Thursday, February 12, 2015



ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ - በፖለቲካና ሙስና የጎበጠው ተቋም

(ዮናስ መብራህቱ)

ሀገር በትውልድ ትገነባለች፡፡ ትምህርት ደግሞ ትውልድን ይገነባል፡፡ ለዚህም ነው - Education is one of the most important agents of socialization!!! የሚባለው፡፡ ስለዚህም ነው ተቋማዊ ነጸነት ያለው፣ ጥራቱን የጠበቀ እና በከፍተኛ ሞራላዊ አስተምህሮት የተመሰረተ ትምህርትና የትምህርት ስርዓት ለአንዲት ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ነው የሚባለው፡፡ከዚህ መርህ አንጻር በኢትዮጵያም የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ህገ-መንግሰት ትምህርት በማናቸውም ረገድ ከሀይማኖት፣ከፖለቲካ አመለካከቶች እና ከባሕላዊ ተጽዕኖዎች ነጻ በሆነ መንገድ መካሄድ አለበት የሚለው (90(2)፡፡ ሌሎች ህጎችም ለምሳሌ የከፍተኛ ትምህርት ዓዋጅ (650(2001)) ተቋማዊ ነጸነት ከተጠያቂነት ጋር ማረጋገጥ የዓዋጅ ዋነኛ ዓላማ እንደሆነ በማያሻማ መልኩ ያሰቀመጣል፡፡

ህግ ማውጣት እንጂ መሬት ላይ ጠብ የሚል ነገር የለም፡፡ በተለይ የማንነት ፖለቲካን መሰርት ያደረገውን የፌደራሊዝም ስርዓት መምጣትን ተከትሎ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አደረጃጀትና አመራር ከብሔር ተዋጽኦና ፉክክር ጋር በከፍተኛ ደረጃ ተቆራኝቷል፡፡የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፌደራል መስርያ ቤት መሆናቸው ቀርቶ በክልልና በከተማ አሰተዳደር አመራሮችና ካድሬዎች እንደሚተዳደሩ ያደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ከሞላ ጎደል ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች በሚባል ደረጃ የብሔር ፖለቲካ ስሌት ሰለባዎች እንደሆኑ ቢታወቅም ላለፉት ስድስት ዓመታት በመምህርነት ያገለገለኩበት ድሬዳዋ ዩንቨርስቲ ግን በተለዬ ሁኔታ ዓይን ያወጣና በብሔር ፖለቲካ የነቀዘ ተቋም ነው ብል ማጋነን አይመስለኝም፡፡ የዩንቨርስቲው ችግር የድሬዳዋ አስተዳደር የማንነት ፖለቲካ ችግር ነጸብራቅ በመሆኑ በአስተዳደሩ ያለው የኦህዴድ እና ሶህዴፓ( የሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ) የይገባኛል ወዝግብ በተቋሙ ውስጥም በጉልህ ይንጸባረቃል፡፡ድሬዳዋ ዩንቨርስቲ በ 1999 .ም በዓወጅ ሲቋቋም ከሀሮማያ ዩኒቨርስቲ የተላለፈ ስለነብር ከሌሎች አዳዲስ ዩንቨርስቲዎች የተሻለ መሰረት ነበረው፡፡ ነገር ግን በሙስናና በመልካም አስተዳደር ችግር እግር ተወርች ተጠፍሮ፣ተቋማው ነጸነት እርም ሁኖበት፣ተማሪዎችን፣መምህራን እንዲሁማ ሌሎች የግቢው ማህበረሰብ አባለትን እያስመረረ ላለፉት 9 ዓመታት እየዳሀ ይገኛል፡፡ ሙስናና የብሔር ፖለተካ ተቋምን አበስብሰውታል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ዓዋጅ ፕሬዝዳንቶችና ምክትል ፕሬዝዳንቶች በይፋ ተወዳዳሪዎች ተጋበዘው የተሻለ ብቃትና ዝግጁነት ያለው ተመርጦ በቦረድ ይሾማል ብሎ ቢደነግግም ውድድርና በቃት ምንም ቦታ ስለሌላችው አንድም ቀን ተግባራዊ ሁኖ አያውቅም፡፡ ለምሳሌ ከ1999 እስክ 2006 በነበረው የፓርቲዎች አሰላለፍ ሶህዴፓ የአስተዳደርና ቢዝነስ ጉዳዮች ምክትለ ፕሬዝዳነትነትና ኮታ ያለተቀናቃኝ ስለተሰጠው የፓርቲው የማዓከላው ኮሚቴው አባል የነበረችውን የእውቀት ባዳ ተሿሚ ወ/ሮ ኡባህ አደም ካድሬ አምጥቶ ፍዳችንን ሲያሳይን ነበር፡፡ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕራዝዳንትነትን የኦህዴድ ስለነበር የብሔር መታወቅያወንና የፓርቲ አባልነቱን ብቻ በማየት ያለምን ውድድር ዶ/ር ፍቃዱ ለሜሳ የተባለ አንድ ንጹህ (ከእወቀትና ብቃት ማለቴ ነው) ሰው ግቢውን ሲያስተዳድር ነበር።፡እነዚህ ተሿሚዎች ቢሮ ጉዳይ ባግባቡ አያሰተናገዱም ነበር፤ ብዙ ግዜም ለፓርቲ ስብሳባ ስለሚሄዱ ሜሮን ጌትነት እንዳለችው ወንበሩ ባዶ ነበር። ይባስ ብለው በስሮቻቸው የሚገኙ አመራሮችም በብሔርና በፖለቲካ መዋቅር ውስጥ ስላስገቧችው በብቃትና በውድድር መመረጥ እንዲሁም ተጠያቂነትና ሀለፊነት አይጎበኛቸውም፡፡ አሁንም ድረስ የሚገርመኝ የሶህዴፓ ተሿሚ ለትምህርት ወደውጭ ስለተላከች ፓርቲው ሰው እስኪያገኝ ተብሎ የአስተዳደርና ቢዝነስ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳነትነትና ቦታ ከ 2005 .ም እሰከ ጥር 2006 .ም ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ባዶ ስለነበር ስራ ሲበደልና ባለጉዳይ ሲጉላላ ማንም ምንም አለማለቱ ነው፡፡ እንድ ተራ የሶዴፓ ካድሬ ድንገት ተገናኝተን ስናወራ ለምክትል ፕሬዘዳነትነት ቦታ ሰው እየመረጡ እንደሆነና እንደሚሾሙልን ሲነግረኝ በጣም ነበር ያመመኝ፡፡ለአንድ የተማረ ማህበረሰብ ይገኝበታል ተብሎ የሚገመት ዩኒቨርስቲ አንድ ተራ ካድሬ አመራሩን ሲሾምለት ከማየት የባሰ ተቋማዊ ንቅዘት የት ማግኘት ይቻላል?

