ቤተ-ክርስቲያን የማን ቤት ናት ? የማን ቤት ናት ? የማን ቤት ናት ?
በላስ ቬጋስ ከተማ የምንኖር ህዝበ-ክርስቲያን ፤ በቅርቡ በቤተ-ክርስቲያናችን በደብረ ምህረት
ቅዱስ ሚካኤል ካህናትና በሰበካ ጉባኤው ላይ በተደረገ ምርጫ ምክንያት ችግር ተፈጥሮ ነበር ።
ችግሩን በመመካከር ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ለአመታት ካገለገሉበት ቤተ-ክርስቲያን የአሪዞና
የዩህታና የኔቫዳ ሊቀ-ጳጳስን አቡነ ዮሴፍንና ካህናቱን ከስራ የሚያሰናብት ደብዳቤ ተልኮላቸው
በቅርቡ ወደተገዛው ቤተ-ክርስቲያን ድርሽ እንዳይሉ ይነገራቸዋል ። ጉዳዩ እስከ ፖሊስ ድርሶ
እስካሁን መፍትሄ ያላገኘ ጉዳይ ሆኗል ።
እኔ ዛሬ ይህን መልእክት እንድፅፍ ያነሳሳኝ ማን በደለ ማን ተበደለ ለማለት አይደለም ።
ምንንም ለመወንጀልም ሆነ ለመኮነን ፍላጎትም የለኝም ። ጳጳሱን አቡነ ዮሴፍን ጨምሮ ካህናቱ
ወደቤተ ክርስቲያኒቱ እንዳይደርሱ ህጋዊ ደብዳቤ ከደረሳቸው በኋላ ፤ ለጊዜውም ቢሆን
ምእመናኑን ለመሰብሰቢያ ተከራይተውት ከነበረው ቤተ- ክርስቲያን ድረስ ተሂዶ በሲኖዶስ
የተወገዙ ናቸው አታከራዩአቸው በሚል ካህናቱ ቦታ አጥተው ምእመናኑን ባለፈው ሳምንት እሁድ
በፓርክ ሰብስበውት ፀሎት ተደርጎ ተበትኖ ነበር ። በዚሁ እለት በፓርኩ የተገኘው ህዝበ-
ክርስቲያን በሰርቢያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን የመምለኪያ ቦታ የሚያገኝበትን መንገድ ለመሻት
ረቡዕ ፊብሩዋሪ 25 ቀን ቀጠሮ ይዞ ተለያዬ ።
በቀጠሮው ቀን የተገናኙት ካህናትና ህዝቡ በዬራሳቸው ዝግጅት አድርገው ነበር የመጡት ።
በእለቱ በብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ግብዣ የዲሲና ሜሪላንድና ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ
አቡነ ሳሙኤል ሳይታሰብ በቦታው መገኘት በህዝበ ክርስቲያኑ ላይ ተጨማሪ የደስታ ድባብ
ዘረጋበት ። በመምህር ውብ አምላክ አስተናጋጅነት የተከፈተው የቀጠሮ ጉባኤ በብፁዕ አባታችን
በአቡነ ሳሙኤል ፀሎት ከተከፈተ በኋላ የደብረ- ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ታቦት በሚቀጥለው
ቀን እንደሚገባ ሲበሰር ወይዛዝርቱ በእልልታ ወንዱ በጭብጨባ መዘምራን በምስጋና መዝሙር
አዳራሹን ሞሉት ።
ይህን ብስራት የናኙልን ደግሞ የእለቱን ትምህርት “ቤተ-ክርስቲያን የማን ናት ?”በሚል ርእስ
የጀመሩት ድምፀ- ነጎድጓዱ ሊቀ-ህሩያን ቀሲስ መላኩ ባወቅ ነበሩ ። በትምህርታቸው ላይ
የዚህች ቤተክርስቲያን አባልነታችሁ በአባልነት ፎርም ሳይሆን በጥምቀታችሁ ነው ሲሉ ህዝቡ
በእኩልነትና በአንድነት መንፈስ የኢትዮጵያ ድርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን አባልነቱን አረጋገጡለት ።
ክርስቲያኖች በተሰበሰቡበት ሁሉ የእግዚአብሂር መንፈስ ይኖራልና ፤ እዚህ ቤተ-ክርስቲያን
እንዳትደርሱ የተባሉት ካህናት ህዝቡ በሰጣቸው ፍቅርና ሙቀት ፤ ባሳየቸው አንድነት ፊታቸው
በደስታ ጸዳል ሲሞላና ስብራታቸው ሲጠገን እዚያው የነበርን ሁሉ ምስክሮች ሆንን ።
ንብ ያለአውራው ባዶ እንደሆነ ሁሉ ፤ ህዝበ-ክርስቲያንም ያለ ካህናት ባዶ ነው ። ንብ በአውራው
አማካይነት የመንጋውን ዘር ቋሚ የህይወት ቀጣይነት እንደሚያረጋግጥ ሁሉ ካህናትም
የምእመናኑን መንፈሳዊ ህይወት ጠባቂዎች ናቸው ። በዚህ ወከባና ጩሀቱ በበዛበት አለም
ካህናት የእግዚአብሄር እንደራሴዎች ናቸው ። እነዚህን የመንፈስ አባቶች ነው በሥጋዊው ህግ
በብጥሽ ወረቀት ወደቤተ-ክርስቲያኒቱ እንዳይደርሱ የተወሰነባቸው ።
የአምልኮት ተግባራችንን መፈፀም የሚያስችለን ካህናቱ ስርዓተ-ቅዳሴውን ሲመሩት ብቻ ነው
ያለው ህዝበ-ክርስቲያን አውራዎቹን ይዞ በማምለኪያ ቦታ እጦት ለሳምንታት ተንከራተተ ።
ብርድና ነፋሱ ሳያግዱት ምእመኑ ህጻናት ልጆቹን ይዞ በህዝባዊ ፓርክ ውስጥ የአንድ ሰንበት
አምልኮ አደረገ ።
ከላይ የጠቀስኳት የቀጠሮዋ ቀን ፌብሯሪ 25 በላስ ቬጋስ ኔቫዳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ
ክርስትያናዊ ታሪክ ታላቅ ቀን ሆና የምትታሰብ ናት ። ምሽት ላይ በሰርቢያ ኦርቶዶክስ ቤተ-
ክርስቲያን አዳራሽ የተሰበሰበው ህዝብ ለላስ ቬጋስ አዲስ የሆነውን የደብረ-ብስራት ቅዱስ
ገብርኤል ታቦት በማግስቱ እንደሚገባ ብስራቱን ሲሰማ ፤ ታቦታችንማ በድህነት አይገባም ሲል
ሁለት ሰአት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ $104 ሽህ 845 የአሜሪካን ዶላር በማዋጣት አከበረው ። ወንዱ
የጣቱን የወርቅ ቀለበት ሴቷ የአንገቷን ሃብል እያወለቀች የታቦቱን ግባት ቀን በደስታ አከበርነው ።
በማግስቱም ታቦቱ ሲገባ የዋዜማው በረከት ያልደረሳቸው ወንድሞችና እህቶች እኛስ ለምን
ይቀርብናል በረከቱ ለኛም ለቤታችንም ይትረፍ በማለት ተጨማሪ $23 ሺህ በማዋጣት አዲሱን
ታቦት ተቀበሉት ።
ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ዮሴፍ ካደረጓቸው ንግግሮች ውስጥ አንድ የሩሲያ ሰው የትናገረው ነው
በማለት እንዲህ ያሉት ይጠቀሳል ። “ሰው ገፍቶ ገፍቶ ከክርስቶስ እግር ስር ጣለኝ”አዎ ይህን
የተናገረው የሩሲያ ታዋቂ ደራሲ ደስተዮቭስኪ ነበር ። ደስቶዮቭስኪ በድርሰት ስራዎቹ ምክንያት
ብዙ መከራ ደርሶበታል ። ከዚያም ፍርድ ቤት ቀርቦ የሞት ፍርድ ተፈርዶበታል ። የፍርድ ቀኑ
ደረሰችና የሞት ቅጣቱን ፈፃሚዎቹ የመስቀያውን ገመድ አንገቱ ውስጥ አስገቧት ። ሸምቀቆው
እየጠበቀ እየጠበቀ ትንፋሹ እያጠረች ስትሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ የክርስቶስን ስም ጠርቶ
እንዲያድነው ተማፀነ ። ወዲያው የመሰቀያው ክፍል በር ተከፈተና የሩሲያው ንጉስ መልክተኛ
ፈጥኖ ገባ ። ከንጉሱ የተጻፈውንም መልእክት ከፍ አድርጎ አነበበው ። የሞት ቅጣቱ ተሽሮ
