Tuesday, February 23, 2016

 ኢትዮጵያ የኦሮሞዎችም ናት!! 12-2-2016 ከብስራት ኢብሳ (ሆላንድ) በዚህ ርዕስ ላይ እንድጽፍ ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያት፣ አቶ ጆሃር መሃመድ “ኦሮሞ የኦሮሚያ ናት” ብሎ በቅርቡ ያወጣውን መጣጣፍ ተመልክቼ፣ እኔም የበኩሌን አስተያየት ሳቀርብ፣ የጆሃር አጀንዳ በትክክል ገብቷቸውና መንገዱ ይጠቅመናል ብለው አቅዋም የወሰዱትን ለማሳመን ሳይሆን፣ የግል አስተያየቴን ለአንባቢዎች ለማካፈል ነው፡፡ በኔ አስተያየት የዘር የፖለቲካ መሪዎች ብዙ ጊዜ እንደዚህ አይነት ከፋፋይና አጨቃጫቂ አጀንዳ ሆነ ብለው የሚመርጡት፣ ሳያውቁ ወይም ሳይገባቸው ቀርቶ ሳይሆን፣ በተለያየ ዕርከን ሊያስፈጽሙ የሚፈልጉትን “ግልጽና ህቡዕ” አጀንዳዎቻቸውን ለማራመድ ይጠቅማል ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡ ለተሳሳተ ጥያቄ ትክክለኛ መልስ አይገኝለትም፡፡ ምክንያቱም ጥያቂው የተዘጋጀው፣ መላሹ እንዲሳሳት እንጂ እንዲመልሰው ስላልሆነ፡፡ የጆሃርም ትንኮሳ(ፕሮቮኬሽን)፣ ሊያስከትል የሚችለውን እሰጥ እገባ ቀድሞ ስለሚያውቀው፣ ለዛ በሚመልሰው መልስ “ትርፉን” አስልቶ ስለሆነ፣ ባጭሩ በቀውስ ውስጥ የራሱን ሥራ እየፈጠረ፣ እኔ እያደርኩት እንዳለው፣ ብዙ ሰዎች ለጆሃር መልስ ይሰጣሉ፡፡ ጆሃርም የመልስ መልስ እየሰጠ እይታ ውስጥ ይቆያል ማለት ነው፡፡ ጆሃርም “ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ናት” ብሎ ያልጨረሰው የሌሎችንም ባለቤትነት እረስቶት ወይም ሳያውቅ ቀርቶ ሳይሆን፣ ሆን ብሎ ማጨቃጨቂያ ክፍተት ለመፍጠር ነው፡፡ አለበለዚያ ቀና አመለካከት ቢኖር? ኢትዮጵያ የኦሮሞዎችም ናት ወይም ኦሮሚያ የኢትዮጵያውያን ናት ብሎ ሰፊ ሕዝብና ትልቅ ግዛታችን ሆኖ ያለውን እውነታ በጠቀሰ፡፡ በሱ አቀራረብ እንዲመለስለት መስማት የፈለገው፣ “ኦሮሚያ የሚባል ሀገር የለም” ተብሎ ተመልሶለት፣ በዛ የተለመደ ጉንጭ አልፋ ክርክርና እንዲጀመርና፣ ጆሃርም በዛ “የኦሮሞ ሕዝብ ሆይ! ማንነትህን ካዱህ! ሀገርህ ያንተ አይደለም አሉህ!”...ወዘተ እያለ ኦሮሞው ከሌላው ወገኑ ጋር ቆሞ፣ ባጠቃላይ ሀገራችን ላይ እየደረሰ ባለው፣ የፍትህ የዲሞክራሲና ኢ ሰባአዊ ድርጊት ላይ ላይ እንዳያተኩርና የሱን ዕቅድ እንዳያደበዝዝ ነው፡፡ ለኦሮሞ ሕዝብ ኢትዮጵያ በሙሉ ሀገሩ ናት፣ ለአማራውም ለደቡቡም ....