አመራሮች እንዲለወጡ፣ የመምህራን ማህበር እንዲቋቋም በተደጋጋሚ ለዩኒቨርስቲው ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪ አካል - የዩኒቨርስቲው ቦርድ - ቢጠየቅም በፓርቲዎቹ ፉክክር ምክንያት ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ይመልሰን ነበር፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ፉክክሩ ጡዘት ሲያይልና የፖለቲካ አስፈጻሚነታችወ ላይም ድክመት ስላሳዩ በራሱ ግዜ አነሳችው፡፡ በ2006 .ም ተግባራዊ የሆነው ከብሔር ፖለቲካ ያልወጣው ያመራር ለውጥም አሁንም ብቃትና ልምድ በኢትዮጵያ ባይተዋር እንደሆኑ ማሳያ ነው፡፡ በአዲሱ አሰላለፍ ኦህዴድ በለስ ቀንቶት የፕሬዝዳነትነት ቦታ ለዶ/ር ግርማ ጎሩ ሲያሰረከብ ሶህዴፓ የለመደውን የምክትል ፕሬዝዳነትነት ቦታ በ ዶ/ር መሀዲ ኢጌ በኩል ተረክቧል፡፡ ቀሪው የምክትል ፕሬዝዳነትነት ቦታ ለብአዴን ኢህአዴግ እጣ ወጥቶለታል፡፡ ተቋማዊ ነጸነት ይልኋል እንግዲህ ይህ ነው፡፡ በቦርዱና በፓርቲዎቹ መሃል ባለ የፖለተካ ሸኩቻና ስምምነት የሚሾሙ የብቃትና የእውቀት መሀን ካድሬዎች ዩኒቨርስቲውን ስለሚያሾሩት ለዶክትሬት እና


