Monday, April 6, 2015

1 ለራሱ ሕዝብ አዋኪ፤ ለውጭ-ኃይል ተንበርካኪ! የኢትዮጵያን ብሔራዊና አገራዊ ጥቅም ለጊዚያዊ ሥልጣን ማቆያ አሣልፎ የመስጠት ጥንውት የማይለቀው ተንበርካኪው የሕወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ የግል አስተያየት : - ከ አያል ሰው ደሴ ወርኀ መጋቢት፡ ፪ ሽህ ፯ ዓ/ም ዓባይ አገራችን ኢትዮጵያ እስካሁን በምትችለውና በምትፈልገው መጠን ልትጠቀምበት ያልቻለች ብሔራዊ የተፈጥሮ ሃብት ብቻ ሣይሆን ለፀትታዋ፣ ለአንድነቷ፣ ለሉዓላዊነቷና ለብሔራዊ ክብሯ ፈታኝ፤ ለሕዝቧም የዝንታለም የቁጭት መገለጫም የጥቃት ሰበብም ሆኖ የቆየ ወንዝ ነው። ብዙ አገር-ወዳዶች የታላቁን የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ አጥብቀን የደገፍነው እቅዱ ሲጠናቀቅ ከሚሰጠው ታላቅ የልማትና ዕድገት ቁሣዊ አገልግሎትና ጠቀሜታ በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የአገራዊ ፀጥታ፣ መረጋጋትና ነፃነት፣ የብሔራዊ ክብርና በራስ-የመተማመን መገለጫ ከመሆኑ አኳያ በማየት ነው። ለዚያም ነው በተለይ የአገሪቱን አንድነት ላስጠበቀ የፖለቲካ ለውጥ ለምንታገል ወገኖች ይኽ ኅዳሴ ግድብ ብሔራዊ እቅድ ላይ የሚወሰድ አቋም አገዛዙን በምናይበት ዓይን በግልቡ በመመልከትም ይሁን በተለመደና አዘቦታዊ በሆነ ደፈናዊ ተቃውሞን ተከትሎ ሣይሆን ከላይ ከተጠቀሱት መመዘኛዎች አኳያ የምንታገልለት ብቻ ሣይሆን የምንታገልበት ዓላማ ሊሆን እንደሚገባ በበኩሌ ያሳሰብኩት። ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የለገሳትን የዓባይ ውሃ ለመጠቀም ታላቁን የኅዳሴ ግድብ ለመገንባት የተያዘውን እቅድ ከልብ ከደገፉና ከሚደግፉ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ እኔ ነኝ። አሁንም ሆነ እስከወዲያኛው የዚኽ ብሔራዊ እቅድ ደጋፊ ነኝ። ይኽ ግንባታ ከሕወሓት/ኢሕአዴጋዊ የአንድ ድርጅት የግል እቅድነት ወጥቶ አገራዊና ብሔራዊ እንዲሆን የአንዳንዶቻችን ውትወታም ከግድቡ ብሔራዊ አስተጋብዖና ዋጋነት አኳያ የዜጎች በጎ-ፈቃድ ያለበት ሙሉ ተሣትፎ አስፈላጊ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የአገዛዙ መሪዎች እስካሁን በተጨባጭ እንዳረጋገጡት ከሕዝብ ጀርባ በሚያደርጓቸው ድብቅ ስምምነቶች ያለ-ምንም ታሪካዊና ሕጋዊ ምክንያት የአገርን አንጡራ መሬት ለባዕዳን አሣልፎ የመስጠትን የመሣሰሉ እጅግ ከባድ፣ ኃላፊነት-የጎደላቸውና በክህደት-አስጠያቂ የሆኑ ውሳኔዎችን ለመውሰድ ቅም እንደማይላቸው ከመረዳትና ለባዕዳን ጫና ያላቸውን የተንበርካኪነት ባኅሪ በመገንዘብ እንደሆነ ግልጥ ነው። የታላቁን የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ እቅድ በተመለከተ ረቂቁ የካቲት ፳፬ ቀን ፪ ሽህ ፯ ዓ/ም (March 3, 2015) ቀርቦ መጋቢት ፲፬ ቀን ፪ ሽህ ፯ ዓ/ም (March 23, 2015) ሱዳን ዋና ከተማ ኻርቱም ላይ በግብፁ አብዱል ፋታህ አል ሲሲ፣ በሱዳኑ ዑመር አልበሽር እና በኢትዮጵያው ኃይለማርያም ደሣለኝ አማካይነት ተፈጸመ የተባለው “በመርኅ ላይ የተመሠረተ የስምምነት አዋጅ” አገር-እና-ወገን-ወዳድ ኢትዮጵያውያንን ግር ያሰጠ፣ ብዙዎችንም ከልብ ያሳሰበ፣ ያሣዘነና እያነጋገረ ያለ፣ ወደፊትም ብዙ ሊያከራክርም ሊያወዛግብም የሚችል ጉዳይ መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም። በዚኽ ግድብ ዙሪያ ላለፉት አራት ዓመታት ከበርካታ ኢትዮጵያውንም ሆነ ኢትዮጵያዊ ካልሆኑ ሰዎች በተቃውሞም ሆነ በድጋፍ መልክ ብዙ የተለያዩ አስተያየቶች መቅረባቸው ይታወቃል። በበኩሌም በጉዳዩ ላይ ሰፋ-ያለ አስተያየት ሰጥቻለሁ። በዚያ ጽሑፍ ላይ ሦስት ጉዳዮችን ማለትም፡- ይኽ ብሔራዊ እቅድ ለምን መደገፍ እንዳለበት፣ ግድቡ ሙሉ-በሙሉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ-ጥቅም ባስከበረ መንገድ እንዲጠናቀቅና አገልግሎቱን በአስተማማኝ ሁኔታ ሊሰጥ እንዲችል በአንድ በኩል በገዥው ክፍል፣ በሌላ በኩል በአገሪቱ ላይ አዎንታዊ-ለውጥ እንዲመጣ በሚታገለው ወገን መወሰድ ስለሚኖርባቸው እርምጃዎች፣ እና ግድቡ በታቀደው መሠረት ሥራው እንዳይጠናቀቅ እክል ሊሆኑ የሚችሉ ስጋቶቸን ለማሳየት ሞክሬአለሁ። ለመሆኑ ይኽ “በመርኅ ላይ የተመሠረተ የስምምነት አዋጅ” ኢትዮጵያውያንን ለምን አሳሰበ? 2 እስኪ ከሁሉ በፊት ለ‘ስምምነቱ’ የተሰጠው ስያሜ ላይ መግባባት ይቻል እንደሁ እንይ። ይኽ ‘ስምምነት’ ሲጠናቀቅ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ጊዜ የሦስቱን ውል-ፈጻሚ መሪዎች ምስል (ፎቶ) አጅቦ የሚታየው በሦስት ቋንቋዎች የተጻፈ ንባብ የሚያሣየውና ከዚያም በኋላ በኢሕአዴግአውያን ሲነገር የሚሰማው ስምምነቱ ‘በመርኅ ላይ የተመሠረተ’ ነው ይላል። ሆኖም የእንግሊዝኛው አባባል ‘በመርኅ ላይ የተመሠረተ’ የሚል ነገር የለውም። ከየት እንደመጣና ለምን አላውቅም። የዚኽ በድብቅ የተደረገና አሁን ይፋ የሆነ የስምምነት ሰንድ የአማርኛ ቅጂ እስካሁን ይፋ አልተደረገም። በውጭ-ጉዳይ ሚኒስቴርም ሆነ በአገሪቱ የዜና ወኪሎች ድረ-ገጾች ላይ ፈልጌ ላገኘው አልቻልኩም። በግብፆችና በሱዳኖች በኩል ግን በሁለቱም ቋንቋዎች (በአረብኛና በእንግሊዝኛ) ይፋ ተደርጓል። ስምምነቱ በግብፆችና በሱዳኖች መኻል ብቻ የተደረገ ሣይሆን ከኢትዮጵያ ጋር ያደረጉት ስለሆነ፤ አገዛዙ ለዚኽ ስምምነትም እንደተለመደው የራሱን ትርጉም እየሰጠ ዓይኖቻችሁን ጨፍኑ፣ ጆሮዎቻችሁን ድፈኑ በሚል ከንቱ አደንቋሪ ልፈፋ ‘ድል ተገኘ.. አጨብጭቡ’ ከማለቱ በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ በስሙ የተደረገውንና የተፈረመውን ውል በቅድሚያ በአገሪቱ መንግሥታዊ ቋንቋ(*1) (በአማርኛ) ቀጥሎም በዋና-ዋና ቋንቋዎቻችን ተተርጉሞ በአስቸኳይ ይፋ እንዲሆንና ሌት-ተቀን ገንዘብ አዋጣ እየተባለ የሚወተወተውና ተስፋ የተሰጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲመረምረውና ሃቁን እንዲረዳ ያስፈልጋል። የአድዋ ጦርነት ይፋ መነሻው በውጫሌ ውል ላይ ሆን-ተብሎ ተጣምሞ በተሰነቀረ የቃላት አገባብ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። ለነገሩ በአገሮች መኻል የሚደረጉ ዓለም-አቀፍ ውሎች በውል-ፈጻሚዎቹ መንግሥታዊ-ቋንቋዎች ተተርጉመው መቅረብ ብቻ ሣይሆን ትርጓሜውም ትክክል መሆኑ ሊረጋገጥ ይገባል። ይኽ የሚሆነው ደግም ለአገሮቹ ብሔራዊ ክብር ብቻ ሣይሆን በተለይ የሕዝብ-ተወካዮች ም/ቤት (ፓርላማ) ባለባቸው አገሮች ከሌላ አገር ጋር የሚደረግ ውል መጽደቅ ያለበትና ሕጋዊነት የሚኖረው በዚኽ አካል ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በሚገኝ ይሁንታ ስለሚሆንና ያ ደግሞ ውሉ በአገሩ ቋንቋ መሆንን የግድ ስለሚል ነው። በእርግጥ በዘመነ-ሕወሓት/ኢሕአዴግ የአገሪቱን አንጡራ መሬት ለሱዳን በድብቅ ሲሰጥ የተፈራረመውን ይሁን፤ እራሱ በተነኮሰው ጦርነት ድባቅ ለተመታው የሸዓብያ መንግሥት በትግራይና በአፋር የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙትን መሬቶች ለጦር-አጫሪው ክፍል አሣልፎ የሰጠውን ስመ-ጥፉ የአልጀርስ ስምምነት ተተርጉመው ሕዝብ እንዲወያይባቸው ያላደረገ ኃይል ስለሆነ ድርጊቱ አዲስ አይደለም ሊባል ይችል ይሆናል። ሆኖም ሊታለፍ የማይገባው ስህተት ነው። በዚኽ ጉዳይ ትችት የማቀርበው በእንግዚዝኛ ቋንቋ ከወጣው ላይ ያሉትን ነጥቦች በማየት እንደሆነ ይታወቅልኝ። ይኽ አሁን ተገኘ የተባለ የ“ስምምነት” መግለጫ በሁለንተናዊ መልኩ በቅድሚያ ግብፅን ቀጥሎም ሱዳንን ከባለቤትነት ያልተናነሰ መብት የሚሰጥ፤ በአንፃሩ ግን ኢትዮጵያን ያላስፍላጊ ግዴታዎች ውስጥ የሚያስገባ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። በመሠረቱ በአገሮች መካከል ድንበር-ዘለል ወንዝ አጠቃቀምን በተመለከተም ይሁን ሌሎች ችግሮችን በስምምነትና በጋራ-ጥቅም ላይ በተመሠረተ መግባባት መፍታት ምን-ጊዜም ቅድሚያ የሚሰጠውና የሚመረጥ መንገድ ነው። የድንበር-ዘለል ወንዞችን ውሃ ወንዞቹ የሚመነጩበት (የሚነሱበት) አገር ብቻ እንደፈለገው የሚጠቀምበትና ሌሎች የወንዙ-ተፋሰስ (ወንዙ ድንበራቸውን አቋርጦ የሚያልፍባቸው) አገሮችም በውሃው ላይ የመጠቀም መብት እንዳላቸው ግልጥ ነው። በዚኽም መሠረት በብዙ አገሮች መኻል ከ3600 ያላነሱ ውሎችና ስምምነቶች እንደተደረጉ ይታወቃል። በመሆኑም ይኽ ስምምነትም በዚያው መንፈስና መርኅ መሠረት የተደረገ ነው የሚል ክርክር ሊቀርብ ይችላል። ሆኖም 3 በተለይ ግብፅና ሱዳንን የመሰሉ ቀደም-ሲል አብዛኛውን የወንዙን ውሃ በበላይነት ለመጠቀም ብቻ ሣይሆን ለመቆጣጠር የሚያስችል ውል አለን ብለው ድርቅ ያለ አቋም የያዙና ያንንም መሠረታዊ አቋም መተውአቸውን በይፋ ያረጋገጡበት አንዳችም መረጃ በሌለበት ሁኔታ፣ ዓባይን የሚያክል በታሪክ የተመዘገበ የአገርን ኅልውና የሚፈታተንና የቆየ ውስብስብ ችግር ያለበት ከባድ ጉዳይ ባለቤት የሆነው ሕዝብ ሳይመክርበትና ያለ-መግባባቱ መሠረት በቅጡ ሳይጤን የሚደረግ ስምምነት በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። የዓባይን ውሃ አጠቃቀም በተመለከተ ከግብፅና ከሱዳን ጋር የነበረው/ያለው ችግር ሁለቱ አገሮች (በተለይ ግብፅ) ባለቤት ከሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይበልጥ የባለቤትነት “ታሪካዊ መብት” አለንና ይኽ ይከበር፣ አልፎም ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ምንም ዓይነት የልማት እቅድ ለማድረግና ተፈጥሮ የለገሣትን የውሃ ሃብት ለመጠቀም በቅድሚያ የእነሱን በጎ-ፈቃድና ይሁንታ ማግኘት አለባት የሚል የትምክኅት አቋም ማራመዳቸው ሲሆን፣ ይኽ ደግሞ መሠረታዊ በሆነ መልኩ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መብትና አገራዊ ነፃነት የሚጥስ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ የማንንም ጎረቤት ጥቅም ተጋፍታ የማታውቅና እንዲያውም ምናልባት ከኬንያ በስተቀር ከቦረቤቶቿ በኩል ያልተቋረጡ ጥቃቶች ሰልባ ሆና የቆየች አገር መሆኗ ግልጥ ነው። ይኽን ስምምነት የምንቃዎም ወገኖች የዓባይ ውሃን አጠቃቀም በተመለከተ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ብዙ ትሥሥር ያላቸውን የግብፅና የሱዳንን ሕዝቦች ያላስፈላጊ ችግር ውስጥ የሚያስባ ስምምነት መደረግ አለበት ከሚል ፍርደ-ገምድል አስተሣሰብ በመነሣት ሣይሆን፤ ከእነኚህ አገሮች ጋር የሚደረግ ማንኛውም ድርድር፣ በነፃ ለሚጠቀሙበት የውሃ ሃብት ተመጣጣኝ ክፍያ ወይም ሚዛናዊ ካሣ የሚያስገኝ ይሁን ባይባልም፣ ቢያንስ ቢያንስ ቢያንስ ይኽንን ኢትዮጵያ እንኳን ልትገዛበት መቼም ቢሆን ተቀብላው የማታውቀውን የእነሱን አጉልኛ ‘የመብት’ ጥያቄ ዳግም በማይነሣበት መልክ ውሳኔ የሚያስገኝ ስምምነት ሊሆን ይገባል ከሚል ነው። የተቃውሞዬ መንሻም ይኽ አሁን በአቶ ኃይለ-ማርያም ደሣለኝ ፊርማ ተደረገ የተባለው ‘በመርኅ ላይ የተመሠረተ ስምምነት’ ይኽንን የሁለቱ አገሮች በተለይም የግብፅን የቆየ አቋም የሚቀይር ሣይሆን ባርኮ የሚሰጥ ሆኖ ስላገኘሁት ነው። ለመሆኑ የኢሕአዴግ መሪዎች ይኽንን ውል ‘በመርኅ ላይ የተመሠረተ ስምምነት’ ነው ሲሉ የትኛውን መርኅ ነው መሠረት አደረገ የሚሉት? ግብፅ አበክራ “ታሪካዊ መብቴ” ነው የምትለውን የተዛባ የጥቅም-ማስከበር መርኅ? በአጎራባች አገሮች መኻል መኖር ስለሚገባው የድንበር- ዘለል ወንዞች አጠቃቀም መርኅ? ደካሞች በተለያዩ ምክንያቶች ተገድደው መቀበል ስላለባቸው ጫና- የወለደው የተንበርካኪ የስምምነት መርኅ-አልባ መርኅ? የቱ ነው? ከቻሉ መውለክለክ የሌለበት ቀጥተኛ መልስ ቢሰጡ መልካም ነበር፤ ግዴታም አለባቸው። ማንኛውም ድርድር የችግሩን መንስዔ ሊፈታ ካልቻለ እና ይደርሣል ተብሎ የሚሰጋበት ምናልባታዊ መዘዝ በማንኛውም ዓይነት ጫና ተገድዶ ከሚደረግ ስምምነት ይበልጥ ዘለቄታዊና ስትራቴጂያዊ ጉዳት የሚያስከትል ከሆነ፤ ሊደርስ ይችል ይሆናል የሚባለውን ስጋት በክብር መቀበሉ የተሻለ ይሆናል። በእርግጥ በተለይ ግብፆች ኅዳሴ ግድቡ ጨርሶ እንዳይሠራ ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ደጅ ያልጠኑት መንግሥትና ያልተማጸኗቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፤ በአደባባይ ከማስፈራራት፣ ከመፎከርና ከመጎፍላት ጀምሮ፣ ከቀድሞ ባለ-ሥልጣናት ምሑር እስከተባሉት ድረስ ያሉ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማንቀሣቀስ ተቃውሟቸው በአገራቸው ሕዝብ ዘንድ ብቻ ሣይሆን ዓለም-አቀፍ ድጋፍ እንዲያገኝና በኢትዮጵያ ላይ ጫና ያሣድራል ብለው ያሰቡትን ማንኛውንም ዘዴ ሁሉ ለመጠቀም ያልተቆጠበ ጥረት አድርገዋል። ሁኔታዎች በመቀየራቸው ግን ያ ሁሉ ጥረት ያሰቡትን ግብ ሊመታላቸውና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የግንባታ እቅድ ከመቀጠል ሊያስቆሙ አልቻሉም። ታዲያ ሁኔታው ያ ሆኖ እያለ የኢሕአዴግ መሪዎች አሁን ባለው አካባቢያዊና ዓለም-አቀፋዊ ሁኔታ በዚኽ ጊዜ ይኽንን የመሰለ የተዛባ ስምምነት ለማድረግ ምን አስገደዳቸው? ለምንስ ከዓመት ወይም ከዚያ በፊት ማድረግ አልቻሉም/አልፈለጉም? ወይም ግብፆች በዚኽ ስምምነት ላይ ቀደም-ሲል ሊቀበሉት ያልቻሉትና በአሁኑ ጊዜ የተቀበሉት/የተቀበሏቸው ነጥብ/ነጥቦች አለ/አሉ የሚባል ከሆነ የቱ/የትኞቹ ነው/ናቸው? ከሆነስ ለምን? ለሚሉት ጥያቄዎች የኢሕአዴግ ቁንጮዎች አጥጋቢ ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል። 4 ምናልባት ከኢሕአዴጋውያን በኩል በግብዝ ድፍረት ‘ይኸው ግብፅኮ ሳትወድ በግድ የኅዳሴ ግድቡን አምና ተቀበለች’ ሊሉ እንደሚከጅሉ አልጠራጠርም። በበኩሌ በግብፅ በኩል ይኽንን ‘ስምምነት’ ለመፈረም ቀደም ሲል ካራመደችው መሠረታዊ አቋም የተቀየረ አንድም ነገር የለም። ግድቡ እንዳይሠራ አጥብቃ የገረገረችውና ኢትዮጵያ አንድነቷ የተጠበቀ ጠንካራ አገር እንዳትሆን ዝንታለም ስትገዘግዛት የኖረችው ከዓባይ ውሃ ‘ታሪካዊ ድርሻየ’ የምትለው ጥቅም እንዳይነካባት በመፈለግ እንደሆነ ግልጥ ነው። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ የግድቡን ግንባታ ለማስቆም የማታቸንፈው ጦርነት ውስጥም ሳትገባ፣ ይገባኛል የምትለውን በአሃዝ ያልተተመነ የውሃ መጠን ማግኘት የሚያስችል ብቻ ሣይሆን ምንም ዓይነት ይኽ ነው የሚባል ወጭና ድካም ሣይኖርባት ከግድቡ የሚገኙ ተዛማች ጥቅሞችን ሊያረጋግጥ በሚችል ውሎች የታሰረ ስምምነት ተንበርክኮ የሚሰጥ ተደራዳሪ ሲገኝ ፈንድቃ የማትቀበልበት ምክንያት የለም። ይኽ አደገኛ ውል የሚያደርገው ያንን ነውና። ከዚኽ የክህደት ውል ሱዳን ድርብ ተጠቃሚ ናት ማለት የቻላል። በአንድ በኩል የኅዳሴ ግድቡን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ወግና በመቆሟ (*2) ለጊዜው ስትራቴጂያዊ አጋሯ ከሆነችው ግብፅ ጋር የነበረውን መፈራቀቅ በዚኽ ስምምነት ሣቢያ ተመልሰው እንዲገጥሙ ሲያስችል፣ እዚያው-በዚያው ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ፈርጀ-ብዙ የጥቅም ትሥሥር እንደተጠበቀ እንዲቀጥል አስችሏታል። የኅዳሴ ግድቡን በመደገፍ ከሦስት ዓመታት በፊት በተጻፈውና በድጋሚ በግንቦት ፪ ሽህ ፭ ዓ/ም በወጣው ጽሑፍ ላይ በሰጠሁት አስተያየት እንዳመላከትኩት እቅዱን በተመለከተ ከነበሩኝ ስጋቶች መኻል አንዱ በተለይ ግብፆች በወቅቱ በነበረባቸው (አሁንም ድረስ ባልፈቷቸው) የውስጥ ችግሮቻቸው እና ቀደም- ሲል ያለ-የሌለ ጫናቸውን በኢትዮጵያ ላይ ለማሣደርና ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ይጠቀሙባቸው የነበሩ ለእነሱ ያጋደሉ የአካባቢና ዓለም-አቀፍ ሁኔታዎች አመቺ አለመሆናቸውን፣ እቅዱን ለማስቆም ቀጥተኛ የኃይል ጥቃት ለመፈጸም የሚያስችል የተመቻቸ ሁኔታም ሆነ ይኽ ነው የሚባል ወታደራዊ ቀመር እንደሌለ በመገንዘብ፤ ሁኔታዎች እስኪቀየሩ ድረስ በትርጉም-የለሽ ድርድር ስም የግድቡን ሥራ ማጓተትና ማዘግየት የተሻለ ምርጫ አድርገው እንደሚወስዱ በመገመት፤ በኢትዮጵያ በኩል አንድም የግድቡን ሥራ በተቻለ-መጠን ማፋጠንና መመለስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ማድረስ፣ ይኽ እየተደረገም የዓባይን የውሃ ሃብት ፍትኃዊ በሆነ መልክ በጋራ ለመጠቀም እንዲስያችል ታስቦ በናይል ኢኒሺየቲቭ አማካይነት ‘የዓባይ ወንዝ ጠገግ የመተባበሪያ ማእቀፈ-ግብር ስምምነት’(Agreement on the Nile Basin Cooperative Framework) በሚል ርዕስ በወንዙ ተፋሰስ አገሮች የተደረሰበትን አዲስ የውል ስምምነት (ከግብፅና ከሱዳን በስተቀር ያሉት የዓባይ-ተፋሰስ አገሮች የፈረሙትን) ሁለቱ አገሮች እንዲፈርሙ የሚቻለውን ጥረት ማድረጉን መቀጠል እንደሚያስፈልግ፤ ግብፆች የዓባይን ጉዳይ በደፈናው የኅልውና ጥያቄ አድርገው ስለሚያዩትና በተለይ ለውስጥ ፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የአገሪቱ ፖለቲከኞች ሕዝብን ለማነሣሣት ታስቦ ለሚደረግ ቅስቀሣ አመቺ በመሆኑ አጉል መደናገጥ አንዳይኖር፤ በተዘዋዋሪ በሚውጠነጠኑና ከላይ ቅን መስለው ሊታዩና ኢትዮጵያን ጠልፈው ሊጥሉ በሚችሉ የግብፅ መሠሪ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች መዘናጋት እንደይኖርና መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ አሳስቤ ነበር። ብዙ ወገኖች ለመሆኑ የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት መሪዎች በኢትዮጵያ ስም ይኽንን ከክህደት ያልተናነሰ፣ ብሔራዊ ጥቅምንም ሉዓላዊነትንም