በኦሮምያ ክልል የተጀመረው ሕዝባዊ ንቅናቄና
የሃገራችን መጻሒሁኔታ!
ከኃይለገብርኤ አያሌው
ሃገራችን በረጅም ዘመን ታሪኳ አያሌ ግጭትና ጦርነቶችን እስተናግዳለች ።
በተደጋጋሚ ሕልውናዋን ሊያጠፉት የተቃረቡትን የውጭና የውስጥ አደጋዎች ተቋቁማ ዛሬ
የደረስንበት ዘመን ላይ ደርሳለች። በነዚህ ዘመናት ውስጥ የገጠሟትን ችግሮች ፤ ዘር
ሃይማኖት የቋንቋ ልዩነት ሳይገድባቸው ቆራጥና አስተዋይ ልጆቿ በሕብረት በከፈሉት ወደር
የለሽ ተጋድሎ ሕልውናዋን እስጠብቃ ኖራለች። ሃገራችን ከዓለም ቀድምት ከሆኑት
የስልጣኔና ፈር ቀዳጅ ጥቂት ሃገራት ተርታ የሚቆጠር አኩሪ ታሪክ ያላት ፡ በምድር የከበረች
በሰማይም የተመሰገነች ፤ የቅዱሳን መሸሸጊያ የነጻነት ተምሳሌት ሆና ታፍራና ተከብራ
መኖሯ እርግጥ ነው።
ኢትዮጵያ ዙሪያዋን በከበቧት እረፍት የለሽ የቅርብና የሩቅ ጂዖ ፖለቲካዊ
ስትራቴጂካዊና ታሪካዊ ጠላቶቿ ሴራ በተራዘመ የግጭት አዙሪት ውስጥ ወድቃ እንድትኖር
የቀበሩት ግዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጂ በተደጋጋሚ ጉዳት ሲያደርስብን ቆይቷል። እነዚሁ
ከራሳችን ሊወርዱ የማይሹት ባላንጣዎቻችን የተንኮል ሴራ ፍላጎታቸውን ሊያስፈጽሙ
የሚችሉ ሃገር በቀል እንደ ሕውሃት ያለ ቅጥረኛ ባንዳዎች ያልተቋረጠ ድጋፍ ሲሰጡ
ቆይተዋል። በዚህም ትላንት በቀጥታ ያልቻሉትን በገዛ ወንድሞቻችን ጀርባ ተረማምደው
የሃገራችንን ሕልውና በማፍረስ ሃገሪቱን በእጅ አዙር ለመቆጣጠር ብዙ ግዜ ሞክረው
ያልተሳካላቸው ፖሊሲ ይህው በ 21 ክ/ዘ ተሳክቶላቸው በባህል በሃይማኖት በጋብቻና በዕለት
ተዕለት ሕይወት ተቆራኝቶ ተስማምቶ ለዘመናት የኖረውን ሕዝባችንን በዘውግ ፖለቲካ
ተከፋፍሎ፤ ያለፈ ታሪክ ማጥ ውስጥ ጥለውን እርስ በዕርስ እንድንጠፋፋ ሲያመቻቹን
ከርመዋል። ሕወሃትና ሸሪኮቹ ሃገራችንን እየቀሙን በስደት የባዕዳን አሽከር በሃገራችንም
ሁለትኛ ዜጋ ሆነን ተነጣጥለን እንድንቆም ማድረግ በመቻላቸው ብሶትና መከራችን የጋራ
መሆኑ ቀርቶ ክልልን የማይሻገር በጎጥ የታጠረ የተናጥል እንዲሆን ተድርጎ ቆይቷል።
በተለይም አውሮፓውያን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ስጋ ተከፋፍለው ባካሄዱት
ሕገወጥ የጭካኔ ወረራ ድፍን አፍሪካን ተቀራምተው ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲበቁ ፤
እንቢኝ አሻፋረኝ ብለው ለቅጥሯ ዘብ ሆነው ወራሪዎችን አይቀጡ ቅጣት እየቀጡ
የሃገራችንን ሕልውና ለማስጠበቅ አባቶቻችን ቢችሉም ፥ ይህ ሽንፈት ያልተዋጠላቸው
ምዕራባዊ ተስፋፊ ሃይሎች ከገዛ ልጆቿ ማህል በመለመሏቸው ባንዳና ሹንባሾች ፤
በብሔሮች መካከል ጸንቶ የኖረውን ውህዳዊ የአብሮነት ኑሮ ለመበረዝ ጨቋኝና ተጨቋኝ ፤
ቅኝ ገዥና ተገዢ የሆነ ሃገር በቀልና ብሔርን መሰረት ያደረገ አስተዳደር እንዳለና እንደነበር
አድርገው የረጩት ፕሮፓጋንዳና ያቀዱት የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ ዘመን ተሻግሮም ቢሆን
ሊሰምርላቸው ችሏል።
በዚህ ባለንበት የ21ኟው ክፍለ ዘመን ዓለም በቴክኖሎጂ መንጥቆ የመገናኛ
ዘዴዎችን ባቀለለበት የህዝቦች የባህል ፤ የኢኮኖሚና የጸጥታ ጉዳዮችን በቀላሉ ከአንዱ
ወደ ሌላው ክፍለ ዓለም በሰከንድ መረጃ በሚያደርስበት ግሎባላይዜሽን በሚዘመርበት
የሃሳብ የበላይነት ገኖ በወጣበት በዚህ ባለንበት ዘመን ራሱን የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት
ብሎ የሚጠራው ፤ ከቅኝ ገዥዎች መቃብር ላይ የበቀለ የጥፋትና የዘረፋ ቡድን ዘመን
የሻረውን ሗላ ቀርና በታኝ የከፋፍለህ ግዛው ፍልስፍና በሃገራችን ላይ አንብሮ በተንኮልና
በአሻጥር ሲያተራምሰን ቆይቷል።
ይህ ከዘመኑ አስተሳሰብ የተጣላ የዕውቀት ጠር ጨካኝና አረመኔ አገዛዝ ባለፉት 25
አመታት ሃይማኖትን በሃይማኖት ፤ ብሄርን ፤ ከብሄር የሚያጋጭ ክፉ ፖለቲካ ሲያራምድ
ቆይቷል። እንደዚህ ፋሽስታዊ ቡድን ቅስቀሳና ፍላጎት ምንም ሕዝባችን ወደ አጠቃላይ
ግጭት ባያመራም ፤ ነገር ግን ጸንቶ የኖረውን የሕዝባችንን አብሮነት በማወክ ለጋራ ሃገራዊ
አላማዎች የጋራ ሕብረት እንዳይኖረው ማድረግ የሚያስችል መሰሪ ዕቅዱ ለረጅም ግዜ
ተግባራዊ ሆኖ ቆይቷል። ዛሬም ቀጥሏል ። ለነገም ይህን እኩይ ሴራ ነቅቶ ማክሸፍ
የማይቻል ወገን ካለ መከራውም ይረዝማል ፥ ልዩነቱም ይሰፋል ፤ ባርነቱም ፤ ይቀጥላል!!
ለዘመናት በአንድነት የኖረው ሕዝባችንን አንድነቱን አላልቶ በቅራኔ አፋጦ ባለፈ
የታሪክ ጠባሳ ላይ ስንታገል ሕወሓት ግን አፓርታይዳዊ ዘረኛና ዘራፊ አገዛዙን በላያችን
ጭኖ ያሻውን ሲያደርግና ሲፈጽምብን ቆይቷል። የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ይህው
የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ እስከግዜውም ቢሆንም ተሳክቶለት ፤ አማራው ሲጠቃ ፤ ኦሮሞው
ቆሞ እንዲያይ ፤ ኦሮሞው ሲጎዳ አማራው በጸጥታ ሲያልፈው ፤ እንዲሁም ክርስቲያኑ ችግር
ሲገጥመው ሙስሊሙ ዝም ሲል ፤ ሙስሊሙን ጉዳት ሲገጥመው የክርስቲያኑ ጸጥታ እስከ
ተወሰነ ግዜ ገዥዎችን ሲጠቅም ቆይቷል። በነዚህ ዘመናት የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት
እያፈራረቀ በተለያየ አጀንዳና ግንባር የሚፈልገውን እየደፈጠጠ አገዛዙን በሕዝብና በሃገር
ላይ አጽንቶ ልክ እያስገባን ይገኛል።• ።
የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የረጨው የጥላቻና የመለያየት መርዝ ነቅቶ በግዜ
በማርከስ ሕዝብን ማቀራረብ የነበረባቸው የአማራውና የኦሮሞ ምሁራን መካከል ተካሮ
የቆየው ልዩነት ለዘረኛው አገዛዝ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩም በላይ ሁለት ግንባር በአንዴ
ከማጥቃት ተቆጥቦ ስልታዊና ታክቲካዊ ሽግሽግ በማድረግ የግዜና የሁኔታዎችን አመቺነት
እያሰላ ፤ በተከታታይ እንደታየው የተነሳበትን ሕዝባዊ ተቃውሞና የአመጽ እንቅስቃሴ
ለማዳፈን አንዱን በሌላው ላይ እየቀሰቀሰ ከጎኑ ለማሰለፍ ሲችልና ሲያደርግ ቆይቷል ፤
አሁንም ያንኑ ስልቱን በመቀመር በከፋና ምንአልባትም ሃገሪቷን ሊበታትን የሚችል የዘር
ግጭት ለመቅስቀስ እየተንቅሳቅስ ለመሆኑ ከሚወጡት መረጃዎች መረዳት ይቻላል።
በተለይም ባልፉት አራት አስዕርተ አመታት ውስጥ በአንዳንድ የኦሮሞ ምሁራን
ተላላነት በጥቂት ሆድ አድሮችና በእንዳንድ ጽንፈኞች ቅንብር እና በትግራይ ነጻ አውጪ
ድርጅት አዝማችነት በተሳሳተ ፕሮፓጋንዳና በተንሸዋረረ የማንነት ውዥንብር የኦሮሞን
ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነት ማዕከል ለመነጠል ያልተቋረጠ ሴራ ሲራመድ ቆይቷል። የዚህም
ሴራ ዋና አላማ እንዱ የኦሮሞ ማሕበረሰብ ዙሪያውን ካሉት ሌሎች ብሄሮችና ከእንድነት
ሃይሎች ጋር ያልተቋረጥ ቅራኔ ውስጥ ከቶ ፋታ በመንሳት በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገውን
የኦሮምያ ምድር በምስለኔዎቹ ተረማምዶ ለዘመናት ትቆጣጥሮ ያለ ከልካይ ሲመዘብር
ለመኖር ካለው ሕልም የተንሳ ነው።
በዚህም የሴራ ቅመራ ባለፉት አመታት እንደሆነውና እንደታየው ፥ በተለይ የአማራ
ተወላጆችን ከኦሮሞ ማህበረሰብ ፍላጎትና ፈቃድ ውጪ የጥላቻ ቅስቀሳ በማድረግ
በካድሬዎቹ አዝማችነት ተወልደው ካደጉበት ፤ ለፍተው ያፈሩትን ሃብትና ንብረት እየቀሙ
ከክልሉ በገፍ እንዲባረሩ ሁን ተብሎ በትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት በተቀነባበረ ሴራ በብዙ
ሺህ በሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ላይ የጅምላ ግድያና ፥ የዘር ማጥፋት ወንጀል በኦሮሞ
ነገድ ስም ሲፈጸም ቆይቷል። ዛሬም ይህው ሴራ ቀጥሏል ፥ ነገም በጋራ ካልቆምን ካሁን
ቀደሙም የከፋ የእርስ በዕርስ መተላለቅ ሊከሰት እንደሚችል ለመረዳት ነብይ መሆን
አይጠይቅ።
ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ነው ፤ ኢትዮጵያም የኦሮሞ ናት! ይህን ሊፍቅና ሊያስቀር የሚችል
ምንም ውሃ የሚቋጥር ምክንያት የለም። የኦሮሞ ልጆች ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና
ለወሰኗ ክብርና ለሉዓላዊነቷ ወደር የሌለው መስውዕትነት ሲከፍሉ ኖረዋል። ይህንን የክብርና
የኩራት ታሪክ ንደው የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን ከሃገራዊውና ከአህጉራዊው ተምሳሌታዊ
ሕዝብነት አርቀው የባርነትንና የተገዥነትን የሃሰት ማቅ ሊያለብሱት በጠባብ
ብሔረተኝነትና በጨለምተኛ የስሜት ፖለቲካቸው እሳት ውስጥ ትውልዱን ሊጥሉት
የሚራወጡ ጽንፈኞች የሚያራምዱት ኦሮሚያ ለኦሮሞ የሚል ከፋፋይና አፍራሽ እንቅስቃሴ
ለማንም የማይጠቅም ዘመኑን ያልዋጀ መፈክር ነው።
እርግጥ ነው ፥ መላው ሕዝባችን በየግዜው በተፈራረቁት መንግስታት ሲበዘበዝና
ሲጨቆን የመኖሩን ሃቅ ሊዘነጋ የማይችልና ጠባሳውም ያልጠፋ ነው። ነገርግን ትላንትም
ሆነ ዛሬ ጥቂት መሳፍንት ባላባትና ኤሊቶች ፥ ከአንዱ ወይ ከሌላው ብሄር በቁጥር ልቀውና
የስልጣን ወንበር ይዘው ቆይተው ሊሆን ይችላል። አንድ ብሄረሰብ አጠቃላይ ተጠቃሚና
የበላይ ሌላው ጎሳና ነገድ ተገዥ የሆነበት የመንግስት መዋቅር ፥ አልነበረም ፥ የለምም ።
ምናልባት ዛሬ የትግሬዎች የበላይነት አለ የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል። እርግጥ
ነው በሃገራችን ታሪክ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ በማይታወቅ ደረጃ የሃገሪቱን የስልጣን ፥
የኢኮኖሚ ፥ ወታደራዊና ፥ ማህበራዊ ሴክተሮች ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በትግራይ
ተወላጆች ተይዞ ለመገኘቱ አይን የሚያየው ሃቅ ነው። ይህም ሆኖ ግን በስመ ትግሬነት
ሁሉንም የብሄሩን ተወላጆች ከስልጣኑም ከዘረፋውም እንጥፍጣፊው ያልደረሳቸውን
ጨምሮ በአንድ ቅርጫት ከቶ የመፈረጁ አተያይ ተገቢም አስፈላጊም አይሆንም። ዛሬ
ሕዝባችንን አለያይቶ የዘረፋ አገዛዙን ያነበረው የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ፥ ለዚህ አሁን
ለደረሰበት ልዕልና ያበቃውን የትግራይ አርሶ አደር ክዶ ብዙ ሺዎች የከፈሉትን የሕይወትና
የአካል መስዋዕተነት ረስቶ ቁንጮ መሪዎቹና አጫፋሪዎቻቸው በሃብት ላይ ሃብት
ሲያካብቱ ፥ የራሳችውን መደብ ለይተው በቅንጡ ቪላ ሲምነሸነሹ ያስተዋልው የትግራይ
ሕዝብ አፓርታይድ መንደር ሲል ብሶቱን መግለጹ ይታወሳል።
ዛሬ ለደረስንበ ሃገራዊ ውድቀት አያሌ ምክንያቶች መጥቀስ ይቻላል ነገር ግን
እንደ አንድ የዚህ የጥበብና የግሎባልይዜሽን አለም ውስጥ እንዳለ እንድ ሕብረተሰብ ዛሬም
በዛው እንዲያውም በባሰ ደረጃ ተዳክመን ለመገኘታችን ተጠያቂው ማን ነው። ሃገራችንን
በብረት ክንዱ ደቁሶ የከፋፍልህ ግዛው ያረጀና ያፈጀ ሃገር በታኝና ትውልድ እውዳሚ
የጥላቻና የጎሳ አስተሳስብ እየገዛ ያለው የህውሃት ቡድን በዋናነት ሊጠቀስ የሚችል ቢሆንም
፤ ይህ እኩይ ሴራ በአንድም ሆን በሌላ ምክንያት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ተቀብለን ፤
ዘውገኛ አመለካከትን ያራባንው ፤ በጠባብና ግትር አመለካክት ተካርን ለዘመናት ተዋልዶና
ትጋብቶ በፍቅርና በአብሮነት የኖረውን ሕዝባችንን ጠላቶቻችን ዘር መሰረት ያደረገ ግንብ
ሲያጥሩልን ድንጋይ ያቀብልነው ፤ አጥፊነቱን እያወቅን በዝምታ ያለፍንው ፤ ጊዚያዊ
ጥቅምና ጎጠኘነት አይሎብን ጸጥታን የመረጥንው ፤ ሁላችንም የተጠያቂንቱን ድርሻ
ማንሳት ይኖርብናል ።
ታሪክ ሠሪው ሠፊው ሕዝብ ነው አዋቂዎች እንዲሉ ፤ የትላንት ገናናነታችን
የዛሬው ውድቀታችን ተመስጋኙም ሆነ ተወቃሹ በዘምኑ ያለ ትውልድ ነው። ቀደምት
አባቶቻችን ዘርና ሃይማኖት ቋንቋና ነገድ ሳይሉ ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን
ከስክሰው ቢያንስ በዓለም አደባባይ አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ ታላቅ የስነልቦና
ውርስ ትተውልን አልፈዋል።
ዛሬም ያለነው ትውልዶች ከቀደሙት አባቶቻችን መልካሙንና በጎውን ባህልና ፥
እሴት ጠብቀን አሮጌውን ጥለን እንደ ግዜያችን ዘመን የዋጀው ህይወት እንዲኖረን ፤
ለመብትና ነጻነታችን ዋጋ ሰጥተን ራሳችንን አስከብረን ሌሎችንም አክብረን ለመኖር
የሚያስችል አስተዳደራዊ ስርዕት በሃገራችን እንዲኖር ፤ አሮጌ አስተሳሰቦችንና የጭቆና
መዋቅሮችን እጅ ለእጅ ተያየዘን አፍርሰን የሕዝቦችን መብት የሚያከብር መንግስታዊ
ስርዓት ልንመሰርት የሚያስችለንን ትግል በጋራ ልናደርግ ይገባል ።
በአሁኑ ወቅት ሃግራችንን የገጠማት የህልውና አደጋ ከምን ግዜውም የከፋ ሆኖ
ይታያል ። የሕወሃት መራሹ ዘረኛና አፓርታይዳዊ አገዛዝ ባለፉት ሁለት አስዕርተ ዓመታት
ሲከተለው በቆየው የጥቂት ወገኖችን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ የአገዛዝ መዋቅርና የኢኮኖሚ
ፖሊሲ የፈጠረው የጭቆናና የችጋር ወጀብ ሃገራችንንና ሕዝባችንን ውድቀት አፋፍ
አድርሶዓታል። ይህ ሃገራዊ አደጋ እንዳይከሰት አስቀድመው ድምጻቸውን ያሰሙ የፖለቲካ
መሪዎች የኢኮኖሚ ባለሙያዎችና አክቲቪስቶች የተለያየ ስንካላ ምክንያትና የፈጠራ
ወንጀል እየከሰሰ ከሃገራዊ ጉዳይ እንዲገለሉ ሲያደርግ ቆይቷል።
ሕወሃት ላለፉት 25 አመታት ቁልፍ የስልጣን ቦታዎችን ያለተቀናቃኝ ይዞ በመቆየቱ
በሕዝባችን ላይ የፈለገውን ሲያደርግ ሊገድበው የሚችል ሳይኖር ቆይቷል። የዚህ የግፍና
የጭካኔ ሰለባ የሆነው መላው ህዝባችንን በየግዜው ከማሃሉ ብሶቱን ብሶቴ ብለው
በአደባባይ የታገሉትን ፖለቲከኞችን ጋዜጠኞችና የመብት ተከራካሪዎች ሲገልና ሲያስር
የቀሩትንም ያለፍላጎታቸው ሃገር ለቀው እንዲሰደዱ አድርጓል።
ሕዝባችን ሕወሃት ባነበረበት አስከፊ የድህነት ሕይወት የሚካሄድበትን ጭቆና
በጋራ መከላከያ እንዳይቻል በእለታዊ ኑሮው እንዲጠመድ ሁን ተብሎ ከመደረጉም በላይ
አንዳንዴም ገንፍሎ ሲወጣ የተወሰደበት ምህረት የለሽ ጭፍጨፋ አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር
አስገድዶት ቆይቷል። የአገዛዙን ግፈኛ እርምጃ በትግዕስት ችሎና በፍርሃት ተሽብቦ
መቀመጡ ይበልጥ ልባቸው እንዲደነድን የሆኑት የህወሃት መሪዎች የከተማውን ሕዝብ
በግፍና በገፍ አፈናቅለው ራሳቸው ለፈጠሯቸው የጠፍ ጨረቃ ከበርቴዎች አከፋፍለዋል።
በከተማ የጀመሩትን የመሬት ዝርፊያና ቅርምት አልበቃ ብሎዐቸው የገጠሩን አርሶ አደር ያለ
ተመጣጣኝ ካሳ ከመሬቱ እያፈናቀሉ ለድህነትና ለጎዳና አዳሪነት አድርገውታል።
በኦሮሚያ ከአመት በፊት ይህንን ግፍና በደል ያስተዋሉ የምስኪን ገበሬዎች ዋይታና
እንባ ያስቆጫቸው ተማሪዎች በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመቃወም አደባባይ በወጡ
ተማሪዎች ላይ እብሪተኛው የሕወሃት አገዛዝ የለመደውን ጭፍጨፋ በማካሄድ
ተቃውሞውን ለማርገብ የቻለ መስሎት ቆይቷል
ብሶት ጭቆናና ፥ የመብት ረገጣ እስካለ ድረስ ትግል መኖሩ እይቀርም ። በኦሮምያ
የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን መሰረት በማድረግ ዳግም ሌሎች በደሎች ገፊ ምክንያት
ታክሎበት የፈነዳው አመጽ ከመጀመሪያው በይዘትም በመጠንም ሆነ በአይነት የተለየ
ከመሆንም በላይ ሕወሃትን በጣም የተገዳደረ ፥ ተምሳሌትነቱ ለመላው የሃገራችን ሕዝቦች
የሆነ ፥ የጸረ አፈና ትግልን መረብ በጣጥሶ ፤ ሕዝባዊ እንቢተኝነትን ያሳየ ፥ ጠንካራ የለውጥ
ሃይል የታየበት ፥ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት መግደል እስከ ቻለ ድረስ ለመሞት የቆረጠ
የማይፈራ ትውልድ በየአደባባዩ ለፍትህ የተሰዋበት ፥ ወጣት ህጻን አዋቂው በጋራ በሰው
በላው የወያኔ አጋዓዚ ወታደሮች አፈሙዛቸው ስር በድፍረት በሰላማዊ መንገድ
ተቃውሞዎች ሲያሰማ በየማህበራዊ ሚድያዎች ተመልክተናል ።
በኦሮምያ በተለያዩ ቦታዎች ላለፉት ተከታታ ወራት ሲካሄድ የቆየውና አሁንም
እንደቀጠለ ያለው ሕዝባዊ ትግል ከዚህ ሁሉ መስዋዕትነት በሗላ እንዳይቀለበስ የፖለቲካ
ሃይሎች ና ሲቪክ ተቋማት በመሰብሰብ ፥ ከዘውገኝነት ከፍ ያለ ሃገራዊነት የተላበስ ፤
በፋሽስታዊው የሕወሃት አገዛዝ የተማረረውን መላውን ሕዝባችንን ያሳተፈ የተቀናጀና ፥
በስልት የታጀበ ሕዝባዊ ትግሉ እንዲፋፋምና ለውጤት እንዲበቃ አመራር ለመስጠት
በሚያስችላቸው ደረጃ ልዩነታቸውን ወደ ጎን በማድረግ በዚህ ቀውጢ ወቅት ለሕዝብ
ያላቸውን አጋርነትን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
ይህ በኦሮምያ ክልል ያሉ ትንታግ ወጣቶች የተጀመረው መሬት አንቀጥቅጥ
የሰላማዊ ትግል ሕዝባዊ ንቅናቄ የሃገራችንን መጻሒ እድል ሊወስን የሚችል እንቅስቃሴ
በመሆኑ ፤ ወደ ሌሎችም ክልሎች ተዳርሶ በእንድ የጋራ አጀንዳና መፈክር ስር ታጅቦ ለስር
ነቀል ለውጥ ትግሉን ለማብቃት ሁሉም ወገን በየአካባቢው መንቀሳቀስ ይኖርበታል።
ህዝባችን የወያኔ አገዛዝ ሰልችቶታል ፥ ከጥቂት የዘረፋው ተቋዳሾች ውጪ ይህንን
መንግስት እንዲለወጥ የማይፈልግ ወገን የለም ።ይህንን የሚሊዮኖች የጋራ ብሶት
አንቀሳቅሶ ወደ ሕዝባዊ እንቢተኝነት ለመለወጥ የሁሉም ወገን የጋራ ጥረትን ይጠይቃል።
ይህም ሲባል ለጥቂት የፖለቲካ ሃይሎች ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉም ያገባኛል የሚል ዜጋ
በያለብት በሚችለውና ባለው እቅም ተሳትፎ የማድርግን ሃላፊንትን በመወጣት የተጀመርው
ሕዝባዊ እንቢተኝነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ የሁኑንም ወገን ጥረት ይጠይቃ ።
እግዚያብሔር ኢትዮጵያን ይባርክል ! !
Tuesday, February 23, 2016
ኢትዮጵያ የኦሮሞዎችም ናት!! 12-2-2016
ከብስራት ኢብሳ (ሆላንድ)
በዚህ ርዕስ ላይ እንድጽፍ ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያት፣ አቶ ጆሃር መሃመድ “ኦሮሞ የኦሮሚያ ናት” ብሎ
በቅርቡ ያወጣውን መጣጣፍ ተመልክቼ፣ እኔም የበኩሌን አስተያየት ሳቀርብ፣ የጆሃር አጀንዳ በትክክል
ገብቷቸውና መንገዱ ይጠቅመናል ብለው አቅዋም የወሰዱትን ለማሳመን ሳይሆን፣ የግል አስተያየቴን
ለአንባቢዎች ለማካፈል ነው፡፡
በኔ አስተያየት የዘር የፖለቲካ መሪዎች ብዙ ጊዜ እንደዚህ አይነት ከፋፋይና አጨቃጫቂ አጀንዳ ሆነ
ብለው የሚመርጡት፣ ሳያውቁ ወይም ሳይገባቸው ቀርቶ ሳይሆን፣ በተለያየ ዕርከን ሊያስፈጽሙ
የሚፈልጉትን “ግልጽና ህቡዕ” አጀንዳዎቻቸውን ለማራመድ ይጠቅማል ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡
ለተሳሳተ ጥያቄ ትክክለኛ መልስ አይገኝለትም፡፡ ምክንያቱም ጥያቂው የተዘጋጀው፣ መላሹ እንዲሳሳት
እንጂ እንዲመልሰው ስላልሆነ፡፡ የጆሃርም ትንኮሳ(ፕሮቮኬሽን)፣ ሊያስከትል የሚችለውን እሰጥ እገባ
ቀድሞ ስለሚያውቀው፣ ለዛ በሚመልሰው መልስ “ትርፉን” አስልቶ ስለሆነ፣ ባጭሩ በቀውስ ውስጥ
የራሱን ሥራ እየፈጠረ፣ እኔ እያደርኩት እንዳለው፣ ብዙ ሰዎች ለጆሃር መልስ ይሰጣሉ፡፡ ጆሃርም የመልስ
መልስ እየሰጠ እይታ ውስጥ ይቆያል ማለት ነው፡፡
ጆሃርም “ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ናት” ብሎ ያልጨረሰው የሌሎችንም ባለቤትነት እረስቶት ወይም ሳያውቅ
ቀርቶ ሳይሆን፣ ሆን ብሎ ማጨቃጨቂያ ክፍተት ለመፍጠር ነው፡፡ አለበለዚያ ቀና አመለካከት ቢኖር?
