በኢትዮጵያውያንና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ስደተኞች ላይ የሕይወት ማጥፋት፣ ማቃጠልና የንብረት ዘረፋ ወንጀል እርምጃዎችን ወሰዱ። ጋዝ በማርከፍከፍ በወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው የግፍ ግድያ የ21ኛውን ዘመን ማህበረሰብ የማይመጥን ኋላ ቀር( Barbaric Act) ድርጊት ነው። በአፓርታይድ ዘመን ለ27 ዓመታት በእስር ቆይተው በመጨራሻ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ለነበሩት ለኔልሰን ማንዴላ መጠለያና የውትድርና ሥልጠና ለሰጠች አገር ዜጎች ለኢትዮጵያውያን ምላሹ ይኼ መሆን አልነበረበትም።ኔልሰን ማንዴላ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ በመቃብራቸው ዕለት ከ20 በላይ የዓለም አገሮች መንግሥታት መሪዎች አሜሪካንን ጨምሮ ተገኝተዋል።አሜሪካ በአፓርታይዱ ጊዜ ኔልሰን ማንዴላንና ድርጅታቸውን ኤ ኤን ሲ(ANC) በአሸባሪነት የፈረጀች ነበረች። እንኳንስ የዘር መድሎ ሲታገሉ ለቆዩት ልታግዝ ይቅርና። ዛሬም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት የሆነው ወያኔ ተላላኪያቸው ስለሆነ የአሜሪካ ወዳጅ ነው። ለጥቅማቸው እንጂ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ግድ የላቸውም። ይህን ልንግናዘብ ይገባናል። የዘመኑ ፈተና፣ ስቃይ ፣ መከራው ተከትሎናል፤ አገር ቤትም ከአገር ውጪም። በሰሞኑ ኢትዮጵያውያንን በያሉበት ያሳቀቀ ፣ አንገት ያስደፋ፣ሕሊናን ያቆሰለ፣ አንጀት ያሳረረ ሐዘን አጋጠመን።ያልፍናል ብለው ስደትን የተጋፈጡ ወገኖቻችን በሊቢያ ምድር በሁለት የተለያዩ ቦታዎች የአይ ኤስ አይ ኤስ(ISIS) አንዱ ክንፍ በሆነው ዳየሽ(አይ ኤስ)(Daesh(IS)) በተባለ አሸባሪ ቡድን እጆቻቸው የፊጥኝ ታስረው አንጋታቸው እንደ ከብት ታረደ፤ ሌሎቹም በጥይት እሩምታ ተደበደቡ ። ድርጅቱ ቆሜለታለሁ ለሚለው ሃይማኖት መመሪያ እንደማይሠራ በተግባሩ አረጋግጧል።ተግባሩም በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው መወገዝ ያለበት አረመኔያዊ እርምጃ ነው። የእስልምና ሃይማኖት አመጣጥ የሚያውቁ ቢሆኑ ብዙ ጊዜ እንደተነገረውና በቅዱስ ቁርአንም እንደተጠቀሰው የእስልምና አማኞች ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው ሲገቡ በኦርቶዶክስ ክርስትና አማኞች እንደተስተናገዱና በአገሪቱ እምነታቸውን ማስፋፋት እንደቻሉ ነው። ለዚህ በጎ ምግባር ኢትዮጵያውያን ከበሬታና መስተንግዶ እንጂ በአረብ አገሮች ግድያ ፣መሰየፍ፣ በፈላ ውሃ መንፈር ፣እስራት ፣ ግርፋት፣ድብደባ-----ለባለውለታ የሚከፈል ወሮታ አልነበረም፤ የሚጠበቅም አይደለም። በመግቢያው ላይ ለማሳየት እንደተሞከረው ሰዎች በግል ሆነ በቡድን ሆነው ከትውልድ ቀያቸው ከአገራቸው ወደ ሌላ አገር ለመሰደድ የሚገደዱት በአገራቸው ሰላም ሲያጡ ፣ መብቶቻቸው ( የመደራጀትና የእምነት----) በግፍ አገዛዝ ሲረገጡ፣ ከአገሪቱ ሀብት እንደ ዜጋ ባለድርሻ ሳይሆኑ ሲቀሩ፣ ፍትሕ ሲጓደል፣ -----ነው። በነዚህ የወያኔ 24 ዓመታት እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች በወያኔ ሕገ መንግሥት ተብዬ በወረቀት ላይ ከመስፈራቸው በቀር ተግባራዊነቱ አልቦ ነው።