ወዘተ፡፡ ከዚህ የተለየ አቅዋም “ይቺ ያንተ ናት፣ ያቺ የሌላ ናት” አካሄድ በግልጽ የሚያሳየው ሌላ ያልተደበቀ የኦሮሞን ሕዝብ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር የሚያራርቅ ስልት ነው፡፡ በተለይም ጆሃር በድፍረት፣ “ለኦሮሞ ኬንያም ኢትዮጵያም አንድ ናቸው” ብሎ ሊያስቀምጥ የሞከረው ሌላ ተጨማሪ ትንኮሳ እየቀጠለ...፡፡ ጆሃርን ከጥቂት ዓመታት በፊት መጀመርያ የማውቀው የነበረው ላጠቃላይ ኢትዮጵያኖች በብሔራዊ አጀንዳ ዙርያ ይመለከተኛል ብሎ አብሮ “ተሰልፎ” ከዓለም ዓቀፍ የዜና ማሰራጫዎች እስከ ፌስ ቡክና ፓልቶክ ድረስ የክብር እንግዳ እየሆነ፣ ኢትዮጵያኖች ምክር ሲጠይቁት፣ እየወከሉ በየአደባባዩ ሲያስተዋውቁት ....ወዘተ ነበር፡፡ ባደባባይ ይነግረን የነበረው፣ ከኦሮሞ አባትና ከክርስቲያን አማራ እናት እንደተወለደና፣ ሁሉም ወገኑ ለሱ እኩል ወገኖቹ እንደሆኑ ነበር፡፡ በመሃሉ ስንት ጊዜ አቅጣጫ እንደቀያየረ በቂ መረጃ ባይኖረኝም፣ እስካሁን ድረስ ከማውቀው፣ በጆሃር ውስጥ ብዙ “ማንነቶች” ተንጸባርቀዋል፡፡ እውነተኛው ጆሃር የቱ እንደሆነ ማወቅ ብቸገርም፣ አንድ ነገር በእርግጠኛነት “ከሚያሳያቸው ማንነቶች” መረዳት የሚቻለው፣ ብዙ ለማይታወቁ አጀንዳዎቹ ጭምር ማስፈጸሚያ አድርጎ የመረጠውና እንደ “ጆከር” አሁን የሚጫወትበት “የኦሮሞ ብሔረተኝነትን” ነው፡፡ ከጽሁፉ እንደተረዳሁት፣ ኦሮሞ በሙሉ አንድ አይነት አቅዋም እንዳለው አድርጎ ሲገልጽ፣ “አክራሪ ኦሮሞ፣ ለዘብተኛ ኦሮሞ ...ወዘተ” እየተባለ የሚሰጠውን አስተያየት “የኦሮሞን ሕዝብ ለመከፋፈል የሚጠቀሙበት፣ ጊዜ ያለፈበት ....ወዘተ” ብሎ ነው፡፡ ይህ አይነት አቀራረብ የኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ አንድ ወጥ የሆነ አመለካከት ብቻ ነው ያለው ወደሚለው አደገኛ አቅጣጫ ይወስደዋል፡፡ አንድ ማኅበረሰብ የፋብሪካ ውጤት አይደለም፡፡ በውስጡ ሁሉም አይነት አቅዋሞች ሊንጸባረቁ እንደሚችሉ ማመን አቶ ጆሃርን ለሚያክል የፖለቲካ ሳይንቲስት ይጠፋዋል ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን ምናልባት እንዲፈጸም የሚመኘው በውስጡ ተጽዕኖ እያሳደረበት መሬት ላይ ያለውን ሃቅ አደብዝዞበት ይሆን? ብዬ ከመጠየቅ አላልፍም፡፡ የኦሮሞም ሕዝብ እንደ አንድ ማኅበረ ሰብ በውስጣቸው ተፈጥሮያዊ የሆነ ጤናማ ልዩነት ይንጸባረቃል፡ ፡ በታሪክም ሆነ በዕድሜዬ እንደተረዳሁት፣ የኦሮሞ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ፣ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ሆኖ ለሀገር ዳር ድንበር የተዋደቀ፣ ለአንድነታችን ዋጋ የከፈለ፣ ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር ተዋህዶና ተቀላቅሎ እየኖረ ያለ፣ ብዙ ስመ ጥር ሀገራቸውን የሚወዱ አርበኞች የወጡበት፣ ለሀገር ግንባታውም ከፍተኛ አስተዋጾ ያደረገ ማኅበረሰብ ነው፡፡ የራሱንም ሆነ የሌላውን ባህል ቋንቋና እምነት የሚያከብር ሀገሩንና ሥራ የሚወድ ሕዝብ ነው፡፡ በአንጻሩም በውስጡም፣ የባህል፣ የዕምነት፣ የአኗኗር ልዩነት እንዳለ ሳይረሳ፣ የጨቁኑት፣ ይሸጡትና ያስማሙት፣ ከጠላት ጋር ተሰልፈው የወጉት፣ ለጥቅም፣ ለሥልጣን ብለው የካዱት፣ በስሙ የሚነግዱ፣ የሚሸጡ የሚለውጡ ኦሮሞዎች ሁሉ የነበሩበትና ያለበት ትልቅ ማኅበረ ሰብ ነው፡፡ ሌላው የጆሃር አገላለጽ “በሕዝባዊ ንቅናቄ ውስጥ በቀጥታ በመሳተፍ ጉዳት የደረሰባቸውን ከልብ እንደግፋለን እያሉ ከንፈር በመምጠጥ በሌላ በኩል ደግሞ ታጋዮች አንግበው የተነሱትን መፈክር በመኮነን፣ ድጋፉም ሆነ ከፈር መጠጣው የውሸት እንደሆነ ያሳያል” ይለናል፡፡ ይሄ ጆሃርን አልተመቸኝም የሚለው አካሄድ፣ በግሌ የፖለቲካ ባሕላችን፣ “ከጥቁርና ነጭ የፖለቲካ አካሄድ” መቀየር መጀመሩ እንደሆነ የሚያሳይ ምልክት ስለሆነ፣ እንዲያውም ደስ ሊያሰኘን ነው የሚገባው፡፡ ታጋዮች በማይደግፉት የፖለቲካ አቅዋም ውስጥ ጭምር ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትን ተቃወሙ ማለት፣ በምንጠላው ነገር ውስጥ በጎ ነገርን ማየት መቻል ስለሆነ፣ በበጎ ጎኑ ሊታይና እንዲያውም ሊበረታታ የሚገባ አዲስ የፖለቲካ ጅምር ነው፡፡ በሰሞኑ የኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በስፋት በመንቀሳቀስ እየጠየቁ ያለውን የመብትና የፖለቲካ ጥያቄ፣ ከኦነግና መሰል “ነጻ አውጭ” ድርጅቶች የሥራ ውጤት እንደሆነ ተደርጎ የሚቀርብ የታሪክ ሽሚያ ታይቷል፡፡ በመሠረቱ ኢትዮጵያዊ የኦሮሞ ወጣቶቹ እንዳደረጉት፣ መብት ካለ አግባብ ሲነጠቅ መከላከልም ሆነ መቃወም ትክክልም ተገቢም ነው፡፡ ነገር ግን “የነጻ አውጭ ድርጅቶች”፣ ሁኔታውን ተጠቅመው ሕዝብን ከፋፍሎ ወደ እርስ በእርስ ግጭት ሊወስድ ወደሚችል፣ ለጠባብ የፖለቲካ ዓላማ ሊጠቀሙበት ሲሞክሩና ሁኔታው ተመቻቸልን ብለው በወጣቶቹ ትከሻ ፕሮፓጋንዳውን ሲያጦዙት፣ ሀገራችን እንዳትበታተን የምንፈልግ ሰዎች ፈርተንና ቆም ብለን አስበን፣ ጉዳዩን ለጠባብ የፖለቲካ ፍጆታ ብቻ መጠቀሚያ ከማድረግ፣ ወደ ብሔራዊ ትግሉ ከፍ አድርጎ ለሁሉም ሊጠቅም በሚችል መልኩ፣ እንቅስቃሴውን አስፍቶ የጋራ ለማደርግ መሞከርና፣ ሲቃወሙ ለተጎዱት ወጣቶች ወገናዊነትን ማሳየት ትክክለኛ አቅዋም ነው፡፡ ትክክል የማይሆነው አንዳንዶች እንዳደረጉት፣ የጥያቄውን ይዘት ብቻ በመመዘን፣ ከነገሰባቸው የውስጥ ፍርሃት ወይም ጥላቻ ተነስተው ከኋላው የፖለቲካዊ ትርጉም ብቻ በማንጠልጠል፣ “ይበለው፣ የተሳሳተ ጥያቄ ስለጠየቀ” ብለው፣ ወተት እንደሰረቀች ድመት በወጣቶቹ ላይ የተፈጸመውንም በደል አላየንምና አልሰማንም ብለው ሲያደፍጡ ነው፡፡ የዘር ግድብ ሳይገድባቸው፣ የፖለቲካ ልዩነት ሳይከፋፍላቸው፣ ሥርዓቱ በመላ ሀገሪቱ ውስጥ እያደረሰ ያለውን ችግር እኩል ሊያሳይ የምችል ሚዛናዊ የሆነ መፈክር አዘጋጅተው አሉ የሚባሉትን ችግሮች በጋራ ሲያሰሙ መውጣታቸው ያስመሰግናቸዋል እንጂ፣ የጆሃርን የፖለቲካ አቅዋም ብቻ ሙሉ ለሙሉ ስላላንጸባረቁ ሊወቀሱ ባልተገባ፡፡ ምናልባት ወጣቶቹ እንደጀመሩት፣ ትግሉን አፍኖ አቅጣጫ በማስቀየር፣ የፖለትካ ሞሳ ሰርቶ የሻንፒዮን ዋንጫ ለብቻ ለመውሰድ ከመሞከር ይልቅ፣ አጋጣሚውን በመጠቀም ተቻችሎ አብሮ መቆም የጀመረውን በማበረታታት፣ ጽንፍ የቆሙትን ወደመሃል ባማምጣት፣ ከፓርቲና ከተወሰነ ቡድን ጥቅም ፍላጎት ከፍ አድርጎ ወደ ሀገራዊ የረዥም ጊዜ ጥቅም፣ ትኩረት ቢሰጥ እንደ ጥሩ ጅምር ሆኖ፣ ብዙ ውጪ የቆሙትንም እንደሚስብ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በመጨረሻ ሳልጠቅስ የማላልፈው፣ ከአቶ ጆሃርና ተመሳሳይ አቅዋም ካላቸው በተደጋጋሚ ያስደመጡንም ሆነ የአስነበቡን፣ “የኦሮሞ ወጣቶችን ለመብታቸው እንዲቆሙና እንዲታገሉ በረዥሙ ሰርተው የገነቡት ጥረት እንደሆነ ነው”፡፡ እኔ የማየው በሌላ መንገድ ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች በዜና ማሳራጫ አውታሮች እንዳየናቸው፣ ዕድሜያቸው ቢበዛ ከ15 እስከ 25 ዓመት ቢደርሱ ነው፡፡ አብዛኞቹ ወያኔ ስልጣን ከያዘ ቦኋላ የተወለዱ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ቋንቋንና ዘርን...ወዘተ መሠረት ባደረገ “የፌዴራል”ሥርዓት ውስጥ፣ ከክልል እስከ ቀበሌ፣ በጎሳ ድርጅት ሃላፊዎችና ካድሬዎች፣ ስለ ክልላቸውና የወጡበት ማኅበረሰብ ብቻ እንዲያስቡ፣ በሬዲዮን፣ በቴሌቪዥን፣ በዕድር፣ በዕቁብ፣ በየስብሰባው፣ የኦሮሞ ክልል፣ የአማራ ክልል፣ የደቡብ ክልል...