ኢትዮጵያ የኦሮሞዎችም ናት ወይም ኦሮሚያ የኢትዮጵያውያን ናት ብሎ ሰፊ ሕዝብና ትልቅ ግዛታችን
ሆኖ ያለውን እውነታ በጠቀሰ፡፡ በሱ አቀራረብ እንዲመለስለት መስማት የፈለገው፣ “ኦሮሚያ የሚባል
ሀገር የለም” ተብሎ ተመልሶለት፣ በዛ የተለመደ ጉንጭ አልፋ ክርክርና እንዲጀመርና፣ ጆሃርም በዛ
“የኦሮሞ ሕዝብ ሆይ! ማንነትህን ካዱህ! ሀገርህ ያንተ አይደለም አሉህ!”...ወዘተ እያለ ኦሮሞው ከሌላው
ወገኑ ጋር ቆሞ፣ ባጠቃላይ ሀገራችን ላይ እየደረሰ ባለው፣ የፍትህ የዲሞክራሲና ኢ ሰባአዊ ድርጊት ላይ
ላይ እንዳያተኩርና የሱን ዕቅድ እንዳያደበዝዝ ነው፡፡
ለኦሮሞ ሕዝብ ኢትዮጵያ በሙሉ ሀገሩ ናት፣ ለአማራውም ለደቡቡም ....ወዘተ፡፡ ከዚህ የተለየ አቅዋም
“ይቺ ያንተ ናት፣ ያቺ የሌላ ናት” አካሄድ በግልጽ የሚያሳየው ሌላ ያልተደበቀ የኦሮሞን ሕዝብ ከሌሎች
ወገኖቹ ጋር የሚያራርቅ ስልት ነው፡፡ በተለይም ጆሃር በድፍረት፣ “ለኦሮሞ ኬንያም ኢትዮጵያም አንድ
ናቸው” ብሎ ሊያስቀምጥ የሞከረው ሌላ ተጨማሪ ትንኮሳ እየቀጠለ...፡፡
ጆሃርን ከጥቂት ዓመታት በፊት መጀመርያ የማውቀው የነበረው ላጠቃላይ ኢትዮጵያኖች በብሔራዊ
አጀንዳ ዙርያ ይመለከተኛል ብሎ አብሮ “ተሰልፎ” ከዓለም ዓቀፍ የዜና ማሰራጫዎች እስከ ፌስ ቡክና
ፓልቶክ ድረስ የክብር እንግዳ እየሆነ፣ ኢትዮጵያኖች ምክር ሲጠይቁት፣ እየወከሉ በየአደባባዩ
ሲያስተዋውቁት ....ወዘተ ነበር፡፡ ባደባባይ ይነግረን የነበረው፣ ከኦሮሞ አባትና ከክርስቲያን አማራ እናት
እንደተወለደና፣ ሁሉም ወገኑ ለሱ እኩል ወገኖቹ እንደሆኑ ነበር፡፡ በመሃሉ ስንት ጊዜ አቅጣጫ
እንደቀያየረ በቂ መረጃ ባይኖረኝም፣ እስካሁን ድረስ ከማውቀው፣ በጆሃር ውስጥ ብዙ “ማንነቶች”
ተንጸባርቀዋል፡፡ እውነተኛው ጆሃር የቱ እንደሆነ ማወቅ ብቸገርም፣ አንድ ነገር በእርግጠኛነት
“ከሚያሳያቸው ማንነቶች” መረዳት የሚቻለው፣ ብዙ ለማይታወቁ አጀንዳዎቹ ጭምር ማስፈጸሚያ
አድርጎ የመረጠውና እንደ “ጆከር” አሁን የሚጫወትበት “የኦሮሞ ብሔረተኝነትን” ነው፡፡
ከጽሁፉ እንደተረዳሁት፣ ኦሮሞ በሙሉ አንድ አይነት አቅዋም እንዳለው አድርጎ ሲገልጽ፣ “አክራሪ
ኦሮሞ፣ ለዘብተኛ ኦሮሞ ...ወዘተ” እየተባለ የሚሰጠውን አስተያየት “የኦሮሞን ሕዝብ ለመከፋፈል
የሚጠቀሙበት፣ ጊዜ ያለፈበት ....ወዘተ” ብሎ ነው፡፡
ይህ አይነት አቀራረብ የኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ አንድ ወጥ የሆነ አመለካከት ብቻ ነው ያለው ወደሚለው
አደገኛ አቅጣጫ ይወስደዋል፡፡ አንድ ማኅበረሰብ የፋብሪካ ውጤት አይደለም፡፡ በውስጡ ሁሉም አይነት
አቅዋሞች ሊንጸባረቁ እንደሚችሉ ማመን አቶ ጆሃርን ለሚያክል የፖለቲካ ሳይንቲስት ይጠፋዋል ብዬ
አላምንም፡፡ ነገር ግን ምናልባት እንዲፈጸም የሚመኘው በውስጡ ተጽዕኖ እያሳደረበት መሬት ላይ
ያለውን ሃቅ አደብዝዞበት ይሆን? ብዬ ከመጠየቅ አላልፍም፡፡
የኦሮሞም ሕዝብ እንደ አንድ ማኅበረ ሰብ በውስጣቸው ተፈጥሮያዊ የሆነ ጤናማ ልዩነት ይንጸባረቃል፡
፡ በታሪክም ሆነ በዕድሜዬ እንደተረዳሁት፣ የኦሮሞ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ፣ ከሌሎች ወገኖቹ
ጋር ሆኖ ለሀገር ዳር ድንበር የተዋደቀ፣ ለአንድነታችን ዋጋ የከፈለ፣ ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር ተዋህዶና
ተቀላቅሎ እየኖረ ያለ፣ ብዙ ስመ ጥር ሀገራቸውን የሚወዱ አርበኞች የወጡበት፣ ለሀገር ግንባታውም
ከፍተኛ አስተዋጾ ያደረገ ማኅበረሰብ ነው፡፡ የራሱንም ሆነ የሌላውን ባህል ቋንቋና እምነት የሚያከብር
ሀገሩንና ሥራ የሚወድ ሕዝብ ነው፡፡
በአንጻሩም በውስጡም፣ የባህል፣ የዕምነት፣ የአኗኗር ልዩነት እንዳለ ሳይረሳ፣ የጨቁኑት፣ ይሸጡትና
ያስማሙት፣ ከጠላት ጋር ተሰልፈው የወጉት፣ ለጥቅም፣ ለሥልጣን ብለው የካዱት፣ በስሙ የሚነግዱ፣
የሚሸጡ የሚለውጡ ኦሮሞዎች ሁሉ የነበሩበትና ያለበት ትልቅ ማኅበረ ሰብ ነው፡፡
ሌላው የጆሃር አገላለጽ “በሕዝባዊ ንቅናቄ ውስጥ በቀጥታ በመሳተፍ ጉዳት የደረሰባቸውን ከልብ
እንደግፋለን እያሉ ከንፈር በመምጠጥ በሌላ በኩል ደግሞ ታጋዮች አንግበው የተነሱትን መፈክር
በመኮነን፣ ድጋፉም ሆነ ከፈር መጠጣው የውሸት እንደሆነ ያሳያል” ይለናል፡፡
ይሄ ጆሃርን አልተመቸኝም የሚለው አካሄድ፣ በግሌ የፖለቲካ ባሕላችን፣ “ከጥቁርና ነጭ የፖለቲካ
አካሄድ” መቀየር መጀመሩ እንደሆነ የሚያሳይ ምልክት ስለሆነ፣ እንዲያውም ደስ ሊያሰኘን ነው
የሚገባው፡፡
ታጋዮች በማይደግፉት የፖለቲካ አቅዋም ውስጥ ጭምር ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትን ተቃወሙ ማለት፣
በምንጠላው ነገር ውስጥ በጎ ነገርን ማየት መቻል ስለሆነ፣ በበጎ ጎኑ ሊታይና እንዲያውም ሊበረታታ
የሚገባ አዲስ የፖለቲካ ጅምር ነው፡፡
በሰሞኑ የኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በስፋት በመንቀሳቀስ እየጠየቁ ያለውን የመብትና የፖለቲካ
ጥያቄ፣ ከኦነግና መሰል “ነጻ አውጭ” ድርጅቶች የሥራ ውጤት እንደሆነ ተደርጎ የሚቀርብ የታሪክ ሽሚያ
ታይቷል፡፡ በመሠረቱ ኢትዮጵያዊ የኦሮሞ ወጣቶቹ እንዳደረጉት፣ መብት ካለ አግባብ ሲነጠቅ
መከላከልም ሆነ መቃወም ትክክልም ተገቢም ነው፡፡ ነገር ግን “የነጻ አውጭ ድርጅቶች”፣ ሁኔታውን
ተጠቅመው ሕዝብን ከፋፍሎ ወደ እርስ በእርስ ግጭት ሊወስድ ወደሚችል፣ ለጠባብ የፖለቲካ ዓላማ
ሊጠቀሙበት ሲሞክሩና ሁኔታው ተመቻቸልን ብለው በወጣቶቹ ትከሻ ፕሮፓጋንዳውን ሲያጦዙት፣
ሀገራችን እንዳትበታተን የምንፈልግ ሰዎች ፈርተንና ቆም ብለን አስበን፣ ጉዳዩን ለጠባብ የፖለቲካ ፍጆታ
ብቻ መጠቀሚያ ከማድረግ፣ ወደ ብሔራዊ ትግሉ ከፍ አድርጎ ለሁሉም ሊጠቅም በሚችል መልኩ፣
እንቅስቃሴውን አስፍቶ የጋራ ለማደርግ መሞከርና፣ ሲቃወሙ ለተጎዱት ወጣቶች ወገናዊነትን ማሳየት
ትክክለኛ አቅዋም ነው፡፡
ትክክል የማይሆነው አንዳንዶች እንዳደረጉት፣ የጥያቄውን ይዘት ብቻ በመመዘን፣ ከነገሰባቸው የውስጥ
ፍርሃት ወይም ጥላቻ ተነስተው ከኋላው የፖለቲካዊ ትርጉም ብቻ በማንጠልጠል፣ “ይበለው፣ የተሳሳተ
ጥያቄ ስለጠየቀ” ብለው፣ ወተት እንደሰረቀች ድመት በወጣቶቹ ላይ የተፈጸመውንም በደል አላየንምና
አልሰማንም ብለው ሲያደፍጡ ነው፡፡
የዘር ግድብ ሳይገድባቸው፣ የፖለቲካ ልዩነት ሳይከፋፍላቸው፣ ሥርዓቱ በመላ ሀገሪቱ ውስጥ እያደረሰ
ያለውን ችግር እኩል ሊያሳይ የምችል ሚዛናዊ የሆነ መፈክር አዘጋጅተው አሉ የሚባሉትን ችግሮች በጋራ
ሲያሰሙ መውጣታቸው ያስመሰግናቸዋል እንጂ፣ የጆሃርን የፖለቲካ አቅዋም ብቻ ሙሉ ለሙሉ
ስላላንጸባረቁ ሊወቀሱ ባልተገባ፡፡
ምናልባት ወጣቶቹ እንደጀመሩት፣ ትግሉን አፍኖ አቅጣጫ በማስቀየር፣ የፖለትካ ሞሳ ሰርቶ የሻንፒዮን
ዋንጫ ለብቻ ለመውሰድ ከመሞከር ይልቅ፣ አጋጣሚውን በመጠቀም ተቻችሎ አብሮ መቆም የጀመረውን
በማበረታታት፣ ጽንፍ የቆሙትን ወደመሃል ባማምጣት፣ ከፓርቲና ከተወሰነ ቡድን ጥቅም ፍላጎት ከፍ
አድርጎ ወደ ሀገራዊ የረዥም ጊዜ ጥቅም፣ ትኩረት ቢሰጥ እንደ ጥሩ ጅምር ሆኖ፣ ብዙ ውጪ የቆሙትንም
እንደሚስብ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
በመጨረሻ ሳልጠቅስ የማላልፈው፣ ከአቶ ጆሃርና ተመሳሳይ አቅዋም ካላቸው በተደጋጋሚ ያስደመጡንም
ሆነ የአስነበቡን፣ “የኦሮሞ ወጣቶችን ለመብታቸው እንዲቆሙና እንዲታገሉ በረዥሙ ሰርተው የገነቡት
ጥረት እንደሆነ ነው”፡፡ እኔ የማየው በሌላ መንገድ ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች በዜና ማሳራጫ አውታሮች
እንዳየናቸው፣ ዕድሜያቸው ቢበዛ ከ15 እስከ 25 ዓመት ቢደርሱ ነው፡፡ አብዛኞቹ ወያኔ ስልጣን ከያዘ
ቦኋላ የተወለዱ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ቋንቋንና ዘርን...ወዘተ መሠረት ባደረገ “የፌዴራል”ሥርዓት ውስጥ፣
ከክልል እስከ ቀበሌ፣ በጎሳ ድርጅት ሃላፊዎችና ካድሬዎች፣ ስለ ክልላቸውና የወጡበት ማኅበረሰብ ብቻ
እንዲያስቡ፣ በሬዲዮን፣ በቴሌቪዥን፣ በዕድር፣ በዕቁብ፣ በየስብሰባው፣ የኦሮሞ ክልል፣ የአማራ ክልል፣
የደቡብ ክልል...ወዘተ እየተባሉ ያደጉ ናቸው፡፡
እንደ እኛ በአንድነት ውስጥ የነበሩትን በጎ ነገሮች ለማየትም ሆነ ለመስማት አልታደሉም፡፡ ከፓርላማ
እስከ ቀበሌ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ወጪ እየወጣ የአንድ ጎንዮሽ የሆነውንና ያልሆነውን፣ አሉታዊ
የተጋነኑና የተፈበረኩ ታሪኮች ሲጠቀጠቅ ለኖረው ምስኪን ወጣት፣ አቶ ጆሃር የተወሰነ ውጤት ቢያዩ
“እኛ ሰራነው” ብለው ሊኩራሩ አይገባም፡፡
የአንድነቱ ደጋፊ ይህንን አይነት ዕድል ቢያገኝ፣ ሃያ አምስት ዓመት አይደለም በግማሽ ዓመት ውስጥ ምን
አይነት ሥራ ሊሠራ እንደሚችል ቢታይ፣ እነ አቶ ጆሃርን ሥራ ፈት አድርጎ ያስቀምጣቸው ነበር፡፡ ስለዚህ
ይህንን አብሮ የኖረ ሕዝብ ለራሳችሁ ፍላጎት ብላችሁ ለመለያየት አትሞክሩ፡፡ ሕዝብ እንደሆን
ተዋህዷል፣ ንጹህ የሚባል ዘር ያለው በሁሉም ማኅበረ ሰባችን ውስጥ ባሉ ዘረኞች ጭንቅላት ውስጥ
እንጂ ያልተቀላቀለ የለም፡፡ በሁሉም ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ጎጠኛ ልሂቆች ወደ ሕዝብ የሚገፉት እንጂ
በሕዝብ ማሃል ችግር የለም፡፡ ደሞም ዘር አንመርጥም፣ በኢዮጵያዊነታችን ኦሮሞም፣ ጉራጌም፣ አማራም
....ወዘተ ሁሉንም ነን ማለት መብት ነው፡፡
ኦሮሞን ጨምሮ የሁሉም ወገናችን ችግር ይመለከተናል ብለው ጸንተው የቆሙ ሚሊዮኖች እንዳሉ
አትዘንጉ፡፡ ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ከዘር ፖለቲካ ጫጫታው ስለራቁና እንደ ጎጠኞች ጮክ ብለው
ጆሮዋችንን ስላላደነቆሩት፣ የዘር ፖለቲካ ስለሚደግፉ ነው ብሎ ለማመን መሞከር እራስን ማታለል ነው፡
፡ ከሰማንያ የሚበልጡ ብሔረሰቦች ባሉበት ሃገራችን ውስጥ፣ ሁላችንም ለየራሳችን የምንፈልገው አይነት
ዕቅድ እያወጣን ሁሉም ይቀበለው ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡
ስለዚህ ለሕዝባችን የሚበጀው ልዩነት ሳይሆን አንድነት ነው፡፡ በዘር በኃይማኖትና በፖለቲካ አቅዋም
ተከፋፍሎ የቆመውን ምሁር፣ ሁሉም የራሱን አጀንዳ ብቻ ቢገፋ፣ ሁሉም ተሸናፊ እንደሚሆን አምነን፣
በእውነት ስለ ሀገርና ሕዝብ ከሆነ ትግሉ፣ ትክክለኛ መንገዱን የሀገራችን ልሂቃን ይጠፋቸዋል ብዬ
ለመምከር አልሞክርም፡፡
ኢትዮጵያ የኦሮሞዎች፣ ኦሮሞም የኢትዮጵያውያኖች ናት፡፡
ሀገራችንን ከአውቆ አጥፊ ይጠብቅልን፡፡
ብስራት ኢብሳ
tebaber@gmail.com
የሁሉም ጠላት ወያኔ ነው!
ከአንተነህ መርዕድ ፌብሩዋሪ 17 ቀን 2016
ወያኔ የኦሮሞ ጠላት ነው
መለስ ሲያጉረመርምበት ብርክ የሚይዘውና የሚሙለጨለጨው፣ ጓደኞቹን ደጋግሞ በፍርሃቱ የሸጠው አባይ ፀሃዬ ዞር ዞር ብሎ ሲመለከት
ከሱ የተሻሉና የሚያስፈሩት ህወሃቶች የሌሉ መሆናቸውን በማረጋገጡ በየመድረኩ ብቅ እያለ መፎከርና መዘባረቅ የእለት ተእለት ሥራው ሆኗል።
በተለይም በዋና ባለቤትነት የአዲስ አበባን መሬት ሸጦ ከጨረሰ በኋላ የአካባቢውን ገበሬዎች ከነመሬታቸው ሊቀራመት ያደባበት ተንኮል አልሠራ
ሲል “ልክ እናስገባቸዋለን”ሲል ፎከረ። አሁን ደግሞ ፉከራው የለኮሰውን እሳት ማዳፈን ተስኖት “ወያኔ የኦሮሞ ጠላት አይደለም” የሚል የሽሽት
ሽምጥ ሩጫ ይዟል። እሳቱ ግን እሱን ሳይለበልበው የሚመለስ አይደለም።
ወያኔ ወደ ምኒልክ ቤተመንግሥት ሲገሰግስ ኦነግን ከተኛበት ቀስቅሶ ያመጣው ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም ብሎ ሳይሆን በኦነግ እጅ ኦሮሞውንና
ሌሎችንም ለመሸንቆጥ ወይም ልክ አስገብቶ ለመግዛት መሆኑን ለማወቅ ቀናት አልወሰደም። ወያኔዎች እንኳን ለኦሮሞው፣ ቆመንለታል ላሉት
የትግራይ ህዝም ቢሆን ገና ከመጀመርያው ጠላቱ እንደሆኑ ድርጊታቸው መስክሯል። ህወሃት ጠፍጥፎ የሠራውን ኦህዴድን ማንም ስለማያውቅና
ስለማይቀበለው ኦነግን ለመሸጋገርያነት ማዘጋጀታቸውን የማያውቁት የጊዜው የኦነግ አመራሮች ብቻ ነበሩ። ኦነግ ሳይሆን በስሩ የተሰባሰበው ህዝብ
የወያኔን ተንኮል ቀድሞ በመረዳቱ አልገዛም ሲላቸው ወያኔዎች ሰይፋቸውን የመዘዙት በጓደኞቻቸው የኦነግ አመራሮች ሳይሆን በኦሮሞ ህዝብ ላይ
ነው። አመራሮቹን ቀስ አድርገው ከአገር ከመሸኘታቸው በፊት “ሰራዊታችሁን ካምፕ ውስጥ አስገቡልን” አሏቸው። በአሜሪካና በሻዕብያ ዋስትና
ሰጭነት ሰራዊቱን ከህዝቡ መሃል አስወጥተው ካምፕ አስገቡላቸው። የሚገርመው የተመረጡት ካምፖች ከወያኔ ሰራዊት በቅርብ እርቀት ላይ
ተወስነው በቀላሉ የሚደርስባቸው እንዲሆኑ የተመቻቹ መሆናቸው ነው። በጊዜው ኦነግን ወክሎ ምርጫ ለማስፈፀም ደሴ ተመድቦ ከነበረው የኦነግ
አመራር አባል ከሆነው ነገሪ ፈይሳ ጋር ለመገናኘትና ለመግባባት እድል አግኝቼ ነበርና ካምፕ ማስገባቱም ሆነ የተመረጡት ቦታዎችን አደገኝነት፣
ሻዕብያና አሜሪካ ከኦነግ ይልቅ ወያኔን የኋላ ኋላ እንደሚደግፉ ሃስቤን ስሰነዝርለት የሁኔታውን አሳሳቢነት የተረዳ አልነበረም። ጉዳዩ እንግዳ
ቢሆንበትም ኋላ ላይ በከፋ ሁኔታም ቢሆን ሳይማር አይቀርም። የሆነውም ይሄው ነው። ወዳጄ ነገሪ ፈይሳና እነ ሌንጮም ሰራዊቱን አስረው
አስረክበው እነሱ በቦሌ የመውጣት የቪዛ ሽልማት አገኙ። የገረመኝና እስከ አጥንቴ የሰበቀኝ ነገር፤ ያለምንም ፋታ ኦሮሞዎችን በመጨፍጨፍና
በማሰቃዬት የተካነውን መለስ ዜናዊን እስትንፋሱ በሞት እስክታቆም ድረስ ሲገናኙት መኖራቸውን ሌንጮ ለታ ሲናገሩ የሰማሁ እለት ነው። በምን
ተስፋ? በምን ውለታ? አቶ ሌንጮ!
በወቅቱ የወያኔን ሰራዊት የሚመራው የመከላከያ ሚኒስትሩ ስዬ አብርሃ በካምፑ ውስጥ ያሉትን በመክበብ የሚገድለውን ገድሎ
የተረፈውን እስር ቤት ውስጥ ሞላቸው። እስር ቤቶች ኦሮምኛ መናገር የጀመሩት ስዬ ከጓደኞቹ ተጣልቶ እስር ቤት በገባበት ወርቅት ሳይሆን እሱና
ጓደኞቹ የኦሮሞን ልጆች እንደ አውሬ እያደኑ በገደሉና ባሰሩ ጊዜ ነበር። “የአይጥ ምስክሯ ዲንቢጥ” እንዲሉ “እስር ቤቶች ኦሮምኛ ይናገራሉ አለ
ስዬ” እየተባለ ሲጠቀስ ይገርመኛል። እውነቱ እውነት ቢሆንም የድርጊቱ ፈፃሚዎችን ምስክርነት ግን የሚጠይቅ አይደለም። ወያኔ ገና ጫካ እያለ
ያቀደውን ነው ተግባራዊ ያደረገው። ስዬ፣ ገብሩ፣ አዳነች ወዘተ እጃቸውን እንደጲላጦስ እየታጠቡ ከደሙ ንጹህ ለመሆናቸው ብዙ ሊሉን ይችላሉ።
በድርጊታቸው እንጂ በአፋቸው የማይነግሩን እውነት ቢኖር ኢትዮጵያንና ህዝቧን የሚጠሉ መሆናቸውን ነው። በአባይ ፀሃዬና አሁን ባሉትም ሆነ
በተገለሉት የህወሃት መስራቾች መካከል ምንም ልዩነት የለም ። ቢኖርማ አሁን በኦሮሞ፣ በጋምቤላው፣ በአማራው፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን
ላይ የሚሠራውን ግፍ ዝም ብለው አይመለከቱም ነበር። የትግራይ ህዝብ ተነካ ብለው አይደለም እንዴ መሳርያ ይዘው ጫካ የገቡት። ዛሬ ምነው
አደባባይ ወጥተው አገር ልትፈራርስ ስትል ያልጮሁ?
ወያኔ የኦሮሞ ጠላት አለመሆኑን ከዚህ በታች ያለውን ሰንጠረዥ ተመልከቱና ፍረዱ። እስር ቤቶች በኦሮሞ የተሞሉ ብቻ ሳይሆኑ የግፉ
ሁሉ መጨረሻ ዝግናኝ ኢሰብአዊ ድርጊት ሁሉ የሚፈጸምባቸው ቦታዎች ናቸው። ዝርዝሩን ለኦሮሞዎች የሚቆረቆር አካል ለቅሞ ያወጣው ቢሆንም
እውነቱን አጉልቶ ያሳያልና በጥሞና ተመልከቱት። ከአምስት መቶ በላይ የሆኑ እስረኞችን ዝርዝር የያዘ ቢሆንም ሞትና የእድሜ ልክ እስራት
የተፈረደባቸውን ሰማንያ ሰዎች ብቻ መርጨ ነው ያቀረብሁት። ከዚህ ዝርዝር በተጨማሪ ከየመን ተጠልፎ እስር ላይ የሚገኘውንና የሞት ፍርድ
የተፈረደበትን አንዳርጋቸው ጽጌን አትርሱ። በዚህም አያበቃም፤ ባይታሰሩም ብርሃኑ ነጋ፣ አበበ ገላው …..እያላችሁ በወያኔ እጅ ባይኖሩም
እድሜልክና ሞት የተፈረደባቸውን ኢትዮጵያውያን በህሊናችሁ እያሰባችሁ ዝርዝሩን ማስፋት ትችላላችሁ። እነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያውያን የትኛው
ወንጀላቸው ነው ሞትና እድሜልክ የሚያስፈርድባቸው? ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን የገደሉና እየገደሉ
ያሉ ህወሃቶች ምን ሊፈረድባቸው ነው? ነፃውን ፍርድቤትም በህሊናችሁ ነፃነቱን ቃኙት።
እውነቱን ባይቀይረውም በዝርዝሩ ላይ ስህተት ካለ እታረማለሁ።
ተ.ቁ የእስረኛው ስም ፆታ ብሄር የተወነጀለበት ጉዳይ ፍርድ እስር ቤት
1 አበረ አሰፋ አበራ ወንድ አማራ ሽብር ሞት ቃልቲ
2 አህመድ እስማኤል ሙዳሙመድ ወንድ ኦሮሞ ሽብርና ለጦርነት ማነሳሳት ሞት ቃልቲ
3 በያን አህመድ እስማኤል ወንድ ኦሮሞ ሽብርና ለጦርነት ማነሳሳት ሞት ቃልቲ
4 ዲሪቢ ኢታናገመቹ ሴት ኦሮሞ ሉአላዊነትን በመፃረር ሞት ቃልቲ
5 ኢብራሂም ሃሰን ናሊያ ወንድ ኦሮሞ ሽብር ሞት ቃልቲ
6 ጀማል ሙስጠፋ አደም ወንድ ኦሮሞ ሽብርና ለጦርነት ማነሳሳት ሞት ቃልቲ
7 ጁሙአ ሩፋኤል አሚን ወንድ ኦሮሞ ሉአላዊነትን በመፃረር ሞት ቃልቲ
8 ከዲር ሻኩር ሙሴ ወንድ ኦሮሞ ሽብር ሞት ቃልቲ 9 ሊቨን ዋሪዮ ጉዮ ወንድ ኦሮሞ ሽብር ሞት ቃልቲ
10 መላኩ ተፈራ ጥላሁን ወንድ
ኦማራ ሽብር ሞት ቃልቲ
11 መስፍን አበበ አብዲሳ ወንድ ኦሮሞ ሽብር ሞት ቃልቲ
12 ሙሃመድ አህመድ አብዱላሂ ወንድ ሶማሌ ሽብር ሞት ቃልቲ
13 ሙሃመድ ሃሰን ሙሃመድ ወንድ ሶማሌ ሽብር ሞት ቃልቲ
14 ታደሰ ሃይሌ መኮነን ወንድ አማራ ሽብር ሞት ቃልቲ
15 ኡርጂ አበበ ቃበታ ሴት ኦሮሞ ሉአላዊነትን በመፃረር ሞት ቃልቲ
16 አብዱልራሺድ አብዱላሂም ወንድ ኦሮሞ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
17 አብዱራህማን ሙሳ ኢቶሳ ወንድ ኦሮሞ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
18 አብዱራህማን ኢሳ ሚቴሶ ወንድ ኦሮሞ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
19 አብዱራሺድ ባሺር ሁሴን ወንድ ኦሮሞ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
20 አበ
ረ አሰፋ አበራ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
21 አለሙ ጌትነት አባተ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
22 አሊዩ ሙሚ ቦኮ ወንድ ኦሮሞ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
23 አማኑኤል ገመቹ ዱሬሳ ወንድ ኦሮሞ ሉአላዊነትን በመፃረር እድሜ ልክ ቃልቲ
24 አመራር ባይካል ካሳ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
25 አንዱዓለም አራጌ ወንድ አማራ ህገመንግሥትን በሃይል መናድ እድሜ ልክ ቃልቲ
26 አሳምነው ፅጌ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
27 ባካሪ ሙሃመድ አባሴና ወንድ ኦሮሞ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
28 ባሺር አህመድ መክታል ወንድ ኦሮሞ ለጦርነት መቀስቀስ እድሜ ልክ ቃልቲ
30 በላይ አበራ ጃቤና ወንድ ኦሮሞ ሉአላዊነትን መፃረር እድሜ ልክ ቃልቲ
31 ቦጋለ ጎንፋ ዋይሳ ወንድ ኦሮሞ ሉአላዊነትን መፃረር እድሜ ልክ ቃልቲ
32 ቸርነት የማነ ታደለ ወንድ አማራ ሽብር
ና ጦርነት መቀስቀስ እድሜ ልክ ቃልቲ
33 ዳኔል አያሌው ጮርቃ ወንድ አማራ ሽብር
ና ጦርነት መቀስቀስ እድሜ ልክ ቃልቲ
34 ደምሰው አንተነህ ደመላሽ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
35 ደርጉ ኢቴና ገመቹ ወንድ ኦሮሞ ሉአላዊነትን በመፃረር እድሜ ልክ ቃልቲ
36 ዱላ ኦቲ ኦልጂራ ወንድ ኦሮሞ ህገመንግሥትን በሃይል መናድ እድሜ ልክ ቃልቲ
37 እማዋዪሽ ዓለሙ ወልደሚካኤል ሴት አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
38 ፋይራ ኪቲላ ሳንካሌ ወንድ ኦሮሞ ሉአላዊነትን በመፃረር እድሜ ልክ ቃልቲ
39 ፋንታሁን ሙሃባ ሙፍቲ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
40 ጌታቸው ብርሌ ደሴ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
41 ገቱ ወርቁ ናደው ወንድ ጉራጌ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
42 ግርማ ረጋሳ ወይሳ ወንድ ኦሮሞ ሉአላዊነትን በመፃረር እድሜ ልክ ቃልቲ
43 ጎበና በላይ አየለ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
44 ጎዳና ዳዩ ወንድ ኦሮሞ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
45 ጎሽራድ ጸጋው አጋፋሪ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
46 ሃሊማ አብዲ ሞሃመድ ሴት ኦሮሞ ሉአላዊነትን በመፃረር እድሜ ልክ ቃልቲ
47 ሃሰን ሞሃመድ ሃሰን ወንድ ኦሮሞ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
48 ሁሴን ኡስማን ሳፋ ወንድ ኦሮሞ ሉአላዊነትን በመፃረር እድሜ ልክ ቃልቲ
49 ጃታኒ ኩኖ ቱንዳ ወንድ ኦሮሞ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
50
ካዲር ዝናቡ አባቡልጉ ወንድ ኦሮሞ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
51 ከበደ ግርማ ሁንዴ ወንድ ስልጤ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
52 ከፍያለው አብዲሳ ዱፈራ ወንድ ኦሮሞ ሉአላዊነትን በመፃረር እድሜ ልክ ቃልቲ
53 ክፍሌ ስንሻው ታደገ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
54 ከፍያለው ተፈራ ደረሶ ወንድ ኦሮሞ ህገ መንግሥትን በሃል መናድ እድሜ ልክ ቃልቲ
55 ሊባን ዋሪዮ ጉዩ ወንድ ኦሮሞ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
56 መኮነን ወርቁ ዓለሙ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
57 መንግስቱ አበበ አረጋዊ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
58 መንግስቱ ሆርዶፋ ሙለታ ወንድ ኦሮሞ ሽብር
ና ጦርነት መቀስቀስ እድሜ ልክ ቃልቲ
59 መስፍን ኢታና ፉፋ ወንድ ኦሮሞ ሽብር
ና ጦርነት መቀስቀስ እድሜ ልክ ቃልቲ
60 ምስጋናው ተሰማ ተገኘ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
61 ምስክር ካሳ ወንድም ወንድ አማ
ራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
62 ምትኩ ተስፋ ፋፋ ወንድ አማራ ሽብር
ና ጦርነት መቀስቀስ እድሜ ልክ ቃልቲ
63 ሞሃመድ ዳዲ ጃራ ወንድ ኦሮሞ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
64 ሞሃመድ ሁሴን ሞሃመድ ወንድ ኦሮሞ ሽብር
ና ጦርነት መቀስቀስ እድሜ ልክ ቃልቲ
65 ሙሳ ኡማር ዋዲያ ወንድ ኦሮሞ ሉአላዊነትን መፃረር እድሜ ልክ ቃልቲ
66 ሰይድ ሃሳን በሺር ወንድ ኦሮሞ ሉአላዊነትን መፃረር እድሜ ልክ ቃልቲ
67 ሰለሞን አሻግሬ አምበርብር ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
68 ጣሂር ሞሃመድ ኡስማን ወንድ ኦሮሞ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
69 ተማም ኢድሪስ አንቾ ወንድ ኦሮሞ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
70 ተመስገን ባይለየኝ ጸጋው ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
71 ተፈራ ማሞ ጨርቆስ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
72 ተሻለ ሺፈራው ረጋሳ ወንድ ኦሮሞ ሉአላዊነትን በመፃረር እድሜ ልክ ቃልቲ 73 ፅጌ ሃብተማርያም ጮማሳ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
74 ዋለልኝ ሃጢሶ ወንድ ሲዳማ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
75 ውድነህ ተመስገን ዓለሙ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
76 ያሲን አዱኛ ዳባ ወንድ ኦሮሞ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
77 የሺዋስ መንገሻ በየነ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
78 የሺዋስ ምትኩ ቸኮል ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
79 ይበልጣል ብርሃኑ ታፈረ ወንድ አማራ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
80 ዘይኑ አብዶ ተማም ወንድ ኦሮሞ ሽብር እድሜ ልክ ቃልቲ
ከላይ የተዘረዘሩትን እስረኞች አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሶማሌ ጉራጌ እያሉ ማስቀመጡ ተገቢ ባይሆንም ወያኔ በዘር ላይ አነጣጥሮ እንደሚዘምት
ማሳያ ይሆናልና አስፍላጊ ሆነ። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ እስረኞችና በአጥቃላይ አገሪቱ ውስጥ የሚሰቃዩት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ቋንቋቸው፣ ሃይማኖታቸው፣ ፆታቸው፣ ሙያቸው የማንነታቸው መገለጫ አካል ቢሆንም ኢትዮጵያዊነታቸውን በልጦ የማንነት መታወቂያቸው
ሊሆን አይችልም።
ወያኔዎቹ የህዝብ ጠላትነታቸው የሚታየው በማሰርና በመግደል ብቻ ሳይሆን በዘረፋም ነውና በዚህ መስክ ምን ያህል እንደተሰማሩ ትንሽ
ማየት ያስፈልጋል።
የሃብት ዘረፋን በተመለከተ በተደጋጋሚ በብዙ ጸሃፊዎች፣ አክቲኢስቶችና ፖለቲከኞች ብዙ የተባለ በመሆኑ የዛሬ አጀንዳዬ አይደለም። መላ
አገሪቷን የሚዘርፈው ወያኔ መሆኑን አዲስ አበባ ጥሩ ማሳያ ናት። ለኤርምያስ ለገሰ ምስጋና ይግባውና የምናውቀውን ተጨባጭ እውነት በአሃዝና
በመረጃ እያስደገፈ በማቅረቡ የኢህአዴግን የፕሮፓጋንዳ ልሳን ሳይቀር እንዳይተነፍስ አድርጎታል። ወያኔዎች ከ1997 ዓ ም ምርጫ በኋላ በአዋጅ
የአዲስ አበባን መሬት የቸበቸቡት በሃይለስላሴ፣ በግርማፅዮን በርሄ፣ በሃይሌ ፍስሃና በነጋ በርሄ መሪነት ቢሆንም ከዚያ በፊት ገና እንደገቡ ጀምሮ
የመሬት ዘረፋው ላይ ያልተሰማራ ትልልቅ ባለስልጣን የለም። ሙት ወቃሽ አያርገኝና ጄኔራል ሃየሎም አርአያ በጓደኞቹ በተቀናበረ ተንኮል
ቢገደልም፣ ከገዳዩ ጀሚል ያሲን ጋር በመሬት ጉዳይ ጠብ እንደነበራቸው በጊዜው በሚድያ ላይ የምንሠራ ሰዎች የምናውቀው እውነት ነው።
ሃየሎምና የህወሃት መሪዎች የአዲስ አበባን መሬት መቸብቸብ የጀመሩት ገና በማለዳው ነው። ስለሆነም አባይ ፀሃዬ ቢንፈራግጥ አይገርመንም።
አቶ ሮባ መሃመድ “እነሱ ከተማቸው ላይ ኢንዱስትሪ እየገነቡ ለእኛ የተቆረጠ ጡት የያዘ ሃውልት ይገነቡልናል” ያሉትን መራራ እውነት ወያኔዎች
በምንም መልኩ የሚያስተባብሉት አይደለም። ዛሬ ትናንት አይደለም። በትዕግስት ሲመለከታቸው የነበረ ህዝብ ዕድሉን በእጁ ብቻ እንደሚያገኝ
በማመኑ ለመታገል የፖለቲካ ድርጅቶችና የካድሬዎች መሪነት አላስፈለገውም። እስር ቤቶች ሞልተው መፍሰስ ጀምረዋል። ፌደራሎችና አጋዚዎች
የልብ ልብ ተሰምቷቸው ሰው የሚግድሉበትና የሚያሰቃዩበት ቀን ወደ ማብቃቱ ነው። ህዝቡ ይፈራ ነበር። አሁን የሚፈሩት የስርዓቱ አቀንቃኞችና
ደጋፊዎቻቸው ሆነዋል።
ወያኔ የትግራይ ህዝብም ጠላት ነው
የተወሰኑ የትግራይ ልጆች ተሰባስበው የመሰረቱት የህወሃት ዋና አላማ የትግራይን ህዝብ ከአማራ ብሄር ነፃ ማውጣትና የትግራይ
ሪፐብሊክን መመስረት እንደነበር ከራሳቸው ከህወሃቶች ጭምር ሲነገረን የኖረ ስለሆነ ሁሉም ያውቀዋል። ከሚናገሩትና ከሚጽፉት በላይ ግን
የህወሃቶችን ድርጊት ላለፉት አርባ ዓመታት የተከታተለ ዓላማቸውን አጥርቶ ማወቅ ይችላል። ይህ ለትግራይ ህዝብ ጥቅም ቆሜአለሁ የሚለው
ድርጅት እውነት ለትግራይ ህዝብ ቆሟል? ድርጊቱን እንመርምር።
ህወሃት ገና ጫካ ከመግባቱ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሃሳባቸውን የገለፁትንና ድርጅቱ ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ይዞ እንዲታገል የጠየቁትን
ጓደኞቻቸውን የትግራይ ልጆች በግፍ ገድለዋል። አባረዋልም። መሃሪ ዳዊት ከአዲግራት፣ እቁበእግዚዕ በየነ ከአክሱም፣ አስበሃ ዳኘው ከአድዋ፣
መንገሻ በላይ ከሽሬ፣ ሙሉጌታ አብርሃም ከእንደርታ፣ አልማዝ አስፋው ከመቀሌ፣ ኪዳኔ ግርማ ከመቀሌ፣ ተክሉ ሃዋዝ ከአድዋ ምን
እንደተፈጸመባቸው ህወሃቶች ደፍረው ይናገራሉ?