የፖለቲካውም ቅኝት የደቡብ አፍሪካውን አፓርታይድ በሚመስል መልኩ የተዘጋጀና ብዙሃኑ ለጥቂቶች እንዲያገለግሉ ፣ የጥቂቶች በሀብት መናጠጥ የብዙሃኑን ርሃብና እርዛት ፣ የኑሮ ውድነት ጣራ መንካት ፣ በቂ የጤና አጠባበቅ ማጣት፣---- እንዲሰፍኑ በትጋት እየተሠራ ነው። ይህን ለመሸፋፈን ማስመሰልና ሞራል የጎደለው የውሸት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ የወያኔ ሚዲያ ተቋማት ጧትና ማታ ሕዝቡን ከማሰልቸት አልፈው የውጪውን ዓለም ለማጭበርበርም በሙሉ ኃይላቸው እየተንቀሳቀሱ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ግን ወያኔ እርቃኑን ቀርቷል።የዝሆን ጆሮ ይሰጠን ብለው የቆዩ ድርጅቶችና መንግሥታት ገመናውን ሊሸፍኑለት ባለመቻላቸው ፊታቸውን ማዞር ጀምረዋል። የአውሮፓ ሕብረት፣ ብሪታኒያ፣ ---አንዳንድ እርምጃ ወስደዋል።ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የሚያካሄዱት ትግልም ፍሬ እያሳየ ነው።በቅርቡ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊ ዊንዲይ ሼርማን ስለወያኔ ምርጫ ዴሞክራሲያዊነት ያለአዋቂ ማሞካሽት ሳቢያ ከድርጅቶችና ከግለሰቦች ኢትዮጵያውያን የደረሰባቸው ውርጅብኝ የትግሉ ደረጃ ከፍ ማለቱንና የኢትዮጵያውያንን ዕጣፋንታ ለመወሰን የሚዳዳቸውን ኃይሎች አደብ የሚያስገዛ እንደሚሆን አንጠራጠርም ። ኢትዮጵያ ከወያኔ ዘረኛ ሥርዓት ነፃ የምትወጣው በ በሕዝቡ ትግል ብቻና ብቻ ነው። ሌላ አቋራጭ መንገድ የለም። በሰደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴም የሙያ ድርጅቶችን በነፃ የመደራጀት መብትን ነፍጎ ማህበሩን አፍርሶ ለተለጣፊ በማስረከብ ኢመማንና መምህራንን እያሰቃየ የሚገኘውን የወያኔ መንግሥት ዊንድይ ሼርማን ዲሞክራት ነው ማለታቸውን በጥብቅ ይቃወማል። የወያኔን ገመና የሚያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ይህን ዘረኛ ሥርዓት ለጥቅማቸው ሲሉ ደግፈው ያቆሙ የውጪ መንግሥታትን ምስክርነትን አንሻም። በአንድነት ቆመን ከታገልን ከወያኔና ከነፍሰ አባቶቹ ነፃ እንወጣለን። የወያኔ መንግሥት በሊቢያ የተሰዉ ወገኖቻችንን ሁኔታ ለፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ የሚያደርገውን እንቅስቃሴንም ህዝቡ ተረድቶ እንዲቃወም ማሳሰብ እንወዳለን። 28 ኢትዮጵያውያን የተገደሉ መሆናቸው እየታወቀ ሁኔታውን አጣርቶ 3 3 ለሁሉም የሚያስፈልገውን እርዳታ ማድረግ ሲገባው ለተወሰኑት ብቻ እርዳታ እንደሚያደርግ ወያኔና ተከታዮቹ በቁጥጥሩ ስር በሚገኛው በብዙሃን መገናኛ እካሌ ይህን ያሕል ብር ሰጠ ፣ እካሌ ለቅሶ ደረሰ-- እያለ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየተጠቀመበት ነው። ይህንንም ድርጊት እናወግዛለን። ይህን ሁሉ ቀልድ የሚፈጽመው ለቅሶ ላይ ሳሉ ወገኖቻችን ላይ ድንኳን እያፈረሰ ባለበት ሁኔታ ነው። የዚህ ሁሉ ስቃይ መከራ ስደትና ሞት መንስኤው ወያኔ/ኢህአዴግ ነው።ስደት ሰቆቃው እንዲያበቃ ወያኔ አገዛዝ ያብቃ።ቆርጠን እንታገል።ከመሰደድ አሳዳጆችን ማስወገድ። በመጨረሻም በሰደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ መምህራን፣ ተማሪዎች ፣ ወላጆች፣ ሠራተኞች፣ አርሶአደሮች፣ በአጠቃላይ እያንዳንዱ ዜጋ በትግሉ ተሳታፊ እንዲሆን ፣ ትግሉን ወደ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እንዲሸጋግር ጥሪውን ያቀርባል። በሊቢያና፣ በደቡብ አፍሪካ ዘመዶቻቸውን በሞት ላጡ ቤተሰቦች ኮሚቴው የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይገልጻል። ስደት ያብቃ!! ዜግነታችንን የሚያስከብር ሥርዓት ለመፍጠር ቆርጠን እንታገል!! ኢትዮጵያ የጋራ ቤታችን ነች!!

No comments:

Post a Comment