ሌሎች ትምህርቶች ወደ አዲስ አበባና ሌሎች አገሮቸ የሚሄዱ መምህራን ወይ በዛው የዉሃ ሽታ ሁነው ይቀራሉ አልያም ወደ ዩኒቨርስቲው ላለመመለስ ትምህርታቸውን ያራዛማሉ፡፡
ስለ ዪኒቨርስቲ ከተወራ ስለ ፓርቲ ክንፍ (part wings) አለማውራት ይከበዳል፡፡ ከፕሬዝዳንት እስከ ዝቅተኛ አመራር በፓርቲ ሰዎች መያዙ አልበቃ ብሎ የፓርቲ ክንፍ ተብለው ከኢህአዴግ(ኦህዴድ፣ብአዴንና ህዉሀት) እና ከ ሶህዴፓ ተወክለው በግቢው ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ በዓይነ ቁራኛ የሚከታተሉ እንደአስፈላጊነቱም የተለያየ እርምጃ የሚወስዱ አስፈሪ የፖለቲካ ካድሬዎች ናቸው ፡፡ እርግጥ ነው በመንግስት ንብረት ወይም በህዝብ ሀበት የፓርቲ ስራ መስራት ነውርም ህገ-ወጥም ነው፡፡በመንግስትና በፓርቲ ህልውና ያለው ልዩነት ያልገባው ቢገባውም ለመርህ ግድ የሌለው የኢህአዴግ መንግስት ግን ለፓርቲ ክንፍ አባላት ሙሉ ወጪያቸውን ከህዝበ ሀበት ሸፍኖ ከፍተኛ የመኪና እጥረት ባለበት ግቢ የተለያዩ መኪናዎች ታዞላቸው በግቢው ውስጥ ካደራጇቸው የመምህራንና የተማሪዎች የህዋስ አባላት ጋር በመሆን ቀን ከለሊት ተማሪዎቸንና መምህራንን እየሰለሉ በክፍል ሳይቀር ማን ምን ተናገር እየተባለ ስጋትና ጭንቀት ውስጥ የሚከቱ ናቸው፡፡ አልፎ አልፎም በፓርቲ ስራ ምክንያት ፈተና ያመለጠው ወይም አሳይመንተ ያላሟላ ተማሪ ካለ በከንቲባው ጸ/ቤት አድርጎ በፕሬዝዳነት ያልፍና ድጋሚ እንድትፈትን ወይም ውጤት እንድታስተካክል ትዕዛዝ ይመጣል፡፡ የዚህ ስርዓት ዉጤት የሆነው ተማሪም በስራውና በውጤቱ የሚተማመን ስላለልሆነ በብአዴን ወይም በህወሀት ስም ፈተና ወረቀት ላይ በመጻፍ የሚማጸኑ እንዳሉ የዪኒቨረስቲው የቦርድ ሰብሳቢ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስተር ደኤታ አቶ ሙሉጌታ ስጦታው በመስከረሙ የመምህረን የፖለቲካ ስብሰባ በአደባባይ የተናገሩት ነው፡፡በፓርቲዉ ዉስጥ ባለው የህዋስ አደረጃጀትና ተሳትፎ በሚሰጠው ዉጤት የሚመጻደቅና አስተማሪውን የሚያመናጭቅ እንዲያ ሲልም ለድብድብ የሚጋበዝ ትውልድ እያፈራን ነው - ምስጋና ለኢህአዴግ ስርዓት!!!

በቅርቡ ደግሞ ከቀጣይ ግንቦት ምርጫ ጋር በተያያዘ ባሉት አመራሮች ላይ እምነት ያጣው መንግስት በዩኒቨርስቲ ውስጥ ያሉት የት/ት ክፍል ዲኖችና ዳይሬክተሮች በአመነባቸው አመራሮች የመቀየር ስራ ተያይዞታል፡፡ በነጻ ውድድር ተወዳደሩ ቢልም ለውድድር የቀረበዉ መስፈርቶች ግን በዋነኝነት ፖለቲካዊ አመለካከቶችን መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ለማንምና ለምንም ግልጽ ያልሆኑ ልማታዊና ዲሞክራሲያው አስተሳሰቦች መላበስና በተቋሙ እንዲሰፍን ማድረግ፣የኢህአዴግ ፖሊሲና ስትራተጂ ለመተግበር ያለው ራዕይ የመሳሰሉት ዋነኞቹ መስፈርቶች ነበሩ፡፡ የምርጫ ሂደቱን ያየን እንደሆነም ተወዳዳሪዎች ዕቅዶቻቸውን ለአወዳዳሪዎች በንግግር ሲያቀረቡ ሶሶት የፓርቲ ክንፍ አባላት እንዲታዘቡና እንዲገመግሙ የተደረገ ሲሆን የግምገማዉን ውጤት ከ 50% ውጤቱን ለሚሞሉት ፕሬዝዳንቶች ሀሳብ በማቅረብ (recommend) በማድረግ እነሱ የፈለጉት እንዲመረጥ ተደርጓል፡፡ ስለዚህ ዪኒቨርሰቲ ውስጥ የሚካሄደውን ምርጫ በተመለከት የሚያሰጋው ነገር አይኖርም ምክንያቱመ ምርጫውን (ምርጫ የሚባል ካለ) ለማጭበርበር የሚያስችል ስራ ተሰርቷል፡፡