በ1977 ዓ ም በነበረው ድርቅ ለትግራይ ህዝብ የተላከን እርዳታ ዘጠና ከመቶውን መሳርያ መግዣና የአመራሮች የውጭ ባንክ አካውንት
ማበልፀያ በማድረግ በርካታ የትግራይ ገበሬዎች በርሃብ ተቀጥፈዋል።
አገራቸውን ከጠላት ተከላክለው ያዳኗትን የዮሃንስን፣ የአሉላንና የቀሪውን ጀግና የትግራይ ህዝብ ታሪክ ተፃርሮ የአገርን አንድነት አደጋ ላይ
ጥሏል። ዮሃንስ የሞቱለት ድንበር ሳይቀር ለሱዳኖች ለመስጠት በመስማማት ላይ ነው።
ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ጥቂት የትግራይ ልጆችን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ለይቶ በመጥቀም ምስኪኑ፣ ብዙሃኑና ድሃው የትግራይ ህዝብ
በሌሎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደልዩ ተጠቃሚና የስርዓቱ ደጋፊ ሆኖ በጥርጣሬ ዐይን እንዲታይ ሆን ብሎም እንዲቃቃር ሌት ተቀን እየሰራ
ነው።
ወፋፍራሞቹ የወያኔ ድመቶች የሃይል ሚዛኑ ዘንበል ካለ እንደመንግስቱ ኃይለማርያም የያዙትን ይዘው ለመፈርጠጥ ቋፍ ላይ ናቸው። ግን
የትም አያመልጡም። የፈሰሰው ደምና የተዘረፈው የአገር ሃብት የትየለሌ ስለሆነ በየሄዱበት ታንቀው ይጠየቁበታል። ወየው በስህተትም ይሁን
ለጥቅም ብለው ወያኔን ለሚደግፉ አድርባዮች! ታዝዘን ነው የሚለው ምክንያት የደርግ ባለስልጣናትን በእስር ከመበስበስ አላዳናቸውምና።
ወየው በስሙ ለተነገደበትና ከወንድሞቹ ኢትዮጵያውያን እንዲቆራረጥ እየተገፋ ላለው የትግራይ ህዝብ!! ሻዕብያና ወያኔ አቅል ባጡበት
ፍቅራቸውና ኋላም በጠባቸው ጊዜ በሰሩት ስህተት ምስኪኑ የኤርትራ ህዝብ ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ መለያየት ብቻ ሳይሆን እስከአሁን
ለአለበት ዳፋ እንደተዳረገው ወያኔዎች ለትግራይ ህዝብ ያዘጋጁት ይህንኑ ዕድል ነው።
ትዝብት ይሁን ድምፃቸውን ላጠፉት የትግራይ ምሁራን። አንድም የሚደርሳቸው የዘረፋ ጥፍጣፊ፣ አንድም አደባባይ ያላወጡት ዘረኝነት
ተፈታትኗቸው አንደበታቸው ተዘግቷል። ከገብረመድህን አርዓያ፣ ከአብርሃ ደስታና ከአስገደ ግብረስላሴ ውጭ ሌሎች የት ገቡ? ወያኔ ኢትዮጵያን
በተለይም የትግራይን ህዝብ ህልውና ሊያጠፋ ሉአላዊነቷና ዜጎቿ ላይ ሲነሳ፣ በህዝብ ደም እጁን ሲታጠብ የት ነበርን ሊሉ ነው? አፋቸውን
በእጃቸው ከድነው ሲስቁ እየታዩኮ ነው!
ወያኔ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ነው!
ኢትዮጵያን ያለህዝብ ፍላጎትና ውሳኔ ያለወደብ ያስቀረ፤
ከሰማንያ ሺህ በላይ ዜጎቿን በማይረባ ጦርነት ማግዶ ካስጨረሰም በኋላ ያለመፍትሄ ያስቀመጠ፤
ጋምቤላ፣ አሰቦት፣ አርባጉጉ፣ ወተር፣ ጎንደር አደባባይ ኢየሱስ፣ አሶሳ፣ አረካ ወላይታ፣ አዋሳ፣ አፋር፣ አዲስ አበባና አሁን ደግሞ በመላ
ኦሮምያና ጎንደር ኢትዮጵያውያንን የጨፈጨፈና ያስጨፈጨፈ፤
አባቶቻችን በመስዋዕትነት ዳር ድንበሯን ያስጠበቋትን አገር ለሱዳን ለመስጠት ያልሳሳ፤
ድሃ ገበሬን እያፈናቀለ ለህንድ፣ ለአረብ፣ ለቻይና መሬት በነጻ ያደለ፤
የአገሪቱን ሃብት ጠቅልሎ በወያኔ ካምፓኒ ኤፈርት ቁጥጥር ስር ያዋለ፤
የአገሪቱን ወጣት ሴቶችን ለአረብ፣ ወታደሮችን ለአሜሪካ ቅጥረኝነት፣ ህፃናትን ለምዕራቡ ገበያ አውጥቶ የቸበቸበ፤
አገሪቱን ፍትህ አልባ አድርጎ ዜጎችን ሙሉ በሙሉ ወደ እስረኝነት የለወጠ፤
ኢትዮጵያውያንን በዘር ከፋፍሎ ለህልውናችን በአንድነት እንዳንቆም አድርጎ ለአለንበት ውድቀት የዳረገን፤
ሚሊዮኖች ተርበው “የተራበ የለም” የሚልና ሲጋለጥ ደግሞ በርሃቡ ላይ እንዳይተኮር ጠንክሮ የሚሠራ ጨካኝና ዘረኛ ቡድን መሆኑን
ያልተሀነዘበ ኢትዮጵያዊ ካለ ጤነኛ አይደለም። የህወሃት ወፍራም ድመቶች አፋቸውም፣ እጃቸውም ደም በደም መሆኑን ኢትዮጵያዊ ብቻ
ሳይሆን ዓለም አይቷል። መደበቂያ የላቸውም።
ሌሎችን በማጥፋት ራሱን ያገዘፈው ወያኔ ከሁሉም አቅጣጫ በህዝቡ በሚሰነዘር ጥቃት በመድማት ላይ ያለ የቆሰለ አውሬ ሆኗል።
ደም አስክሮት እየተወራጨ ነው። መድማቱን የሚያቆምበት ፋታ አጥቷል። አለኝታ ያጣው ህዝብ በቃኝ ብሎ በመነሳት
የሚወረውራት እያንዳንዷጥቃት የወያኔን ሞት እያፋጠነችው ነው። ከተመልካችነትና ከአሽሟጣጭነት ወጥቶ የህዝቡን ትግል
መቀላቀል አሁን ነው። ወያኔ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጠላት ስለሆነ የመውደቁ ድል የጋራ እንዲሆን ትግሉም የጋራ ሊሆን
ይገባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ!
1
የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ
Ethiopian Border Affairs Committee
P. O. Box 9536 Columbus, Ohio 43209 USA E-mail: ethiopianborders@gmail.com
ሀሰቱም ያብቃ፤ ዳር-ድንበር መሸጡም ይቁም! ከኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሜቴ የተሰጠ መግለጫ
የካቲት 8 ቀን 2008 ዓ/ም ( February 16, 2016 )
ካለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ በአገራችን የተከሰተው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሰሞኑን
የተጀመረ ለማስመሰል እንደሚሞክረው ሳይሆን፤ ሕወሓት ካለፉት በርካታ ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየፈፀመ ያለው
ግፍና መከራ ድምር ውጤት ነው። ብሶቱም መጠነ ሰፊ፤ ጊዜውም ከ25 ዓመት በላይ ያስቆጠረ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው።
በተለያዩ ክፍለ አገራት ያሉ ወገኖቻችን ለዘመናት ይኖሩበት ከነበሩበት መንደሮች በልማት ስም በኃይል እየተፈናቀሉ የትም
እንዲወድቁ ሲደረጉ፤ አንድም ቀን ይህን የሕወሓትን ግፍና መከራ በፀጋ የተቀበሉበት ጊዜ አልነበረም።
ከአፍንጫው ራቅ አድርጎ ማሰብ የማይችል አምባገነን አገዛዝ አንድ ሕዝብ በቁጣ በተነሳ ቁጥር ማስታገሻው ወይም እንደነሱ አባባል
ማርከሻው ሕዝቡን በኃይል "ፀጥ" ማድረግ ነው። "ፀጥ" እናደርጋቸዋለን የሚሉ ወገኖች አንድ ቀን ራሳችው ፀጥ እንደሚሉ
ስለማይገነዘቡ የማይቀረውን የቁልቁለት መንገድ ይያያዙታል። ያኔ ኃይል የነሱ ሳይሆን የሕዝብ መሆኑን ሳይወዱ በግድ ይረዱታል።
በሰሞኑ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ከሕዝብ በተነሱ ዐበይት ጉዳዮች መካከል አንዱ ከሰሜን ኢትዮጵያ አንስቶ እስከ ጋምቤላ ድረስ ያለውን
ለም የድንበር መሬት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት የተጀመረው ሴራ እንዳይተገበር ሕዝቡ አጥብቆ የመጠየቁ ጉዳይ ነው።
ይህን የአገርን ድንበር አሳልፎ የመስጠት ሤራን ሕዝባዊ ተቃውሞ ከመጀመሩ አንድ ወር በፊት የወያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ
ኃይለማርያም ደሳለኝ ለወያኔ ፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ በእሳቸው አባባል "... እነዚህ ኃይሎች (ተቃዋሚዎችንና የኢትዮጵያ
ድንበር ጉዳይ ኮሚቴን ማለታቸው ነው) መንግሥት ለሱዳን መሬት ቆርሶ ሊሰጥ ነውና ሕዝብ ሆይ ተነስ ሲሉ ጥሪ ሲያቀርቡ
እንሰማለን" ነበር ያሉት።
አዎን እርግጥ ነው፤ አቶ ኃይለማርያም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተላለፈውን መልዕክት በትክክል ሰምተዋል። ሕዝቡም ጥሪውን ሰምቶና
ተቀብሎ ዕቅዱ ተግባራዊ እንዳይሆን በየአካባቢው እየተንቀሳቀሰ ነው ያለው። ጥሪውን ሰምቶ ጆሮ ዳባ ያለውና መልስ ያልሰጠው
ቢሰጥም የክህደት መልስ የሰጠው የእርስዎ አገዛዝ ሕወሓት ብቻ ነው። አሊያማ ክ70 በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣
የሲቪክ፣ የሙያና የሚዲያ ድርጅቶች የጋራ አቋም ይዘውበት፣ ሕዝቡም እስከዛሬ የተሸረሸረው አልበቃ ብሎ ሌላ የአገሪቱ ክፍል
(ድንበር) አይሸነሸንም እያለ ቁጣውን ከዳር እስክዳር እያሰማ ያለው በሕወሓት ሹሞች የሚሰጠውን ገደብ የለሽ ውሸት መቀበል
ስላቃተው ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኰሚቴ ድንበር የማካለሉ ተግባር "ካላንዳች ችግር" እየተካሔደ የመሆኑን ዜና
የሰማው ከኢትዮጵያ በኩል ሳይሆን ከሱዳን ጋዜጣ ሱዳን ትሪቡን (Sudan Tribune) እ.አ.አ. ጥር 17 ቀን 2016 ( January 17,
2016 ) ባወጣው እትሙ ነበር።
ጉዳዩ ለአገሪቱና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠቅማል ተብሎ ከታመነበት ድብብቆሹ ለምን አስፈለገ? ለምንስ የሱዳን መንግሥት ለራሱ
ሕዝብ ይፋ እንዳደረገው ሁሉ የወያኔ መንግሥት ለምን ለሕዝቡ በይፋ ሊያሳውቀው አልፈለገም?