ደርቦ አሳልፎ የሚሰጥ ስምምነት እንዲያደርጉ ምን አስገዳጅ ሁኔታ ገጠማቸው? የሚል ቁጭትን ያዘለ የአግራሞት ጥያቄ ማቅረባቸው አይቀርም። መቸም ገና በሽግግር-መንግሥት ስም እያለ ያለ-ምንም ዓይነት ሕጋዊና ታሪካዊ መሠረት አገሪቱ ከሁለት እንድትከፈል ከማድረግ ጀምሮ የሸዓብያ እብሪተኛ መሪዎች በተነኮሱት ጦርነት በተባበረ የኢትዮጵያውያን ክንድ ድባቅ ከተመቱ በኋላ በስመ-ጥፉው ይግባኝ-የለሽ የአልጀርስ ስምምነት በትግራይና በአፋር ግዛቶች የሚገኙ መሬቶችን ለተቸናፊው ክፍል ለሽንፈቱ ማካካሻ ይመስል ገጸ-በረከት የሚያቀርብ፣ ዝንታለም የኢትዮጵያ ይዞታ ሆነው የቆዩ የአገሪቱን አንጡራ መሬቶች እንደግል ጥሪቱ እየቆረሰ ለሱዳን አሣልፎ የሚሰጥ፣ የራሱ ዜጎች በአገራቸው ከሚኖሩበት ቤታቸው ድንበር ተሻግረው በመጡ የሱዳን የባዕድ ጦር ታፍነው ሱዳን ተወስደው እንደ-ወንጀለኛ ለእስር ሲዳረጉ እና ቤት ንብረታቸው ሲዘረፍና ሲቃጠል እንኳን የመቆርቆር ስሜት እንዲያውም “አንድም የተፈናቀለ ገበሬ የለም”፤ አልፎም ለሱዳን ጥብቅና በመቆም ስለ ሱዳን ‘ታጋሽንት’ና ኢትዮጵያ ያለ-አግባብ መሬታቸውን ስለመያዛ ፓርላማ ፊት ሕዝብን-በናቀ ያልተገራ አንደበት የሚቀጥፍ፣ ዜጎች በአረመኔ የአረብ ዋልጌዎችና በመንግሥት ሰብዓዊ-መብቶቻቸውና ክብራቸው 5 ሲረገጥ፣ ዘግናኝ ግፍ ሲፈጸምባቸውና ላባቸውን አንጠፍጥፈውና ሰብዕናቸውን አዋርደው የቋጠሯትን ሣይቀር ተቀምተው እንደ ከብት ታፍሰው ሲባረሩ ምንም ነገር እንዳልሆነ በዝምታ ያለፈ፣ ለባዕዳን ጥቅም ሲባል ዜጎችን በማፈናቀልና በራሣቸው አገር ለእነዚሁ ባዕዳን ተቀጣሪና ሎሌ እንዲሆኑ የሚያደርግ ብሔራዊ- ውርደት ያከናነቡ እርምጃዎችን ሲወስድ የቆየ አገዛዝ በመሆኑ ይኽ አሁን ከግብፅና ከሱዳን ጋር የተፈጸመ ስምምነትም ለብዙዎች አዲስ ሆኖ ላይታይ ይችላል። ሆኖም እነዚያ በታሪክም በሕግም ፊት በኃላፊነት የሚያስጠይቁ እርምጃዎች ይኽንን እንዳናይ ወይም በዝምታ እንድናልፍ አያደርግም። ለዚኽ ‘ስምምነት’ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ቢችሉም የግድቡን ሥራ ለማስቀጠል የገንዘብ አቅም ችግር በዋናነት ሊጠቀስ የሚችል ይመስለኛል። ይኽ ችግር እንደሚያጋጥም ደግሞ በተለይ የግድቡን መሠራት የምንደግፍ ወግኖች ከስጋቶቻችን አንዱ እንደሆነና መፍትኄ ይሆናሉ የተባሉትን ጭምር ሳንጠቅስም፣ ሳናሳስብም አላለፍንም። ሆኖም የአገሪቱን ጉዳይ ሁሉ በአንድ ጠባብ ድርጅታዊ እይታና ወልጋዳ መነፅር ከማየት የማይወጣው ገዢ ክፍል ይኽንንም የዓባይ ግድብ እቅድ ከብሔራዊነት ባኅሪው አውርዶ የግል ድርጅታዊ ጉዳይ አድርጎ በመመልከት፣ ሁሉንም ነገር ከሥልጣን ዕድሜው መራዘም ጋር በማያያዝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገሩ ደኅንነትና ዕድገት ያለውን ጉጉትና መጠን-የለሽ በጎ-ፈቃድ በአጉልኛ ለመጠቀም ከማሰብ ውጪ በውጭም በውስጥም ያለው ኢትዮጵያዊ አመኔታ ኖሮት ገንዘብ በማዋጣት ይሁን በሌላ ረገድ ሙሉ የዜግነት ተሣትፎ እንዲያደርግ ዘወትር ከሚቀርቡ የሕዝብ ጥያቄያዎች መኽል በግፍ የታሰሩ ንፁኃን ዜጎችን እንኳን ለመልቀቅ ፈቃደኝነትም ይሁን የፖለቲካ ድፍረት ሊያሣይ አልቻለም። መቸም ቢሆን ኃላፊነት የሚሰማው የአገር አመራር የተቀየመና ያኮረፈ ሕዝብ ይዞ ከባዕዳን ጋር ጦርነትም ሆነ ድርድር ለማድረግ አይከጅልም። ምክንያቱም በሌላው በኩል የሚሰለፈው ክፍል የተፃራሪውን አቅም የሚለካበት አንዱ የሕዝብ ድጋፍ ደረጃ መሆኑ የታወቀ ነውና። በአገዛዙ መሪዎች አርቆ-ያላዬ ግትር አቋም ምክንያት ጋባዥ ሁኔታዎች ባለመመቻቸታቸው በተለይ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በአንድ ላይ ሊያቆም የሚችለውን የዓባይ ጥያቄ ላይ በሚያሣዝን መልኩ በርካታ ወገኖችን እንዲያመነቱና በኅዳሴው ግድብ ግንባታ ዙሪያ የሚፈልጉትንና የሚጠበቅባቸውን ያኽል ትኩስ ተሣትፎ ለማድረግ አልቻሉም። ያም በመሆኑ፣ ምሑሩም፣ ሙያተኛውም ሌላውም አገር-ወዳድ ኢትዮጵያዊ እራሱ ሊያደርግ ከሚችለው በላይ በገንዘብም ሆነ በተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ መስኮች ሊረዱ የሚችሉ የውጭው ማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ የተቀናበረ ዘምቻ ለማድረግ አልተቻለውም። ያ ደግሞ የኅዳሴውን ግድብ የራሱ ዜጎች በስፋት እንደተቃዎሙት የሚያደርግ የተሣሣተ መልዕክት ሣያስተላልፍ አልቀረም። ይኽም በተራው ኢትዮጵያን ሊረዱት የሚችሉት ክፍሎች እርዳታ ከመስጠት እንዲቆጠቡ፣ ቢያንስ እንዲያመነቱና አልፎም በተለይ የአረቡ ዓለም ድጋፍ ያልተለያት ግብፅ ግድቡን በመቃዎም ለምታደርገው ዘመቻ ያገዘና ኢትዮጵያ ላይ ተዘዋዋሪ ጫና-አሣዳሪ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ማበረታታቱ ከግምት ውጭ አይመስለኝም። በዚኽ ምክንያት የአገዛዙ መሪዎች ለግድቡ ማሠሪያ ብድር ይሰጡናል ብለው የተማመኑባቸው አንዳንድ ክፍሎች ፊታቸውን ቢያዞሩ አይገርመኝም። ግትር አድራጎታቸው ችግር እንደሚያመጣና ይኽ ክፍተት መዘዝ እንደሚኖረው ግን የአገዛዙ መሪዎች ሊገነዝቡ የቻሉ አይመስለኝም። በሚከተሉት አራት ዋና-ዋና ምክንያቶች ይኽ የሦስትዮሽ ስምምነት ኢትዮጵያን ይጎዳል የሚል እምነት አለኝ። እነሱም:- 1ኛ. የኢትዮጵያን ነባር የጠና አቋም ስለሚሽር፤ እንደሚታወቀው ግብፅና ሱዳን ኢትዮጵያንም ሆነ ሌሎች የዓባይ-ተፋሰስ አገሮችን ባገለለ ሁኔታ የጥቁርና ነጭ ዓባይ ወንዞችን የውሃ ሃብት አካፋይም-ተካፋይም፣ ሰጭም-ነሽም እንዲሆኑ የተፈጣጠሟቸውን እነዚያ ውሎች ሁሉም አሜን ብሎ ተቀብሎ እንዲያከብርላቸው የቻሉትን ሙከራ ሁሉ ቢያደርጉም፣ ኃላፊነት የሚሰማቸውና ከምንም-እና-ከማንም በላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር የሚያንገበግባቸው ተከታታይ የኢትዮጵያ ባለ-ሥልጣናት ያንን ተገቢ የሆነ ነባር የእምቢታ አቋም አንዴም ዝነፍ ሣይሉ እንዲቀጥል በማድረጋቸው፤ አሁን በአገራችን የተጀመረውን የኅዳሴ ግድብ ለማስቆም በተለይ ግብፅ ቢያንስ 6 ጉዳዩን ወደ-ፍርድ ሸንጎ ደፍራ ለማቅረብ እንዳትችል አንድ ትልቅ እንቅፋት እንደሆነባት መገመት አያዳግትም። ይኽ ‘ስምምነት’ ግን በጥቅሉ ሲታይ በአብዛኛው የ1929 እና የ1959 ውሎችን በተለይም የ1959ን ውል መሠረት በማድረግ ግብፅና ሱዳን በዓባይ ውሃ ላይ አለን የሚሉትን ‘የመብት’ ጥያቄ እስካሁን የነበሩ የኢትዮጵያ መንግሥታት ጨርሶ አለመቀበል ብቻ ሣይሆን ጉዳዩ በተነሳበት አጋጣሚና መድረክ ሁሉ ኢትዮጵያ በምንም መልኩ እውቅና እንደማትሰጥ አጥብቀው ሲያስገነዝቡና አበክረው ሲከራከሩ የቆዩትን መሠረታዊ ነባር አቋም የሚቀይር ነው። 