ወዘተ እየተባሉ ያደጉ ናቸው፡፡ እንደ እኛ በአንድነት ውስጥ የነበሩትን በጎ ነገሮች ለማየትም ሆነ ለመስማት አልታደሉም፡፡ ከፓርላማ እስከ ቀበሌ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ወጪ እየወጣ የአንድ ጎንዮሽ የሆነውንና ያልሆነውን፣ አሉታዊ የተጋነኑና የተፈበረኩ ታሪኮች ሲጠቀጠቅ ለኖረው ምስኪን ወጣት፣ አቶ ጆሃር የተወሰነ ውጤት ቢያዩ “እኛ ሰራነው” ብለው ሊኩራሩ አይገባም፡፡ የአንድነቱ ደጋፊ ይህንን አይነት ዕድል ቢያገኝ፣ ሃያ አምስት ዓመት አይደለም በግማሽ ዓመት ውስጥ ምን አይነት ሥራ ሊሠራ እንደሚችል ቢታይ፣ እነ አቶ ጆሃርን ሥራ ፈት አድርጎ ያስቀምጣቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ይህንን አብሮ የኖረ ሕዝብ ለራሳችሁ ፍላጎት ብላችሁ ለመለያየት አትሞክሩ፡፡ ሕዝብ እንደሆን ተዋህዷል፣ ንጹህ የሚባል ዘር ያለው በሁሉም ማኅበረ ሰባችን ውስጥ ባሉ ዘረኞች ጭንቅላት ውስጥ እንጂ ያልተቀላቀለ የለም፡፡ በሁሉም ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ጎጠኛ ልሂቆች ወደ ሕዝብ የሚገፉት እንጂ በሕዝብ ማሃል ችግር የለም፡፡ ደሞም ዘር አንመርጥም፣ በኢዮጵያዊነታችን ኦሮሞም፣ ጉራጌም፣ አማራም ....ወዘተ ሁሉንም ነን ማለት መብት ነው፡፡ ኦሮሞን ጨምሮ የሁሉም ወገናችን ችግር ይመለከተናል ብለው ጸንተው የቆሙ ሚሊዮኖች እንዳሉ አትዘንጉ፡፡ ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ከዘር ፖለቲካ ጫጫታው ስለራቁና እንደ ጎጠኞች ጮክ ብለው ጆሮዋችንን ስላላደነቆሩት፣ የዘር ፖለቲካ ስለሚደግፉ ነው ብሎ ለማመን መሞከር እራስን ማታለል ነው፡ ፡ ከሰማንያ የሚበልጡ ብሔረሰቦች ባሉበት ሃገራችን ውስጥ፣ ሁላችንም ለየራሳችን የምንፈልገው አይነት ዕቅድ እያወጣን ሁሉም ይቀበለው ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ ለሕዝባችን የሚበጀው ልዩነት ሳይሆን አንድነት ነው፡፡ በዘር በኃይማኖትና በፖለቲካ አቅዋም ተከፋፍሎ የቆመውን ምሁር፣ ሁሉም የራሱን አጀንዳ ብቻ ቢገፋ፣ ሁሉም ተሸናፊ እንደሚሆን አምነን፣ በእውነት ስለ ሀገርና ሕዝብ ከሆነ ትግሉ፣ ትክክለኛ መንገዱን የሀገራችን ልሂቃን ይጠፋቸዋል ብዬ ለመምከር አልሞክርም፡፡ ኢትዮጵያ የኦሮሞዎች፣ ኦሮሞም የኢትዮጵያውያኖች ናት፡፡ ሀገራችንን ከአውቆ አጥፊ ይጠብቅልን፡፡ ብስራት ኢብሳ tebaber@gmail.com 

No comments:

Post a Comment