ከፍ ሲል በጠቀስነው ንግግራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም የሐሰት መግለጫቸውን ሲያብራሩ "በመሬት ዙሪያ የተደረገ
ንግግርም የለም፣ ተቆርሶ የተሰጠ ነገርም የለም" ሲሉ ጭልጥ ያለ ከነጭም የነጣ ውሸት እንደተለመደው ተናግረዋል።
2
በጣም የሚያሳዝነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን በተናገሩበት አንደበት ወዲያውኑ አያይዘው "... ከኛ አካባቢ እየሔዱ በርካታ
ሱዳናዊያንን እየገደሉ የሚመለሱ ሽፍቶች አሉ" ሲሉ ለዘመናት በአካባቢው ነዋሪ የሆኑትንና፣ ትዳር ይዘው፣ ወልደው ተዋልደው
በሰላም አርሰው የሚኖሩትን ገበሬዎች "ሽፍቶች" ብለው ካለ አንዳች ሃፍረት ማዋረዳቸውና መወንጀላቸው ነው። በርሳቸው
አመለካከት በአካባቢው የሚኖረው ሕዝብ ‘’ነፍሰ ገዳይ ነው፣ ወንበዴ ነው፣ ሽፍታ ነው፣ አልፎ ተርፎም ወንጀለኛ ነው።”
ቀዳማዊው መለስ ሕይወታቸውን ሙሉ ለሱዳን ሕዝብና መንግሥት ጥብቅና እንደቆሙ፣ በአደባባይ እንደተከራከሩላቸው ለዝንተ
ዓለም አንቀላፉ። አሁን ደግሞ ዳግማዊ መለስ በሌለባቸው ውለታና የዘሬን ብተው ዓይነት ሆኖባቸው የራሳቸውን ሕዝብ
በአደባባይና በይፋ መወንጀል ስራዬ ብለው ተያይዘውታል።
ጥማድ በሬ አሰማርቶ፣ ክረምትና በጋን ጠብቆ፣ የሚያርስና መሐር የሚሰበስብ ገበሬ በምንም መለኪያ ቢመዘን "ሽፍታ" መሆን
ቀርቶ "ሽፍታ" ሊባል የሚገባው አይደለም። ይህ "ሽፍታ" ገበሬ ግብሩን የሚከፍለው እኰ ለሱዳን መንግሥት ሳይሆን ለሕወሓት
ነው። "ሽፍታ" ደግሞ እንኳንስ ግብር ለመክፈል ቀርቶ ለዕለት ቀለቡም እየዘረፈ እንደሚበላ አቶ ኃ/ማርያም አጥተውት ነው ብለን
አንገምትም። አባባላቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ከመናቅ የመነጨ እንደሆነ ግን የእስከዛሬው ታሪካቸው ጉልህ ማስረጃ ነው።
አዎን የአገራቸውን ሕልውና የሚደፍርና ማንነታቸውን የሚጋፋ ባላንጣ በተነሳባቸው ቁጥር የአካባቢው ነዋሪዎች ባላቸው አቅም
ንብረቶቻቸውንና ዳር ድንበራቸውን ይጠብቃሉ፣ ያስከብራሉ። መሪር የሕይወት መስዋዕትነትም ይከፍላሉ። ከአባቶቻቸው
የወረሱትን ንብረትና እነ አጼ ቴዎድሮስና እነ አጼ ዮሐንስ ያስረከቡንን ዳር-ድንበር ለማስከበር በመታገላቸው በዛሬ አገር ከሃዲዎች
“ሽፍታ” መባላቸው አይደንቀንም። ሽፍታውስ በአገርና በሕዝብ ላይ ያመጸ፤ ጫካ ሳይሆን ቤተመንግሥት በጉልበት ኃይል
የተቀመጠው ወያኔ እራሱ ነው።
"በርካታ ኪ/ሜትር ገብተው ሱዳን ውስጥ የሚያርሱ እኛም ሱዳኖችም የሚያውቋቸው የኛ ባለሃብቶችና ውስን አርሶ አደሮችም
እንዳሉ" አቶ ኃ/ማርያም አልሸሸጉም። ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል? በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ሳይሆን አቶ ኃ/ማርያም አባባሉን
በአንድ ራስ ወደ 3 ምላስ ከፍ አድርገውታል። በመጀመሪያ የሚሰጥም ለመስጠት የታቀደ መሬት የለም አሉ። አያይዘውም ነፍስ
እየገደሉ የሚኖሩ ሽፍቶች እንዳሉ አስታወቁን። ትንሽ ዝቅ ብለው ደግሞ ሁለቱም ወገኖች የሚያውቋቸው ቱጃር ገበሬዎች እንዳሉም
መሰከሩ። መሠረቱ ውሸት ነውና መደምደሚያው ግራ የሚያጋባ ሆነ። የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሚስተር ኢብራሒም
ጋሐንዶር ስለዚሁ ጉዳይ ለአልጃዚራ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ፤ በተለይ አል-ፋሽጋ የሚባለው ቦታ የሱዳን መሆኑን ከገለጹ
በኋላ በሁለቱ አገሮች መካከል ባለው መልካም ትብብር የተነሳ የሱዳን መንግሥት እነዚህ ገበሬዎች እንዲያርሱ የፈቀደላቸው
መሆኑን በዝርዝር ተናግርዋል።
በሱዳን በኩል ይህን ስራ እንዲያስፈጽም ኃላፊነት የተሰጠው የቴክኒክ ኰሚቴ የድንበር ከለላው ስራ በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቅ
ይፋ ከማድረጉም ባሻገር እስከአሁን ድረስ ሥራው አንዳችም እንቅፋት እንዳልገጠመው አበክሮ አስታውቋል።
የዚሁ የቴክኒክ ኰሚቴው ሹም ሚስተር አብደላ አል-ሳዲቅ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስነን ድንበር ርዝመቱ ወደ 725 ኪ/ሜ እንደሆነ
ገልፀው፣ ወደ 600 ሺህ ኤከርስ የሚሆነው ለም የእርሻ መሬትም ይዘትነቱ የኢትዮጵያ ሳይሆን የሱዳን እንደሆነ በሚገባ
አስምረውበታል።
አካባቢው እንደነ አትበራ (ጓንግ)፣ ሴቲት (ተከዜ) እና በሰላም (ባህረ ሰላም) የሚባሉ ትላልቅ ወንዞች በስም እየተጠቀሱ
የሚፈሱበት አካባቢ እንደሆነና ይዞታው የሱዳን መንግሥት ነው እያሉ የአገሪቱ ባለሥልጣኖች ለዓለም ሲያሳውቁ፣ በኢትዮጵያ
በኩል የሚሰጠው ምላሽ ግን "ሱዳኖች የፈለጉትን ሊናገሩ ይችላሉ" የሚል ነበር። ይህ ደግሞ የአገርን ድንበር የሚያህል ትልቅ የአገር
ጉዳይ አቅሎ ማየትና ወያኔም ዛሬም ቢሆን ከስህተቱ ታርሞ ለሕዝብ ዕውነትን ለመግለጽ ፈቃደኛ አለመሆኑን በተጨባጭ የሚያሳይ
ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የሕወሓት የ25 ዓመት አገዛዝ መሮት ከዳር እስከዳር ለፍትህና ለእኩልነት በተንቀሳቀሰበት በአሁኑ ጊዜ፤ የድንበር
ከለላውን ስራ እያጣደፉ እንዲካሄድ ማድረግ "አጥፍቼ ልጥፋ" ከሚል የአምባገነኖች ባህሪይና ዓላማ ውጭ ነው ለማለት ከቶ
አያስደፍርም።
ሕዝቡ እናስተዳድርሃልን በሚሉ ጎጥኞች ነጋ ጠባ መዘለፉ፣ መዋረድና የሚሰነዘርበት የሐሰት ውርጅብኝ ከአቅሙ በላይ እየሆነበት
መጥቷል። ዛሬ የኢትዮጵያን ሕዝብ የናፈቀው ነገር ቢኖር "ፀጥ እናደርግሃለን" የሚል አዕምሮው በዘር የተበከለ "መሪ" ሳይሆን
3
መብትህ ይጠበቅልሃል ብሎ ማንነቱን የሚያከብርለት መሪ ነው። በባዶ እግሩ የሚሄድ ባላገር ብሎ የሚዘልፈውን ሳይሆን "አርሶ
አደሩ ወገኔ" ብሎ የሚቀርበውን መሪን ነው ዛሬ ለማምጣት እየታገለ ያለው።
በመጨረሻ መስገንዘብ የምንፈልገው፤ አገርን የማስጠበቅ ኃላፊነታቸሁን ክዳችሁ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በሰተጀርባ በተዋዋላችሁት
ውል መሠረት አሳልፋችሁ የምትሰጡት የአገር ዳር-ድንበር በከፍተኛ መሰዋዕትነት ተከብሮ ለዘመናት የኖረ እንደመሆኑ ሁሉ፤ ዛሬም
በሚከፈለው የጀግንነት መስዋዕትነት እንደሚጠበቅ ቅንጣት ያህል ሳንጠራጠር ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን። ይልቁንስ
በምትፈጽሙት የአገር ክህደት ወንጀል በሕግም ሆነ በታሪክ የምትጠየቁ መሆናችሁን ከወዲሁ እናሳውቃለን።
አገራችን በታላቅ ጀግኖች ልጆቿ ተጠብቃ፣ ታፍራና ተከብራ እንደኖሮችሁ ሁሉ፤ ዛሬም ሆነ ነገ በቆራጥ ጀግና ልጆቿ መስዋዕትነት
ተጠብቃና ተከበራ ትኖራለች።
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በቆራጥ ልጆቿ ይከበራል!
ድል ለጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!
የዘመነ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ቅርምት
ገለታው ዘለቀ
በዛሬው ርዕስ ሥር የማነሳው ጉዳይ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ቅርምትን ይመለከታል። በርግጥ
ይህን ርዕሰ ጉዳይ በቅርቡ ከተቋቋመው የ EDF (Ethiopian Dialogue Forum) ድርጅት ዓባላት ጋር
በነበረን ቴሌ ኮንፈረስ ላይ ለውይይት አቅርቤው ነበር። ዛሬ ደግሞ በቀለም ቀንድ ጋዜጣ በኩል
ከሃገር ቤት ወገኖቼ ጋር ለውይይት ይሆነን ዘንድ መረጥኩት።
እንግዲህ በዓለም ላይ እጅግ ብዙዎቹ አገራት ወይ በባህል ወይም ደግሞ በሃይማኖት ብዙሃን ሆነው
አንድ አገር መስርተው ይኖራሉ። አንዳንዶቹ ሃገራት እጅግ ብዙ ቋንቋና ባህል ያላቸው ቡድኖችን
ይዘው በአንድ የፖለቲካ ጠገግ ውስጥ ይኖራሉ። ለምሳሌ ናይጀሪያ ወደ 250 ብሄሮችን ይዛ
እነዚህ ብሄሮች በአንድ ፌደራል ሪፐብሊክ ናይጀሪያ የፖለቲካ ጠገግ ስር ተጠልለው ይኖራሉ።
ኢንዶኔሽያን የመሰረቱ ቡድኖች ደግሞ ወደ 300 ቡድን ናቸው። በርግጥ በዓለም ላይ ካሉ ብዙህ
ሃገራት መካከል በጣም ብዙህ (Diverse) የሆኑት አገራት ቅድስት ምድር እስራዔልና የተባበረችው
አሜሪካ ናቸው። በዓለም ላይ ነጠላ ወይም ሆሞጂኒየስ የሚባሉ አገሮች በጣም ውሱን ሲሆኑ
ከአፍሪካ እንደ ቱኒዚያ አይነት ኣገሮችን ማለት ነው።
ታዲያ እነዚህ ብዙህ የሆኑ አገሮች የተለያየ ቋንቋና ባህል፣ ወይም ጎሳ፣ ወይም ሃይማኖት ይዘው
አንድ አገር መስርተው የሚኖሩት አንዳንዶቹ በጦርነትና በተለያየ ሃይል ተገፍተው ዛሬ
ራሳቸውን በአንድ የፖለቲካ ጠገግ ስር ያገኙ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ምን አልባት አብረን
ብንኖር ይሻላል በሚል ቡድኖች ተነጋግረው አንድ ሃገር መስርተው ይሆናል። ብቻ ግን እነዚህ
አገራት በአሁኑ ጊዜ ዝንባሌያቸው በባለፈው ታሪካቸው ላይ ሳይሆን ቀጣዩን ህይወታቸውን እያዩ
አገራቸውን አጠናክረው የሚኖሩበትን የፖለቲካ ጠገግ በሚገባ እያነጹ መኖር ላይ ነው። እነዚህ
ብዙሃን አገራት አንድ አገር የሚሉትን ሰፊ አዳራሽ ሲመሰርቱ በመስዋእትነት ነው። አገርን
የሚያህል ግዙፍ ነገር ዝም ብሎ ከንፋስ አይፈጠርም። መስዋእትነትን ይጠይቃል። መስዋእትነቱ
ምንድን ነው? ካልን ቡድኖች ካላቸው ሃብትና እሴቶች ላይ የሆነውን ለዚህ አዲስ ለሚፈጥሩት
አገር ለሚሉት ጠገግ መስዋእት ሲያደርጉ ነው። መቼም ይህ የጋራ ቤት ዝም ብሎ አይሰራም
ብለናል። ይህ አዳራሽ ሲሰራ ቡድኖችን የሚጠይቀው ነገር አለ። በመሆኑም ቡድኖች ጎራ እየከለሉ