2ኛ. የኢትዮጵያን መብቶች የተፃረረና ሉዓላዊነቷን አሣልፎ የሰጠ በመሆኑ፤ ሀ. በዚኽ ውል ተራ ቁጥር 2 ‘የልማት፣ የአካባቢ ጥምረት እና የቀጣይነት መተክሎች’ በሚለው ሥር ‘የታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ዓላማ የኃይል ማመንጫ ነው’ ብሎ ያስረዋል። የግድቡ ይፋ ዓላማ የኃይል ማመንጫ መሆኑ ላይ ጥያቄ አይኖርም። የሁለቱ አገሮች በተለይ የግብፅ ሥጋት ኢትዮጵያ የዓባይን ውሃ ለመስኖ ትጠቀማለች የሚልና ጥረቷም ይኽን እንደምንም ማስቆም ስለሆነ፣ ይኽ አንቀፅ መቅረቡ አስፈላጊ ባልሆነ ነበር። ምክንያቱም፣ አንደኛ ዓላማው ባይባልም ግልጥ ነው። ሁለተኛ ግድቡ ከኃይል ማመንጫነት በተጨማሪ ለአሣ እርባታ ይሁን ለሌሎች ተዛማች አገልግሎቶች መዋል ስለሚችልም፣ ስለሚገባም፤ እንዲሁም የዓባይ ወንዝ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚነሱ አያሌ መጋቢ ወንዞችን ያቀፈ ስለሆነ፣ እነ ግብፅ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን በመሠራት ላይ ያሉም ሆነ ለወደፊቱ በእቅድ የተያዙ የመስኖ ግድቦች ላይ ችግር ለመፍጠር ይኽንን ውል በመጥቀስ ለአተካራ በር ሊከፍት ስለሚችል የውሉ አባባል በተቀመጠበት መልክ መሆን ካለበት ከዚኹ ጋር ተያይዞ እነዚኽን ማድረግ እንደሚቻል የሚጠቅስ አንቀጽ ቢኖር መልካም ነበር። ይኽንን በዋና-መርኅ ሥር መቀበል ማለት ኢትዮጵያ ግድቡ ሊሰጥ ከሚችለው የኃይል- አመንጭነት ውጭ ግብፅና ሱዳን እንደሚገለገሉባቸው በጥምር-አገልግሎት-ሰጪነት (ለኃይል ማመንጫና ለመስኖ) እንዳትጠቀም ከወዲሁ የሚከለክል ነው። ግብፅም ሆነች ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር መደራደር የሚገባቸው ቢጠና ሊደርሣቸው ስለሚችል የውሃ መጠን እንጂ ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን በአገሯ ክልል ውስጥ ለምን አገልግሎት መጠቀም እንደምትችል የሚፈቅድና እንዳትችል የሚከለክል ሊሆን ፈጽሞ ፈጽሞ ተቀባይነት ሊኖረው ቀርቶ ለድርድር ሊቀርብ የማይገባው ጉዳይ ነው። ለ. የፍትዊና ሚዛናዊ አጠቃቀም መርኅ ሥር የተጠቀሱ ውሎች: አንደኛ ‘ሦስቱም አገሮች የውሃ ድርሻቸውን በአገሮቻቸው ውስጥ አጥጋቢ ምክንያት ባለው/በአሳማኝ መንገድና ፍትኃዊ/ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ይጠቀማሉ’ ይላል። ይኽ አንቀጽ ተግባር ላይ ሲውል ስሌት ውስጥ መግባት የሚኖርባቸውን ሁኔታዎች ቀጥሎ ባሉት ዘጠኝ ዝርዝሮች ውስጥ ሲያስቀምጥ:- ‘የየአገሮቹ ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ ፍላጎት፤ በውሃው ላይ ጥገኛ የሆነ ሕዝብ ያለበትን አገር ሁኔታ፣ አንዱ አገር የሚኖረው የውሃ አጠቃቀም በሌላው አገር ላይ ሊያደርስ ስለሚችለው/ስለሚፈጥረው ተጽዕኖ፤ በአሁኑ ጊዜ ላሉና ወደፊም ለሚኖሩ ጥቃሞቶች የሚውለው የውሃ ይዞታ፤ አገልግሎት ላይ ያሉም ይሁን ለወደፊት እቅድ የተያዘላቸውን በተመለከተ ሊኖር ስለሚችል አማራጭ ወይም ተመጣጣኝ ምትክ፤ እያንዳንዱ አገር የሚኖረው የውሃ አስተዋጽዖ፣ የእያንዳንዱ አገር ፍሳሽ የሚሸፍነው ልክና መጠን... ’ ይላል። እንግዲህ ከእነዚኽ ሁኔታዎች ውስጥ ማን ምን እንደሚጠበቅበትና ማን ወጥመድ ውስጥ እንደገባ ግልጥ ይመስለኛል። ግብፅ የዓባይን ውሃ አሁን ከምትገለገልበት አልፎ ደረቅ የሰሃራ በረሃዋን ለማልማት ሠፊ እቅድ እንዳላት እየታወቀ፣ የእያንዳንዱ አገር የውሃ ድርሻ መጠን በአሃዛዊ መለኪያ ሣይገመትና በእሱም ላይ ስምምነት ሳይደረግ፣ የውሃው አጠቃቀም አሁን ባለው እንኳን ሣይገደብ ለወደፊት ለተያዙ እቅዶች በሚፈቅድበት፣ ወዘተ.. እንዲሁ በደፈናው - ‘ሦስቱም አገሮች የሕዝባቸው ፍላጎት የሚጠይቀውንና ለልማታቸው የሚያስፈልገውን የውሃ ድርሻቸውን በአገሮቻቸው ውስጥ ይጠቀማሉ...’ የሚል ውል እንዴት ተደርጎ ነው በኢትዮጵያ ላይ የሚጫነው? የዚኽ ትርጉሙ ሌላ ሣይሆን ግብፅ የ1929 እና የ1959 ውሎች ሰጥተውኛል የምትላቸውን ‘ታሪካዊ የውሃ ድርሻ መብቶች’ ኢትዮጵያ በጓዳ በር እንደተቀበለችላት የሚያስቆጥር ነው። በዚኽ ስምምነት ውስጥ አንድም ቦታ ላይ እነዚኽ ያረጁና ተቀባይነት የሌላቸውን ውሎች የሚሽር ወይም ኢትዮጵያ እንደማትቀበላቸውና እንደማትገዛባቸው በግልጥና በማያሻማ ሁኔታ የተጠቀሰ ነገር ስለሌለ ግብፆች ያንን ትርጉም ቢይዙ ያስኬዳቸው ይመስለኛል። 7 በተመሣሣይ ሁኔታ አንቀጽ አራት ዋናውን ዓባይ (የእኛውን ጥቁር ዓባይ) አጠቃቀም በተመለከተ አንዱ አገር በሌላው ላይ ‘አዬል-ያለ ጉዳት እንዳያደርስ አግባብነት ያላቸው ጥንቃቄዎች ማድረግ አለበት’ ይላል። በመቀጠልም ጉዳት ከደረሰ ግን ‘ለእንደዚህ ዓይነት አደጋ አስቀድሞ የተደረገ ስምምነት ከሌለ ጉዳት ያደረሰው አገር ችግሩን ለማስወገድ ከመጣር ባሻገር ጉዳቱ ከደረሰበት አገር ጋር በመመካከርና በመነጋገር ለደረሰው ጉዳት ካሣ መክፈልን በተመለከተ ሊወያዩ ይችላሉ’ ይላል። በተለይ ኢትዮጵያን ከመተናኮል የማትቆጠበው ግብፅ፣ በሆነ-ባልሆነ ምክንያት በሚፈጠር ችግር ኢትዮጵያን ቀስፎ ለመያዝ ካልሆነ በስተቀር፣ አሁንም እንደገና ይኽ አቀራረብ ግብፅን ለሱዳንና ለኢትዮጵያ፣ ሱዳንን ለኢትዮጵያ ተጠያቂ ማድረግ የማይችል ኢትዮጵያን ግን ለሁለቱም ተጠያቂ የሚያደርግና ዓላማውም ይኽው እንደሆነ ግልጥ ነው። ይባስ ተብሎ በአንቀጽ አምስት ላይ የሠፈረው ውል ሉዓላዊነት ደኅና-ሰንብች የሚል