በሩሲያው ንጉስ ምህረት ተደርጎልሃል የሚል ነበር ። ምሳሌው ለሁላችንም ግልፅ ነው ብዬ
እገምታለሁ ።
ህዝብ ያቀፈው ህዝብ የወደደው ዘለአለማዊ ነው ። በላስ ቬጋስ ላለፉት አስራ አራት አመታት
የክህነት ተግባራቸውን ሲያከናውኑ የነበሩት መልአከ-ብስራት ቆሞስ አባ ወልደየሱስም
በተፈጠረው ሁኔታ ምክንያት ጨልሞ የነበረው ፈገግታቸው በምእመናኑ ፍቅርና ሙቀት
እንደተመለሰላቸው ሊቀ-ሕሩያን ቀሲስ መላኩ ባወቅ ሲናገሩ ህዝቡ በእልልታ አዳራሹን ሞላው
።
በመጨረሻም የብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ዮሴፍን መልእክት እንዲህ ይላል ። የአገረ-ስብከቴ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቤተሰቦች ፤ ይህ ያከበራችሁት የደብረ ብስራት
ቅዱስ ገብረኤል ታቦት የገባባት ቤተ-ክርስቲያን አባልነት በጥምቀታችሁ ብቻ ነው ። በተለያዩ
ምክያቶች የአባልነት ክፍያ መክፈል ቢያቅታችሁ እንኳ በጥምቀት የክርስቶስ ልጆች ናችሁና
አባልነት የሚከለክላችሁ የለም ። የአባልነት መታወቂያ ይኖራችኋል ። ዋናው በሃይማኖታችሁ
መፅናት ነው ። ክርስቲያናዊ ፍቅራችሁና አንድነታችሁን እንዲሁም ፅናታችሁን ይህ ክፉ ቀን
አሳይቶናልና አሁን እንዳላችሁት ሁሉ ሳትለያዩ ተፋቅራችሁ ተከባብራችሁ ኑሩ ። እኛ
ለሚበድሉን ሁሉ እንፀልያለን ። ይህ ክርስትያናዊ የተሰጠን ግዴታችን ነው ። ከተለዩን ጋርም
በአምላካችን ፈቃድ አንድ እንደምንሆን ተስፋየ ነው ብለዋል ።
ከዚያም ይህች ቤተ-ክርስቲያን የምትተዳደረውም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ርዕሳነ ሊቃነ
ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ስር ባለው ሲኖዶስ መሆኑንም ገለፀዋል ።
እንግዲህ ቤተ-ክርስቲያን የማናት ? የእግዚአብሄር ቤት ናት ። የናንተ ቤት ናት ፤ እናንተ
በእምነታችሁ በተሰበሰባችሁበት ቤት ሁሉ የእግዚአብሄር መንፈስ አለ ፤ ካሉ በኋላ በዚህ በክፉ
ቀን ሊያፅናኑን ከዋሽንግቶን ዲሲ ድረስ የመጡትን የዋሽንግተንና የሜሪላንድ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ
አቡነ ሳሙኤልን ፤ ከኔው ጋር መገፋቱ የደረሰባቸውን መላከ ብስራት ቆሞስ አባ ወልደየሱስን ፤
ከካሊፎርኒያ ድረስ ሊያበረታቱን የመጡትን ሊቀህሩያን ቀሲስ መላኩ ባወቅን ፤ ከኛ ቀድሞ
የተገፋውን መምህር ውብ አምላክን ፤ ሁሌም ካጠገባችን ሳይለዩ አብረውን የቆሙትን ሊቀ-
ጠበብት ዳኜ ፈረደን ፤ እኛማ ከአባቶቻችን አንለይም ሲሉ አብረውን የተንከራተቱትን ዲያቆናቱን
በመጨረሻም ብርዱም ነፋሱም መንከራተቱም ሳያሸንፋችሁ አብራችሁኝ ለቆማችሁት ልጆቼ ፤
ከቅርብም ከሩቅም በስልክም ሆነ በኢሜል የማፅናኛ መልእክታችሁን ለላካችሁልን ሁሉ
የእግዚአብሄር በረከት ቤተችሁን ይሙላ ፤ የኔም ምስጋና ይድረሳችሁ ፤ በፀሎቴም ሁሌ
አስባችኋለሁ ፤ ብለዋል ።
ከብስራተ-ገብርኤል ፡
ማርች 1 ቀን 2015 ።
No comments:
Post a Comment