ይኖሩበት የነበረውን መሬታቸውን እንዲሁም ደግሞ ፖለቲካዊ ማንነታቸውን ይሰውና አንድ አገር
አለን ይላሉ። ቋንቋዎቻቸውንና ባህላቸውን ደግሞ በየመኖሪያቸው ይዘው እያሳደጉ ሊኖሩ ይችላሉ።
እነዚህ ብዙ ብሄሮች በተለይ መሬታቸውንና ፖለቲካዊ ማንነታቸወን አደባልቀው አንድ ካርታ
ከሰሩ በሁዋላ አንድነት የሚለውን ብሄራዊ ማንነት የሚባለውን ገነቡ ማለት ነው። በመሆኑም ብዙ
ሆነው አንድ ነን ሲሉ በባህል የተለያየን ብንሆንም አደባልቀን መስዋዕት አድርገን የፈጠርነው ሌላ
ብሄራዊ ማንነት አለንና ያ ነው አንድ ነን የሚያሰኘን ማለታቸው ነው። ቢያንስ ያደባለቁት
መሬትና ፖለቲካዊ ስብእና ነው አንድነትን የሰራላቸው። በልዩነት አንድነት የሚባለውም ይህ
መሆኑ ነው መሰለኝ። ግዛትንና ፖለቲካዊ ማንነትን በአንድ ገበታ ላይ ዘርግፈው አደባልቀው
የእኔ…. የእኔ….. ቀርቶ የእኛ ሆኗልና ነው።
ወደ ሃገራችን ኢትዮጵያ ስንመለስ ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላት አገር ናት። ይህቺ አገር እንደ
ዓለም ወግ የተለያዩ ብሄሮች ሲመሰርቷት ግማሹ በቀላሉ ግማሹ በጦርነት የተሰባሰቡባት አገር
ስትሆን በቁጥር ከሰማኒያ ሁለት በላይ ብሄሮች አሏት። እነዚህ ቡድኖች በአንድ የፖለቲካ ጠገግ
ውስጥ ሲኖሩ ሲኖሩ ቆዩ። ልክ ሌላው ዓለም እንዳለፈበት የህይወት ጎዳና የኢትዮጵያ ቡድኖችም
አልፈው ሲያበቁ ሁዋላ በዘመናዊ ታሪካቸው ጊዜ ዘመናዊ አስተዳደር ሲመሰርቱ ቡድኖች
ያላቸውን እዋጥተው አንድ ነን የሚለውን በተሻለ መረዳት ተቀብለውት ኖረዋል። ያለፈው
ታሪካቸው ባይመች፣ የጋራ ታሪካቸው ብዙ ውጣ ውረድ ቢኖረውም በዚህች ዛሬ ራሳቸውን
ባገኙባት አገር ግን ቂም የላቸውም በውነት። ይሁን እንጂ ድንገት አንድ ትውልድ ተነሳ። ይህ
ትውልድ ኢትዮጵያ የተፈጠረችው ያለስምምነት ስለሆነ፣ ቡድኖች ሳይጠየቁና “ዴሞክራሲያዊ”
በሆነ መንገድ ያላችሁን ለኢትዮጵያ ማዋጣትና መስዋእት ማድረግ ትፈልጋላችሁ ወይ? ተብሎ
ሳይጠየቅ የዛሬ ስንት መቶ ዓመት በሃይል ያለንን እሴት እንድናደባልቅ ስለተደረገ እንደገና
እግዜር እንደፈጠረን የብሄር አስተዳደር መስርተን መኖር አለብን እንመለስ አለ። የብሄር ፖለቲካ
የመጨረሻ ግብ ምን እንደሆነ የማይታወቅ ቢሆንም በጫና ሰማኒያ በላይ የሆኑ ብሄሮች በዘጠኝ
ተከፈሉ። ይህቺ ኢትዮጵያ ስትፈጠር ዘጠኝ ናት ያለ የለም። ብቻ መንግስት እንዳሻው በዘጠኝ
ሸነሸነና በዞንና በልዩ ወረዳ የብሄር ፌደራሊዝምን እውን ለማድረግ ተነሳ:: በዚህ መሰረት በ
1983 ዓ.ም አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ስልጣኑን ከያዘ በሁዋላ ኢትዮጵያ በብሄር
ፌደራሊዝም የምትተዳደር አገር ሆና ታወጀባት።
ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን ተፈጠረ? ስንል ሃገር የሚፈጥሩትን ዋና ዋና ጉዳዮች ብሄሮች
እንዲቀራመቱ ተደረገ። ሃገር የሚባለውን ነገር የሚያቆሙት ካስማዎች እንደ ግዛት፣ ኔሽን፣
ፖለቲካዊ ማንነት፣ ታሪክ፣ የጋራ መግባቢያ እነዚህን ካስማዎች እየነቃቀልን በሙሉ በብሄሮች
ዙሪያ ተከልን። በዚህም ኢትዮጵያን የመቀራመት ስራ በመደረጉ አንድነት የሚለው ጉዳይ ሜዳ
ላይ ወደቀብን። ኢትዮጵያ አጨብጭቦ ባዶ እጆቿን ቀረች። ሃገር የሚመሰርተውን ኤለመንት ሁሉ
ብሄሮች ሙልጭ አድርገው ወስዱ። እንደ ቅርጫ ስጋ ታሪክን፣ ግዛትን፣ እሴቶችን፣ ፖለቲካዊ
ማንነትን፣ ሁሉ ተቃረጥን። ብሄሮችን ስስታም የሚያሰኝ ይህ የብሄር ፖለቲካ የወለደው
አስተዳደር ሲመጣ ከዚህ በፊት ለኢትዮጵያ መስዋእት ኣድርገነው የነበረውን የመሬት አንድነትና
ፖለቲካዊ ማንነት እየዘረፍን በየብሄራችን ውሰዱ ተባልን። በየብሄራችን የፖለቲካ ድርጅት
አቋቁመን ቁጭ አልን። ተፈርዶብን እንጂ ወደን አይደለም። መሬታችንን ቋንቋዎቻችንን
እየተከተልን ኮለኮልንና ከዚህ ወዲያ የእኔ ነው አልን። እኛ ራሳችን ኔሽን ነን አልን። ባንዲራዎች
ሰራን። እነዚህን ሁሉ ተቀራመትንና የቀረንን ስናስብ ታሪክ ነው። የብሄር ፖለቲካው መሃንዲስ
አቶ መለስ ዜናዊ የአክሱም ሃውልት ለወላይታው ምኑ ነው? በማለት የታሪክ ቅርምቱን በይፋ
ገለጹ:: በሌላ አነጋገር ይሄ ሃውልት እኔ የመጣሁበት ብሄር ሲሆን ሌሎቻችሁ በየሰፈራችሁ የሚገኝ
ቅርሳቅርስ ካለ ተቀራመቱ፣ ከዛሬ ጀምሮ የኢትዮጵያ ነው የሚባል ነገር የለም እንደ ማለት ነው።
እናም የታሪክ ቅርምት ጀምረንና ኢትዮጵያን ለመቀራመት እነሆ ተነሳን። የአሁኗ ኢትዮጵያ
ብሄራዊ ማንነት የት እንደገባ የጠፋብን ሚስጥሩ ለብሄራዊ ማንነት የተሰውትን መስዋእቶች
መልሰን እንድንዘርፍ ስለተገደድንና ስለተቀራመትን ነው:: በዚህም ብሄራዊ ማንነት ከቦታው
የጠፋብን።
ብሄራዊ ማንነት የጋራ ነገር ይሻል። ብሄራዊ ማንነት ህልው የሚኖረው ቡድኖች ጨክነውም
በቸርነትም በሚሰዋቸው እሴቶች የሚገነባ ማንነት ሲሆን ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ብሄራዊ ማንነት
አለኝ ለማለት ያስቸግራታል። በርግጥ ህዝቡ ቃኪዳኑን በልቡ ይዟል። ከማተቡ ጋር ኣስሮ ቀን
ይጠብቃል። ይሁን እንጂ ኦፊሺያሊ ብሄራዊ ማንነትና ኢትዮጵያዊነት ከነ ሙሉ ስልጣናቸው
የሉም። በግልጽ ቡድኖች የተቀራመቷት አገር እንድትሆን መንግስት ስለፈረደባት እነሆ ዛሬ
ኢትዮጵያ ይህ ቅርምት የተፈጸመባት አሳዛኝ አገር ናት። ያቺ ታላቅ አገር ኢትዮጵያ…….
አንድ እንደገና መሰመር ያለበት ጉዳይ ግን ይህ ቅርምት የኢትዮጵያን ቡድኖች ስነ-ልቡና
በፍጹም አይወክልም። እኔ እራሴ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን አየሁ…..
ኢትዮጵያውያን ሁሉ ቸሮች ናቸው። ደቡብ ውስጥ በቋንቋ የማንግባባ ሰዎች ቤት አምሽቼ ጠብ
እርግፍ እያሉ አስተናገዱኝ። የቤቱ አባወራ ከመሃል አገር የመጣሁ መሆኔን ሲያውቁ
ስለኢትዮጵያ ስለሃገራችን ታሪክ ሊያስረዱኝ ሞከሩ። ቋንቋ የሚገዛ ቢሆን ያን ቀን የኝህን ሰው
ቋንቋ ገዝቼ ማዳመጥ በቻልኩ ኣስብሎኛል። ትንሽ ትንሽ እኔ የምናገረውን ቋንቋ በሚሞክረው
ልጃቸው በኩል የሚነግሩኝ አንድነታችንን የኢትዮጵያውያንን ፍቅር ነበር። የኢትዮጵያዊነታችንን
ወዙን ኣሳዮኝ። ድሬ ተጉዤ ከቤቴ ያልወጣሁ መስሎ ተሰማኝ። ብዙ ውየ ባድር እየተመኘሁ
ተመለስኩ። ናዝሬትን ሳይ፣ ደሴን ሳይ፣ ወዘተ… ኢትዮጵያውያን የማይናወጥ የአንድነት የፍቅር
መንፈስ እንደገዛቸው ተሰማኝ። የኢትዮጵያ ብሄሮች ቸሮች፣ እንግዳ ተቀባዮች፣ በአንድ ገበታ
የሚበሉ ናቸው። ያላቸውን ለማዋጣት እምቢ ማለት የሚያሳፍራቸውና የማይወዱ ናቸው።
እውቀታቸውን ቢሆን፣ ጥበባቸውን ቢሆን፣ መሬት ቢሆን፣ ቁሳዊ ቢሆን መንፈሳዊ ባህል
ለሃገራቸው ለኢትዮጵያ ሰውቶ መልሶ ለመንከባከብ በጥብቅ የሚፈልጉ ናቸው። የኢትዮጵያ
ፖለቲካ ይህን የህዝቡን ስነ-ልቡናና ባህል መሰረት ማድረግ አለበት። ይሁን እንጂ በተጽእኖ
የተጫነባቸው የብሄር ፖላቲካ የሚወዷትን አገራቸውን እንዲቀራመቱ በማድረጉ ሃገራቸው
ውስጣዊ ሉዓላዊነቷ ተሰነጣጠቀ።
መንግስት በዴሞክራሲ ዘመን፣ በግሎባላይዜሽን ዘመን፣ የሰባዊ መብት ጉዳይ በጣም ትኩረት
ባገኘበት ዘመን አዲስ ነገር ተገልጦልኛልና ሁላችን በየቀያችን እንስፈር ሲልና የጋራ የማህበር
ቋንቋ እንኳን ሲያሳጣን የተጎዳችው ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ኢትዮጵያዊነትም ወዙን አጣ።
ለአንድ እናት ልጆች መግባቢያ ቋንቋ እንኳን የማይገደው መንግስት ገጠመን። የቋንቋ ሃብታሞች
ሆነን የፍክክር ቤት እንደሚባለው አንድ የማህበር ቋንቋ እንኳን አጣን።።
በዚህ ቅርምት ምክንያት ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጣዊ ሉዓላዊነቷ አደጋ ላይ ወድቆብናል። አንድ አገር
ሉዓላዊ ነው የሚባለው በውስጡ የሚኖሩ ቡድኖች ቢያንስ በመሬት አንድነትና በፖለቲካ ማንነት
ኣንድ ሲሆኑ ወይም ፖለቲካቸው በዚያ ባደባለቁት መሬት ካርታ ስር በአንድ ብሄራዊ ማንነት ስር
ሲቆም ነው። ኢትዮጵያ በቡድኖቿ ከፍተኛ ቅርምት የተካሄደባት አገር በመሆኗ ያለ ጥርጥር
ውስጣዊ ሉዓላዊነቷ ተደፍሯልና ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያውያን ካሏቸው ልዩነቶች ሁሉ
በላይ ጉልህ ጉዳይ ገጥሟቸዋል።
አንቀጽ 39 በራሱ የሚያሳየው ይህቺ አገር ቡድኖች በስስት የያዙትን ብጥስጣሽ መሬት ይዘው
በፈለጉት ጊዜ ሽርፍ እያሉ መሄድ እንደሚችሉ ነው። ይህ ማለት ይህቺ አገር ሉዓላዊነቷ ዘላለማዊ
ያልሆነ በየትኛውም ጊዜ እየተሸረፈች ልታልቅ የምትችል ተደርጋ የተፈረደባት ሆናለች ማለት
ነው። ቡድኖች ያላቸውን እሴት ሁሉ በራሳቸው ስም አስመዝግበው መቆየታቸው የሚጠቅመው
ለዚህ ለመሸረፍ ቀን ምቹ እንደሆነ መሪዎች ሳይሰቀጥጣቸው ኮራ ብለው ይናገራሉ። ይህንን
እያነሱም አዲሲቱ ኢትዮጵያ ኣሁን ተራምዳለች ይላሉ። የብሄር ብሄረሰቦች መብት እስከ
መገንጠል በሚል መሪ ቃል ዴሞክራሲን እውን ኣደረግን ብለው ያረፉ መሪዎች ያሉን እኛና እኛ
ብቻ ነን። ደግሞ የሚያሳዝነው በዚህ በመለየት አንቀጽ ቡድኖች ተዝናንተዋል ይሉናል። ቡድኖች
ይህ ኣንቀጽ ዋስትና ስለሆናቸው እፎይ ብለው ተኝተዋል ይሉናል። ይህበ እውነት ለኢትዮጵያ
ህዝብ ስድብ ነው። በባህላችንም ቢሆን እንኳን ኣብሮ የኖረ ሰው ሲለያይ ተላቅሶ መልካም
እመኝልሃለሁ ተባብሎ ይሄዳል እንጂ ይሄን ያህል በመለያየት የሚዝናና ብሄር የለንም።
ፍልስፍናው ራሱ የሰው ልጆችን ባህርይ አላገናዘበም። ብሄሮች በመገንጠል አንቀጽ የሚዝናኑ
ከሆነ ለምን ኣብረው ይኖራሉ? እንዴት ሰው በመለያየት አንቀጽ እየዘለለ አብሮ ይኖራል? በዚህ
ደረጃ መለየት ያዝናናቸው ቡድኖች በምን ያህል ፍቅርና መተማመንስ ይኖራሉና ነው እንዲህ
የሚሉን?