የባርነት ውል ነው ማለት እችላለሁ። በጥሬው ሲቀርብ የኅዳሴ ግድቡን ለመሙላት ብቻ ሣይሆን ኢትዮጵያ የግድቡን ገቢራዊ- ሥራና አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ስለምትከተላቸው ዓመታዊ መመሪያዎችና ደንቦች ለግብፅና ለሱዳን ለማሣወቅ (ዘገባ ለማቅረብ) ተስማምተናል ይላል። በሌላ አነጋገር የግድቡ የውስጥ አሠራርና አካሄድ የእነሱን ፈቃድና ይሁንታ በመቀበል ነው መቀጠል የሚችለው ማለት ነው። እንዲሁም አንቀጽ ስድስት ሥር የተጠቀሱት ውሎች ውስጥ ኢትዮጵያ ከኅዳሴ ግድብ የምታመርተውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለውጭ-አገሮች ስትሽጥ ‘ቅድሚያ ለሁለቱ አገሮች መሆን አለበት’ ይላል። ባይሆን ኢትዮጵያ ለሌሎች አገሮች በምትሸጥበት ተመጣጣኝ ዋጋ ቢል እንኳን ሊያስኬድ ይችል ነበር። ለመሆኑ በየትኛው የገበያ ሕግ እና በአቻ ተደራዳሪዎች መኻል በሚደረግ ውል ነው አንድ አገር እንዲህ ዓይነት የውዴታ ግዳጅን መቀበል የሚጠየቀው? ያሣዝናል። ይኽ ውሽልሽል ውል የመሬት-ውስጥ የውሃ ሃብቷን ሳትነካ ደረቅ በረሃዋን ለማልማት የረጅም-ጊዜ እቅድ ያላት ግብፅ ‘ለሕዝቤ ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ እድገት ያስፈልገኛል’ በሚል ቀደም-ሲል የተጠቀሱትን ውሎች ከዚኽኛው ጋር በማዳመር ከዓባይ ውሃ ‘ድርሻዬ’ ነው የምትለው እንዳይጓደልባት የመጠየቅና ያንንም ለማስከበር የምትችለውን ሁሉ ለማድረግ እንድትችል ሕጋዊ መንገድ ይሰጣል ባይ ነኝ። 3ኛ. ከ1999 ጀምሮ በተቋቋመው የዓባይ-ተፋሰስ-አገሮች የጋራ የትብብር መድረክ አባላት መኻል ክፍተት አንዲኖርና የትብብሩን መንፈስ ሊበርዝ፤ ግብፅና ሱዳንን (በተለይም ግብፅን) ብቻቸውን ተነጥለው እንዲቀሩ ያስቻለውን ዲፕሎማሲያዊ ግኝት የሚሸረሽር በመሆኑ፤ የግድቡን መሠራት ስደግፍ በተለይ ወቅቱ ለኢትዮጵያ አመቺ ነው የሚል ነበር። እንደሚታወቀው፣ ምንም-እንኳ የዓባይ-ተፋሰስ-አገሮች በርካታ ቢሆኑም፤ በአገራችን በኩል ከአሁን በፊት የዓባይን የውሃ ሃብት ለመጠቀም የተደረጉ ያላሰለሱ ጥረቶችንም ሆነ ያልተቋረጡ ፍላጎቶችን በመጻረር ከቆሙ ብቻ ሣይሆን እራሣቸውን እንደ ብቸኛ ባለቤት በማድረግ ከሚቆጥሩ ግብፅና ሱዳን (ቀደም ሲልም የዓባይን ውሃ ከምንጩ ለመቆጣጠር ምኞት ከነበራት የእነዚኹ አገሮች ቅኝ-ገዥ ከነበረችው እንግሊዝ) ጋር የተደረጉ እልህ- አስጨራሽ ውዝግቦችንና ፍልሚያዎችን በብቸኝነት ስትጋፈጥ የኖረችው ኢትዮጵያችን ነበረች። ያ ደግሞ እነዚኽ አገሮች ጥረቶቿን ለማሰናከል ከጠቀሟቸው ምክንያቶች አንዱ ሆኖ መቆየቱ ግልጥ ነው። ቀደም-ሲል በ1929 ግብፅና እንግሊዝ መኻል ብቻ ከዚያም በ1959 ከግብፅና ከሱዳን በስተቀር ሌሎቹን የዓባይ-ተፋሰስ አገሮች ባልጨመረና ባላወቁት ሁኔታ በቅኝ-ገዥዋ እንግሊዝ ችሮታ የተደረጉትን መሠሪ ውሎች በማጣቀስ በዓባይ ውሃ ላይ እራሣቸውን እንደ-ባለቤት መቁጠር ብቻ ሣይሆን የላዕላይ-ተፋሰስ (የምንጩ ባለቤት የሆኑት አገሮች) ያለ-እነሱ ፈቃድ በወንዞቹ ላይ ምንም ዓይነት የግንባታ ሥራ እንዳይሠሩ የአጋጅ-አስገዳጅ መብት አለን በማለት ሲከራከሩም፣ ሲፎክሩና ሲያስፈራሩ መቆየታቸው ይታወቃል። ሆኖም የዓባይን የውሃ ሃብት በእኩል ለመጠቀምና የጥቁርና የነጭ ዓባይ ወንዞችን በጋራ ለማልማት፣ ከልማቱም የሚገኘውን ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ ግኝት በጋራ ለመጠቀም ዘጠኝ አገሮች በ1999 ዓ/ም እ.አ.አ. የዓባይ ጠገግ አብሪ-እርምጃ (የናይል ቤዚን ኢኒሺዬቲቭ) በሚል የምክክር መድረክ ማቋቋም በመቻላቸው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ አገራችን የዓባይን ጉዳይ በተመለከተ ከባላንጣዎቿ ጋር በሚደረግ ውዝግብ ሁሉ ብቻዋን ከመቆም ተገላግላለች። የዚኽን ስብስብ መፈጠር ተከትሎ የጋራ-ትብብር የስምምነት ምኅዳረ-መርኅ {The Cooperative Framework Agreement (CFA)} በሚል ስያሜ የስምምነት ውል ላይ የቀሩት አገሮች ሲፈርሙ፣ ግብፅና ሱዳን ‘ታሪካዊ 8 መብታችንን’ ይጋፋብናል በሚል ምክንያት ተቃውሞ በማቅረብ ውሉን ሳይፈርሙ መቅረታቸው ይታወቃል። የሁለቱ አገሮች ተቃውሞ በዚኽ ውል አንቀጽ 14 ቢ ላይ ‘በማንኛውም የዓባይ ተፋሰስ አገር የውሃ ዋስትና ላይ አዬል-ያለ ችግር እንዳይደርስ ለማረጋገጥ አባል አገሮች በጋራ ይሠራሉ።’ (member countries would work together to ensure "not to significantly affect the water security of any other Nile Basin State.)" የሚል ሲሆን፤ ግብፅና ሱዳን ግን ይኽ ‘አዬል-ባለ ሁኔታ ጉዳት እንዳይደርስ’ የሚለው አባባል ‘በውሃ ዋስትናው ላይና በአሁኑ ጊዜ ጥቅም በመስጠት ላይ ባሉት ላይ ተፃራሪ/አሉታዊ ችግር እንዳይደርስ...’ ("Not to adversely affect the water security and current uses") በሚል እንዲተካ አጥብቀው ያቀረቡት ጥያቄ በሌሎቹ ዘንድ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ነበር። ሁለቱ አገሮች ይኽ እንዲለወጥ የፈለጉበት ምክንያት ግልጥ ነው። ይኸውም ግብፅና ሱዳን ከሁለቱ በስተቀር ሌሎቹ የዓባይ-ተፋሰስ አገሮች በምንም መንገድ የ1929 እና የ1959 ኢ-ፍትኃዊና አድልዖአዊ ውሎችን ተቀብለው ላለመቀጠል ቁርጠኛ ውሳኔ ማድረጋቸውን በመረዳታቸውና አዲሱ የስምምነት ውልም እነዚያን እስከነአካቴው እንደሚሽርና ያንን ከተቀበሉ ደግሞ ‘ታሪካዊ መብት’ የሚሉትን አጉል መከራከሪያ እንደሚያሳጣቸው በተገቢ በመገንዘባቸው ነበር። በዚኽ አዲስ የምሥራቅ አፍሪቃውያን የጋራ ግንባር ስምምነት ምክንያትም የ1929 እና የ1959 ውሎች ፍትኃዊ እንዳልሆኑ፣ በቀጣይም ገዥነት እንደሌላቸውና ተቀባይነትም እንድማይኖራችው በተግባር የሻረ ውል እነደሆነ በማያሻማ መንገድ ማሳወቅ የቻለ የዲፕሎማሲ በጎ-ግኝት ግብፅና ሱዳን ከቀሩት የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ተነጥለው እንዲቀሩና ሌሎቹ በአንድ ግንባር መሰልፍ በመቻላቸው የኢትዮጵያን የጉዳዩ ብቸኛ ተፋላሚ ከመሆን አድኗል። ግብፅና ሱዳን የኅዳሴ ግድቡን እቅድ ለማስቀረትም ሆነ ለማሰናከል ትልቅ ደንቃራ የሆነባቸውና ያላስቻላቸው አንዱ ምክንያት ይኽ የቀሩት የዓባይ ተፋሰስ-አገሮች አንድ ላይ መቆም መቻላቸው ነው። ሁለቱ አገሮች ይኽንን የአፍሪቃውያን አዲስ ግንባር ለማፍረስ ስላልተቻላቸው፣ እነዚኽ አገሮች በጋራ የተስማሙባቸውን ስምምነቶች አንፈርምም ቢሉም ውላ-አድራ ለመጀመሪያ ጊዜ ሱዳን ከግብፅ ተለይታ ከኢትዮጵያ ጎን መቆም ችላለች። ምንም እንኳን የዓባይን ግድብ በተመለከተ ሱዳን ከግብፅ ተለይታ ከኢትዮጵያ ጎን መሠለፍ እንድትችል የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ቢችሉም፤ ለኢትዮጵያ ቀላል የውጭ-ግንኙነት (የዲፕሎማሲ) ድል አልነበረም። ያም-ሆኖ ግን ሱዳንም እንኳ ያንን ውል ሣትፈርም ነው የቆየችው። ኢትዮጵያ ከሁለቱ አገሮች ጋር በተናጠል ይኽን ስምምነት ከማድረጓ በፊት የጋራ ስብስቡ ያወጣውንና ሌሎቹ የተስማሙበትን ሆኖም ሁለቱ አገሮች እስካሁን አሻፈርን ያሉትን ሰነድ በቅድሚያ ተቀብለው እንዲፈርሙ ማድረግ በተገባ ነበር። ሁለቱ አገሮች (ግብፅና ሱዳን) እነዚያ የቅኝ-ግዛት ዘመን ውሎች ያጎናጸፏቸውን መብቶች በተግባር የሻረውን ‘የናይል ኢንሺየቲቭ’ ስምምነት ምንም አዲስ ውል ከመደረጉ በፊት እንዲፈርሙ አለመደረጉ ለሁለቱ አገሮች በተለይም ለግብፅ ድርብርብ ድልን ይለግሳል። ምንም እንኳ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ስብስብ አሁን በሦስቱ አገሮች የተፈጸመውን ስምምነት ደግፎ መግለጫ ቢያወጣም፣ አዲሱ ስምምነት በጋራ ስብስቡ ቀጥተኛ ማእቀፍ ሥር ሣይሆን ከሌሎቹ የአባይ-ተፋሰስ አገሮች ተለይቶ መደረጉ፣ አንደኛ ለሁለቱ አገሮች ከእያንዳንዱ የዓባይ ተፋሰስ አገር ጋር የተናጠል ውል ለመዋዋል በር ይከፍትላቸዋል። ያም ማለት የዓባይን ውሃ አጠቃቀም በተመለከተ ሁሉም የወንዞቹ ተፋሰስ አገሮች በጋራ እንደ-አንድ አካል ሆነው እንዳይሠሩና ሁሉም በመሰለው ከመሰለው ጋር የየግሉን ውል እንዲፈጽም መንገድ ይሰጣል። የዚያ ዓይነቱ አካሄድ በተለይ ለግብፅ ትልቅ ድል መሆኑ አጠራጣሪ አይመስለኝም። ሁለተኛ በዚኽ አዲስ ‘ስምምነት’ ላይ ታሪካዊ መብቶቻችን የሚሏቸውን በተመለከተ ሕጋዊ መከራከሪያ አድርገው የሚጠቅሷቸውን እነዚያኑ የጥንት ስምምነቶች አሁንም በመከራከሪያነት ለማቅረብ የሚያግዳቸው በግልጥ የተቀመጠ ማሰሪያ ባለመኖሩ ነባር መከራከሪያቸውን ለመግፋት ያስችላቸዋል። በዚኽም ረገድ ይኽ ውል- ተብዬ ጉድ አስጠቂ ነው እላለሁ። 4ኛ. ለግብፅና ሱዳን በጥቅም-ላይ-ጥቅም የሚሰጥ፣ ለኢትዮጵያ ዙሪያ-ጥምጥም ግዴታ የሚያሸክም በመሆኑ፤ በዚኽ መርኅ-አልባ ስምምነት ውስጥ ኢትዮጵያ እንድታደርጋቸው የሚጠበቁባትን ግዴታዎች እንጂ ሱዳንና ግብፅ ሊያደርጉ ይገባል የሚል ወይም ኢትዮጵያን ሊጠቅም ወይም ቢያንስ ወደፊት ሊጎዳት 9 ይችላል ተብሎ እንዲያደርጉም ሆነ እንዳያደርጉ የሚጠይቅ አስገዳጅነት ያለው ነገር የለም። በአንጻሩ ግን በተለይ ለግብፅ ሙሉ ስትራቴጂያዊ ድልን ያጎናጸፈና ሚዛናዊነት የጎደለው ውል ነው። የአገዛዙ ሰዎች ገፋ-ቢል ምናልባት ‘ይኽው ግብፅና ሱዳንማ የኢትዮጵያ የኅዳሴ ግድብን ተቀበለዋል’ የሚል እርባና-ቢስ ክርክር ሊያነሱ ይችሉ ይሆናል። ዞሮ-ዞሮ ይኽ ‘ስምምነት’ ከአሁን በፊት ሁለቱ አገሮች (ግብፅና ሱዳን) በብዙ ረገድ እነዚያን ኢትዮጵያ አሻፈረኝ ብላ እውቅና ላለመስጠት ስትታገላቸው የቆዩትንና እነሱም ዝንታለም እንደተመኙት የ1929 እና የ1959 ውሎችን የቀን አብሪ የሌት ተመሪ በሆኑ የኢሕአዴግ መሪዎች አማካይነት በጓዳ-በር ገብተው እነሆ በተዘዋዋሪ ተቀባይነት እንዲያገኙ ሆኖላቸዋል። ያም በመሆኑ ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ በዓባይ ውሃ ላይ ይዛው የቆየችውንና በጦር-ሜዳ ጭምር ብዙ መስዋዕትነትን ባስከፈሉ ፍልሚያዎች አስከብራው የኖረችውን የባለቤትነት መብት ቢያንስ እንዲሸረሸር በመደረጉ አገራችንን አስፈላጊ ወዳልሆነ ተከላካይ ደረጃ የሚያወርድና ለቀጣይ ውዝግብ የሚዳርግ ነው ማለት ይቻላል። የአገዛዙ መሪዎች ይኽንን ‘ስምምነት’ ወደው ሲፈርሙ በተለይ ሌት-ተቀን ሃያ-አራት ሰዓት ያለ- ማቋረጥ ደፋ-ቀና የሚሉ ከልዩ-ልዩ ሙያተኛና መሐንዲስ እስከ ተራ-ሠራተኛ ያሉ ዜጎች፣ ይኽ ብሔራዊ እቅድ እንዳይሣካ የሚፈልጉ ክፍሎች የሚያደርጉትን ዘርፈ-ብዙ ዘመቻ ለመቋቋምና የኢትዮጵያን ፍላጎት ለማስረዳትና የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ያለ-መታከት የደከሙና እየደከሙ ያሉ በሁሉም የዲፕሎማሲ መስክና ደረጃ ያሉ ወገኖች፣ በባዕዳን ሰርጎ-ገቦችም ይሁን በአገር-በቀል ተላላኪዎች መተናኮል የግድቡ ግንባታ እንዳይደናቀፍና በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ፀጥታ በማስከበር ሥራ ላይ የተሰማሩ የጦሩና የፀጥታው ክፍል አባላት፣ በአጠቃላይ ለዚኽ ብሔራዊ እቅድ በንጹህ የአገር ፍቅር ስሜት ተነሣስተው አቅሙ የፈቀደላቸው ብቻ ሣይሆኑ እናቶች ከመቀነቶቻቸው ሣይቀር የቋጠሯትን እየፈቱ ያላቸውን ገንዘብ ለኅዳሴው ግድብ ያበረከቱ ዜጎች፣ በአጠቃላይ ግድቡ ሲጠናቀቅ ከሚሰጠው ቁሣዊ ጥቅም የበለጠ አገራችን ሉዓላዊ መብቶቿ ሣይሸራረፉ ክብሯን ጠብቃ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር እንደምትችል የእቅዱን መጠናቅቅ በጉጉት የሚጠብቀው ሠፊው ሕዝብ ምን ይሰማቸው ይሆን ብለው እራሣቸውን አለመጠየቃቸው የሚገርም ነው። ይኽን ስምምነት ከማድረጋቸው በፊት ቢያንስ የድሮ ዲፕሎማቶች ማኅበርን በጉዳዩ ላይ ሙያዊ ምክር ቢጠይቁ መልካም በሆነ ነበር። ይኸንን ነው እነ አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ ‘በመርኅ ላይ የተመሠረተ ስምምነት’ የሚሉት። አገሪቱ በምን ዓይነት የራሣቸውን ሕዝብ በናቁ ግብዞች ሥር እንደወደቀች ከዚኽ የበለጠ ማረጋገጫ ያለ አይመስለኝም። በዓለም-አቀፍ መድረኮች ሁሉ ተከብረው አገራቸውን ያስከበሩ መሪዎች፣ በተደማጭ ሰብዕናቸውና ርቱዕ አንደበታቸው ኢትዮጵያን ለማዋረድ የሞከሩትን ሁሉ አፍ ሲያዘጉ የነበሩ ዲፕሎማቶች የነበሯት ኢትዮጵያ ይኽንን የመሰለ አዋራጅ ስምምነት ለመዋዋል ለነ ግብፅ የሚንበረከኩ ሰዎች ላይ መውደቋ በእርግጥም ያሣፍራል። ይኽ ስምምነት በአጠቃላይ ሲታይ በዜጎቿ ጥሪትና ድካም የሚገነባው ግድብ፣ የተፈጥሮ ሃብቷ በሆነው የዓባይ ውሃዋ የሚያስገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ግብፅና ሱዳንን ተጠቃሚ ማድረግ ብቻ ሣይሆን ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ለእነሱ አስገዳጅ ውሎች ተገዥ የሚያደርግ ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበትን ነፃነት የሚጋፋና የሕዝቧን ሉዓላዊ መብቶች የሚጥስ ስምምነት በምንም መልኩ ኢትዮጵያ እንኳን ልትቀበለውና ልትገዛበት ልታስተናግደውም አያስፈልግ። ምን ይደረግ? 1. የዓባይ ጉዳይ የማይቆጨውም ሆነ የማያገባው ኢትዮጵያዊ አይኖርም። በርካታ አገር-ወዳድ ምሑራን የኅዳሴ ግድቡን በመደገፍ ቢደረግ ይበጃል ያሉትን አሳብ አቅርበዋል። እኔም ታላቁን የኅዳሴ ግድብ በመደገፍ ባወጣሁት ጽሑፍ ላይ እንዳስገነዘብኩትና ከዚያም በኋላ ለማሳሰብ እንደሞከርኩት፣ የዓባይ ጉዳይ ለአገዛዙ ቁንጮዎች የሚተውም ሆነ በተናጠል የሚገፋ ስላልሆነ፣ የግድቡን ሥራ ትኩረት ሰጥቶ በቅርብ የሚከታተል ከልዩ-ልዩ የኅብረተሰባችን ክፍሎች የተውጣጣ፣ በተለይም ሙያተኞችን ያቀፈ፣ አንድ ጠንካራ የኢትዮጵያውያን ‘የዓባይ መብት አስጠባቂ’ አካል ሊቋቋም ይገባል። አሁንም ቢሆን በጥብቅ ሊታሰብበት ብቻ ሣይሆን በቶሎ ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል የሚል አሳብ በትህትና አቀርባለሁ። በዚኽ አካል 10 አማካይነትም ይኽንን የክህደት ስምምነት በመቃዎም በሚሊዮኖች የሚቆጠር የኢትዮጵያውያን ፊርማ ማሰባሰብ ያስፈልጋል። እንዲሁም በአገር-ውስጥም ሆነ ከአገር-ውጪ ኢትዮጵያውያን በተቀነባበረና ዓለም-አቀፍ ይዘት ባለው መልክ በልዩ-ልዩ መንገዶች ተቃውሞአቸውን ማሣየት ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም:- ሀ). በአንድ በኩል በግድቡ ግንባታና በልዩ-ልዩ ተዛማጅ ሥራዎች ላይ የተሠማሩ ወገኖች በዚኽ ጎጂ ስምምነት ምክንያት ተስፋ-በመቁረጥ ሳይዘናጉ በኢትዮጵያዊ ወኔና በቁጭት በየተሠለፉበት መስክ ሥራቸውን ተግተው ከመሥራት እንዳይቆጠቡ፤ ለ). በተመሣሣይ ሁኔታ የጦር-ኃይሉና የፀጥታው ክፍሎችም በአገርና በመንግሥት መኻል ያለውን ልዩነት እሳቤ ውስጥ በማስገባት ብሔራዊ ተልዕኳቸውን ከመወጣት እንዳይዘናጉ፤ ሐ). ምንም እንኳ በአሁኑ ውቅት ያለው የአገሪቱ ሕዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት በገዥው ፓርቲ ደጋፊዎች የተሞላና የእሱን ፈቃድ ከመፈጸም ውጭ ሊያደርግ አይችልም የሚል ስጋት ቢኖርም፤ በአገሪቱ ላይ በሚሠራው ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55 ቁጥር 20 መሠረት ከውጭ-አገሮች ጋር የሚደረጉ ውሎችና ስምምነቶችን የማጽደቅ ሥልጣንና ኃላፊነት ያለው የዚኽ አካል አባላት፣ አንደኛ ስምምነት ተብሎ የተፈረመው ሰነድ አካሉ እራሱ በሚሰይማቸውና በሕዝብ ዘንድ ተኣማኒነት ባላቸው ገለልተኛ ሙያተኞች ተተርጉሞ እንዲቀርብና ይፋ ውይይት እንዲደረግበት፤ ሁለተኛ በዚኽ ዓብይ ጉዳይ ላይ በሚወሰድ ውሳኔ አካሉ እንደ-አካል ብቻ ሣይሆን እያንዳንዱ ተወካይ ሙሉ የታሪክ ተጠያቂ እንደሚሆን በጽሥፍ ማሳሰብ ያስፈልግ ይመስለኛል። 2. አገራችን ለዚኽ የወረደ ደረጃ መድረስ ዋናውን ድርሻ አሁን ያለው የሕወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ የሚሸከም መሆኑ ቢታወቅም፤ በተቃዋሚው በኩል የተሰለፈው (በተለይም ለፍትኅና ለኩልነት የቆመው የአንድነት ኃይል) ኃላፊነት የለውም ማለት አይቻልም። ቅጥ-አንባሩ በጠፋ የኃይል አሠላለፍ የሚውለከለከውና ውድ ጊዜውን የአገዛዙን ጥፋቶች በመዘገብና በማውገዝ፣ እርስ-በርስ በመጠላለፍና በመናከስ የሚያባክነው ለውጥ-ፈላጊ አገር-ወዳድና ዴሞክራት ኃይል አገርና ሕዝብን ባስቀደመ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መሠረት ላይ በቆመ መርኅ የሕዝብ አመኔታና አክብሮት የሚቸረው ሁነኛ ብሔራዊ- አማራጭ ሆኖ መቅረብ አስካልቻለ ድረስ የጥፋት ሂደቱም ሆነ የሕዝባችን ስቃይ ከመቀጠል፣ በዚያውም እንደ አገዛዙ ተጠያቂ ከመሆን ማምለጥ አይቻለውም። ስለሆነም፣ በልዩ-ልዩ ጊዜዎች በበርካታ ወገኖች ሲጠየቅ እንደቆየው ሁሉ አሁንም ለሃቀኛ ለውጥ የሚታገለው በአገር-ውስጥ ያለው ኃይል ለየግል የሥራ- ዋስተና ከመሆን በማይዘልና አስቀድሞ ውጤቱ በተወሰነ የምርጫ ጨዋታ ውስጥ ገብቶ ከመዳከርና እርስ- በርስ ከመናከስ ወጥቶ የጋራ አሠላለፍ እንዲይዝ፤ በተመሣሣይ ሁኔታ ከአገር-ውጭ ያለውም እንዲሁ ማድረግ እንዳለበት ተገንዝቦ ቢያደርግ አስፈላጊ ይሆናል እላለሁ። ድንቄም በመርኅ ላይ የተመሠረተ ስምምነት! “ሸክም የማይከብደው ሕዝብ” አሉ ትልቁ ሰው ክቡር ኮሎኔል አስናቀ እንግዳ! የኢትዮጵያ እድገት ብሔራዊ ክብሯና ነፃነቷ እንደተከበሩ እውን ይሆናል!! ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!! (*1) በአሁኑ-ጊዜ በሥራ ላይ ባለው የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ሣይሆን የሥራ ቋንቋ አማርኛ እንደሆነ በአንቀጽ 6 ተገልጿል። (*2) ሱዳን የኅዳሴ ግድቡን በተመለከተ ከኢትዮጵያ የወገነችው አንዱ ምክንያት ስትመኝ የኖረችውን የኢትዮጵያ አንጡራ መሬት በለጋሶቹ የሕወሓት/ኢሕአዴግ አውራዎች -፧እነ መለስ ዜናዊና በተባባሪ ጀሌዎቻቸው -በእነ ደመቀ መኮንን በጎ-ፈቃድ በገፀ-በከተትነት ስለተሰጣት እንደሆነ ይገመታል።  

No comments:

Post a Comment