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመባት ቅርምት በአንድ በኩል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት
ፈርክሶ የጣላባት ሲሆን ለጊዜው ግን አገሪቱ በወታደር ተጠርንፋ ትገኛለች። ይህ መንግስት
ስልጣን ከያዘ በሁዋላ ትልቁ ዘፈኑ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ የራስን እድል በራስ መወሰን፣ የራስ
ቋንቋ፣ ራስ… ራስ…. ራስ….። በመሰረቱ አገር በእኔ….. እኔ….. እኔ….. እኔ….. ኣይቆምም።
ኣገር የሚቆመው በእኛ ነው። እኛ ህዝቦች (we the people….) በሚል ነው ኣገር የሚቆመው።
ስለዚህ እኛ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ህዝቦች ሁሉ ይህን በመስዋዕትነት የፈጠርነውን አገር እንዳናጣ
ይህን እኔ… እኔ….. እኔ…. እናቁምና ወደ “እኛ” ምእራፍ እንሻገር።
ይህ ስስት የጥቂት የፖለቲካ መሪዎች ባህርይ እንጂ የኢትዮጵያ ብሄሮች አይደለም። የኢትዮጵያ
ብሄሮች የገጠማቸው ክፉ ችግር ይሄ አይደለም። የኢትዮጵያ ብሄሮች የሚፈልጉት ዴሞክራሲን፣
መልካም ኣስተዳደርን፣ ከድህነት መውጣትን፣ ባህላቸውን መጠበቅን ነው። ስለዚህ ቡድኖች
እንደገና ሊትክዙ ይገባ ይመስለኛል። ይህችን የምንወዳትን ኣገር መስዋእት ኣድርገን እንደገና
ብሄራዊ ማንነታችንን ልንገነባው ይገባል የሚሉበት ዘመን ነው። ለሂቃኑ ሊቆጡ ሊነቁ የሚገባበት
ዘመን ላይ ነን። ከፍ ሲል እንዳልኩት በዓለም ላይ ያሉ ብዙዎቹ ኣገራት የሚኖሩት ቡድኖች
እያዋጡ መስዋእት እያደረጉ ነው። ለዓለም ይህ የቅርምት ኣስተዳደር የሚጠቅም ቢሆን ብዙ
አገሮች በተከተሉት። ነገር ግን ይህን ጥለው ኣልፈው ሄደዋል። በቡድኖች መካከል ይሁን በግለሰብ
ደረጃ የሰባዊ ጥሰት ሲገጥማቸው፣ ኣሰቸጋሪ ኣስተዳደር ሲገጥማቸው ለዴሞራሲና ለመልካም
ኣስተዳደር ይጥራሉ እንጂ በቁጣ ሮጠው ኣገራቸውን ኣይቀራመቱም። በቃ ካልሆነ በየቤትህ እደር
ብለው ወደ ልዩነት ፖለቲካ ኣይገቡም። በዓለም ዓቀፍ ህግም ቢሆን አገሮች ብሄራዊ
ሉዓላዊነታቸውን ይጠብቁ ዘንድ ነው የሚበረታቱት። እንደ ኢትዮጵያ ኣይነት ኣስተዳደር በዓለም
ቢሰፍን ዓለምን ሊያፈርሳት ይችላል። እሚገርመው ነገር የዓለም አገራት እንደ ኢትዮጵያ ያለ
የብሄር ፖለቲካ የፈጠረውን የብሄር ፌደራሊዝም ቢከተሉ ፕላኔት መሬት ልትፈርስ ትችላለች።
ለዚህ ነው በዓለም ህዝቦች ዘንድ የማይደገፈው።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ከዴሞክራሲና ከመልካም ኣስተዳደር ጥያቄ ጎን ለጎን የሉኣላዊነታችን
ጉዳይ ምን ላይ እንደሆነ ልናይ ይገባናል። የተቀራመትናትን ኢትዮጵያን እንደገና መስዋዕት
ልናደርግ የሚገባንን ኣድርገን ልናንጻት ይገባል። አገር አምሮን፣ የጋራ ቤት አምሮን ግን ደግሞ
ምንም መስዋእት ሳናደርግ ብሄራዊ ማንነት ሳንፈጥር መኖር አይቻልም። አሁን ያለው
የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ቅርምት ኣስተዳደር ስልት ወደ ኮንፌደሬሽን የቀረበ ነው። አገሮች
በኮንፌደሬሽን መተዳደር ካማራቸው ብዙ መስዋእት አይጠይቃቸውም። የጋራ ሚሊተሪና
የተወሰኑ ጉዳዮች ኖሯቸው ራስን በራስ ማስተዳደር የሚባለውን እውን ሊያደርጉ ይችላሉ።
ኢትዮጵያ እንደ ኮንፌደሬሽን ባለ የፖለቲካ እምነት ውስጥ ገብታ ግን ደግሞ በጣም ጠንካራ
በሆነ ፈዴራል መንግስትና በጣም ደካማ በሆኑ የክልል መንግስታት ትተዳደራለች። ይህ ችግር
ለሃገሪቱ ሶሺዮ ፖለቲካ ችግሮች ዋና መጋቢ ችግር ሆኖ እናያለን። የራስ በራስ ማስተዳደር
የምንለው አሁን ባለው በብሄር ፖለቲካና በብሄር ፌደራሊዝም እውን ኣይሆንም። አሁን
የምናያቸው የብሄሮች የፖለቲካ ኣሰላለፍ ግራ መጋባትና የህዝቡ የግልጽነት ጥያቄዎች በቀጥታ
የሚያያዘው ኢትዮጵያ አየተከተለችው ካለው ግራ አጋቢ የፖለቲካ መዋቅር ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን የማንነት ጥያቄዎቻችንን በአንድ በኩል ሊመልስ የሚችል መሆን ያለበት
ሆኖ በሌላ በኩል ደግሞ በመዋጮ የሰራነው የጋራ ቤት ሊኖረን ያስፈልጋል። ስለዚህም
ኢትዮጵያውያን ወደ አዲስ ኪዳን ልንሻገር ይገባል። የተቀራመትናትን አገር እንደገና
የወሰድንባትን ሁሉ ባስቸኳይ እንመልስ። እንዴውም ጨምረን ሰውተን የጋራውን ቤታችንን
ደግመን ማነጽ አለብን። ኢትዮጵያን በአዲስ ኪዳን አንጸን ሰርተን ከዓለም ህዝቦች የመጨረሻ
ያደረገንን ድህነት ልንዘምትበት ይገባል። ስለ አዲሲቱ ኢትዮጵያ የመንግስት ውቅር ጉዳይ አንድ
በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አንድነት የሚል ኣሳብ ጸሃፊው በመጽሃፍ መልክ እያዘጋጀ
ስለሆነ ወደፊት መጽሃፉ ሲታተም በዚህ ዙሪያ ማብራሪያ ይሰጣል እስከዚያው ግን ቅርምተ
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የእኛ የኢትዮጵያውያን የመወያያ አጀንዳ ይሆን ዘንድ ይጋብዛል ።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
geletawzeleke@gmail.com
Ethiomedia.com – February 18, 2016
1
የወያኔ የህልውና መድህን አክራሪና የመገንጠል
ዓላማ የተጠናወታቸው ቡድኖች ናቸው
የኢትዮጲያ ህዝብ በወያኔ ጨካኝ አገዛዝ እየተሰቃየ በመሆኑ በተለያያ ጊዜያት
ተቃውሞውን በተለያየ የአገራችን ክፍል ገልጿል። በዚህም ብዙ የንጹሃን ደም ፈሷል።
በቅርብ ጊዜ በኦሮሚያ የአገራችን ክፍል እየተካሄደ ያለው የህዝብ እምቢተኝነት የወያኔ
አገዛዝ ካጋጠመው ፈተና ሁሉ ከፍተኛው ነው። ይህን የድል ተስፋ የታየበትና፣ ብዙ
ንጹህ ዜጎች መስዋዕት የሆኑለትን እምቢተኝነት ለማፈን ወያኔወች ብዙ ታንክና የአጋዚ
ጦር ከማሰለፍ የበለጠ ተቃዋሚወችን በዘርና በቋንቋ መከፋፈልን ይመርጣሉ። ለወያኔወች
የህልውናቸው መድህን አክራሪና የመገንጠል ዓላማ የተጠናወታቸው ቡድኖችና ግለሰቦች
ናቸው። ኢትዮጲያዊ ከኢትዮጲያ አንድነትና ሉዓላዊነት በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ምንም
ነገር የለም።
በኦሮሚያ የሚካሄደውን የህዝብ እምቢተኝነት ለምን ሌላው የአገሪቱ ህዝብ ለመቀላቀል
ተቸገረ ወይም ዘገየ የሚለው የወቅቱ የመወያያ ርዕስ ሆኗል። ደርግ የፈጠረብንን ጊዚያዊ
የአምባገነን በሽታ፣ ወያኔ በቀላሉ በማይነቀልና ለአገር አንድነት አስጊ በሆነ የዘረኝነት
በሽታ ተክቶታል። በአሁኑ ጊዜ የሚደረገው ትግል አምባገነኑንና ጎሰኛውን የወያኔ አገዛዝ
ከስልጣን አውርዶ፣አንድነቷና ሉአላዊነቷ በተጠበቀች ኢትዮጲያችን የህግ የበላይነት
የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ መንግስት መመስረት ነው።
ኢትዮጲያዊ ለአገሩ ሉዓላዊነትና አንድነት ቅድሚያ እንደሚሰጥ የተረዳው ወያኔ፣
ተቃዋሚወችን የመምቻው ዋና መሳሪያ መከፋፈልና፣ የመገንጠል አቋም የሚያራምዱ
ወገኖችን አሰልጥኖ ማሰለፍ ነው። ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች እንደሚባለው፣
ኢትዮጲያዊያን ለአገራቸው አንድነት ሲሉ ብዙ ጥቃትና ግፍን ተሽክመው ቆይተዋል።
ከዚህ አንጻር የምናየው ሰሞኑን እየተደረገ ያለውን ትግል የዘርኝነት ተልዕኮ ያላቸው
ግለሰቦች በመጥለፍ “የኦሮሞ ሕዝብ የአገር ባለቤትነት” የሚደረግ ትግል
ነው፣ “ኦሮሚያ የኦሮሞ ናት” በማለት ብዙውን የኢትዮጲያ ህዝብ ትግሉን
እንዳይቀላቀልና አገሩን ከወያኔ የግፍ አገዛዝ ነጻ እንዳያወጣ መሰናክል እየሆኑበት ነው።
እነዚህ ወያኔ ካሳያቸው የጎሳ መስመር ዉጭ ማሰብ የማይችሉ ጠባብና ዘረኛ አካሄድ የያዙ
ወገኖች የሚከፈለውን መስዋእትነት መልካም ዉጤት እንዳይኖረው እያደረጉ ነው።
ትግሉን ሊቀላቀል የሚገባውን ህዝብ ገፍተው እያራቁት ነው።
ይህን የኦሮሞ ወጣቶች በኢትዮጲያ ለፍትህና ለህግ የበላይነት የሚደረግ ትግል አቅጣጫ
ለማስቀየርና፣ በህዝብ ዘንድ ጥላቻን ለመዝራት የሚጠቀሙባቸውን ግለሰቦች ምንነታቸውን
ማወቅ አስፈላጊ ነው። ግለሰቦቹ ከተለያየ አቅጣጫ አስተያየት ቢሰጣቸውም ለትግሉ
መሰናክል መሆናችውን ሊያቆሙ ባለመቻላቸው ጥፋታቸውን በግልጽ ማሳየት አስፈላጊ
ሆኗል።እነዚህም ግለስቦች እየፈጸሙ ያለውን ስህተት ቆም ብለው ማሰብና አሁንም
አቋማቸውን መመርመር ይገባቸዋል።
2
የኦሮሞን ህዝብ ከሌላው የኢትዮጲያ ህዝብ፣ ሙስሊሙን ኦሮሞ፣ ከክርስቲያኑ ኦሮሞ፣
ወያኔ በነደፈው ዘዴ፣ ለማጣላት የሚቀሰቅሱ የወቅቱ የዘር ጥላቻ ማዕከል የሆኑ ግለሰቦች
ከዚህ አጥፊ ተግባራቸው ሊታቀቡ ይገባል። ከነዚህ ግለሰቦች ተግባር ከወንጀለኞቹ
ወያኔወች በስተቀር የሚጠቀም የለም። ይህን በማድረግ ቅድሚያ ከሚጠራው አንዱ
ወጣት ከአገሩ የወጣው ገና የአስረኛ ክፍል ትምህርቱን እንደጨረሰ ሲሆን፣ በኦነግ
ተዋጊወች ተኮትኩቸ አድጊያለሁ፣ ቁቤ ያስተማሩኝ የኦነግ ተዋጊወች ናቸው፣ ከማለቱ
በስተቀር ስለኢትዮጲያና የኢትዮጲያ ህዝብ አኗኗር መስተጋብርና ታሪክ ብዙም ግንዛቤ
የለውም፣ ወይንም እንደተማረ ሰው እውነቱን ለመመርመርና ለማወቅ አይፈልግም። ይህ
በዚህ በወጣትነት እድሜው ኢትዮጲያን ባልተለመደ መንገድ ለቆ የወጣ ወጣት፣
የቀደምት ኦነግ መሪወች እርግፍ አድርገው የተውትን፣ የማያዋጣና ጊዜው ያለፈበት
አቋም፣ ለምን የራምዳል?
ይህ ግለሰብ ሰሞኑን ይህን ብሏል፤
"ኦሮሚያ የኦሮሞ ነች" የሚለው መሪ ሀሳብ በአሁኑ ወቅት በትግሉ ውስጥ ያለን የኦሮሞ
ወጣቶች ያመጣነው ወቅታዊ መፈክር ሳይሆን የዛሬ አመሳ አመት ገደማ የኦሮሞ ተጋዮች
ለነፃነታቸውና ለእኩልነት ትግል ሲጀምሩ የትግሉ ዋና መሰረት በማድረግ አንግበውት
የተነሱት የሀገር በለቤትነት (mirga abbaa biyyummaa) ጥያቄ ነው።…..ይህ ማለት ኬኒያ
ወይም ኦሮሚያ ውስጥ ሌላ ሰው መኖር ዜጋ መሆን አይችልም ማለት አይደለም። በሚገባ
ይችላለ። የማይቻለው ሀገሬው ተገፍቶ የሀር ባለቤትነት መብቱን ተነጥቆ ሌላው
ሊንደላቀቅበት ማሰቡ ነው። እናም ኦሮሚያ የኦሮሞ ነች የሚለውን መፈክር ልናፍርበት
ሳይሆን በደማችን እውን ለማድረግ እየታገልንለት ያለ ህያው አላማችን ነው።”
ቀድም ባለ ጊዜ ግለሰቡ ይህን ብሎ ነበር፤
“እኔ ባለሁበት ዘጠና ዘጠኝ በመቶ ሙስሊም ነው ስለዚህ ማንም ሰው ደፍሮ ቀና
አይልም፣ በሜጫ ነው አንገቱን የምንለው”
እንደዚሁም ቀደም ብሎ ለወያኔ መንግስት ዲፕሎማት የነበረ ግለሰብ አሁን የዚህን ሰው
አላማ “ለአገር ባለቤትነነት የሚደረግ ትግል ነው” በማለት በማራገብ ላይ ነው።
እነዚህን የመሳሰሉ ግለሰቦች የወያኔን የግፍ አገዛዝ ለመስወገድ የሚታገለውን ህዝብ
በኦሮሚያ አካባቢ የሚደረገውን ትግል በጥርጣሬ እንዲያየውና የተከፈለው የህይወት
መስዋትነት ለድል እንዳይበቃ እያደረጉ ነው።
ተረግጦ እየተገዛ ያለው የኢትዮጲያ ህዝብ የነዚህ አይነት አፍራሽና ከፋፋይ ተልዕኮ
ያላቸውን ግለስቦች በአግባቡ ለይቶ በማወቅ ጊዜው ሳይዘገይ ሊመክራቸው
ሊያስመክራቸውና ሊመልሳቸው ይገባል። ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከመገንጠል ይልቅ
አንድነትን ማስተማር አለባቸው። በዚህ መንገድ ስህተታቸውን አስተካክለው ከሌላው
የኢትዮጲያ ህዝብ ጋር በመተባበር ትግሉን ለድል ለማብቃት አስተዋጾ ማድረግ
አለባቸው። ትግሉን በአገራዊ ጉዳይ ዙሪያ በማስተባበርና፣ በሰለጠነ መንገድ
በመወያየት፣ የጋር ስልት በመንደፍ፣ በአንድ ሆኖ ወያኔን መታገልና ከስልጣን ማውረድ
3
ይገባል። በወያኔ ኢሰብአዊ አገዛዝ መከራውን የሚያየው የኢትዮጲያ ህዝብ ከሁሉም
ጎሳ፣ ከሁሉም አካባቢ፣ ከሁሉም ሃይማኖት ነው። ከግፍ ፈጻሚወቹ በስተቀር በወያኔ
የልተበደለ ኢትዮጲያዊ የለም።
ደረቱን ለአጋዚ ጥይት ሰጥቶ መስዋዕትነት እየከፈለ ያለው ኢትዮጲያዊ አንዱን ዘረኛ
አውርዶ በሌላ ዘረኛ ለመተካት ወይንም አገር ለማፍረስ አይደለም። ስለዚህ እነዚህን
ከፋፋይ የሆኑ፣ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የወያኔ ተልዕኮ ያላቸው፣ ዘርን ከዘር፣
ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጣሉ፣ ግለሰቦች የወያኔን የስልጣን እድሜ እንዲያራዝሙ
ሊፈቀድላቸው አይገባም። እንደነዚህ አይነት ወደፊት ከማሰብ ይልቅ ወደኋላ ማሰብ
የሚቀናቸው፣ ከአንድነታችን ይልቅ ስለልዩነታችን ብቻ መናገር ስራቸው የሆነ፣ ግለሰቦች
ለዘመናት አብሮ የኖረውን፣ በደም የተሳሰረውን፣ የኢትዮጲያ ህዝብ ለመከፋፈልና፣
የአንድነት ታሪኩን ለማራከስ የሚያደርጉት ስራ አደገኛ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጲያዊ
ሊቃወመውና ይገባል። የኢትዮጲያ ህዝብ በዘር በሃይማኖት ሳይከፋፈል በችግሩ ላይ
በእውነትና፣ መልካም ዉጤት ለማምጣት፣ በመወያየትና፣ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ
የጋራ መፍትሄ በመፈለግ፣ የወያኔን ጨካኝ አገዛዝ ለመጣል የሚያደረገውን ትግል
አጠናክሮና አስተባብሮ ሊቀጥል ይገባል። ሁሉም ኢትዮጲያዊ በጋራ በመወያየት
ለትግሉ ግልጽ ስልትና አላማ በመንደፍ በጋራ መስራት የወቅቱ ተቀዳሚ ጥያቄ ነው።
የወያኔን የጭካኔ አገዛዝ ለማስወገድና፣ የተሻለ አስተዳደር ለኢትዮጲያ ህዝብ ለማምጣት፣
ምንጊዜም ቢሆን ከአንድነት ውጭ አማራጭ የለንም። አንድነት ኃይል ነው።
ኢትዮጲያ በአንድነቷ ለዘላለም ትኑር!
አበራ ቱጂ
አዲስ አበባ
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
February 22, 2016
Subscribe to:
Posts (Atom)