ሙስና ሌላው ሀይ ባይ ያጣ ጉዳይ ነው፡፡ በ1997 .ም የተጀመሩ በርካት ህንጸዎች አመራሮቹ ከኮንትራከተሮችና የህንጻ ተቋራጮች ጋር እየተሞዳሞዱና እየተመሳጠሩ እንደአስፈላጊነቱም ኮንትራከተሮችን እያቀያይሩ ከ 10 ዓመት በላይ ተጓተዋል፡፡ የዩኒቨርስተዉ የቀዱሞ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር ወጋየሁ በቀለ በህንጻ ተቋራጮ ጨረት በቀጥታ እንደሚሳተፉና የገቢው Enginering unit (የህንጻ ጉዳይ ተቆጣጣሪ አካል ነው) የጣለው ኮንተራክተር በፕሬዝዳንቱ እንዲያሸንፍ እንደሚደረግ ቢታወቅም አንድም ቀን ተጣርቶ አያውቅም (ከዩኒቭርስቲው ፊትለፊት ባለ 2 ፎቅ የሙአለ ህጻናት ፕሬዝዳንቱ እንዳሰራ ተጨማሪ መረጃ ብሰጣችሁስ)፡፡ ተጠናቀው ዩኒቨርስቲው የሚረከባቸው ህንጸዎችም ቢሆኑ ጥራታችወ የተጓደለና ብዙም ሳይቆዩ የሚሰነጣጠቁ፣መጸዳጃና ሌሎች ፋሲሊቲ ያልተሟላላቸው ስለሆኑ ተማሪዎችም አስተማሪዎችም በምሬት የሚናገሯቸው ናቸው፡፡ እንደውም ባንድ ወቅት ደረጃ የሌለው ህንጻ ተሰርቶ ደብረ ዳሞ ህንጻ የሚል ስም ተሰጥቶት ነበር(ደብረ ዳሞ ገዳም በገመድ እንደሚወጣ ልብ ይሏል)፡፡

በተደጋጋሚ ከምግብ ጥራትና አቅርቦት ችግር ጋር በተያያዘ በግቢው ውስጥ ለሚነሱ እሰከ መስታዎት መስበር የሚደርስ የተማሪዎች ዓመጽመንስዔዎቹ በምግብ አቅርቦት ጨረታና ግዢ የሚፈጸሙ ሙስናዎች ናቸው፡፡ የመንግስት ንብረት አስተዳደርና የጨረታ ህግን ያልተከተሉ ጨረታና ግዢ ስለሚካሄዱ ለተማሪዎች የሚቀርበው ምግብ ጥራቱ ያልጠበቀና በመጠንም አነስተኛ ከመሆኑ ባሻገር ተማሪዎችን ለተለያዩ በሽታዎች ያጋልጣቸዋል፡፡ ለምሳሌ እንድ እኔ በቅርበት የማዎቀው በ2006 .ም መስከረም አካባቢ ለተማሪዎች ምግብ የማቅረብ ጨረታ እሰከ 100 ሽሕ ብር የሚገመት ገንዘብ ለመዝረፍ ተብሎ የሕክምናና ሌሎች በሕጉና በጨረታው የተቀመጡ መስፈርቶች ያላሟላና ከሁሉም ተጫራቾች በላይ ዋጋ ያቀረበ ድርጅት እንዲያሸንፍ በመደረጉ ተሸናፊው ድርጅት ለጸረ-ሙስና ኮሚሽን አመልክቶ ኮሚሽኑ ምርመራውን ጀምሮ ነበረ፡፡ነግር ግን የዩኒቨርስቲው አመራሮች ከኮሚሸኑ ጋር ተደራድረው ሙሰኞችን በተቋሙ የዲሲፕሊን ኮሚቴ እንዲቀጡ ተወሰነ፡፡ ወንጀል የሆነውን ጉዳይ በዚህ መንገድ መቀይር እንደማይቻል ቢታወቀም ፣እኔ የነበርኩበት የዲስፕሊን ኮሚቴ ከተከሳሾችና ሌሎች ምስክሮች ተገቢውን ምርመራ አካሂደን ለቅጣት በምንዘጋጅበት ግዜ ከተቋሙ አመራሮች በመጣ ትዕዛዝ እንዲቋረጥ ተደረገ፡፡ሙሰኞችም እንኳን ሊቀጡና ማስተማርያ ሊሆኑ ወንጀላቸውን ላማድበስበስ ወደ ተሻለ ስልጣን ተቀየሩ፡፡

እኔም በዚህና በሌሎች ጉዳዮች ለምን ብዬ ስለጠየኩኝ ሚያዝያ 1 ቀን 2006 .ም በፕሬዝዳንቱ በተጸፈ ደብዳቤ ከኮሚቴው እንድባረርና ማስጠንቀቅያም እንዲሰጠኝ ተደረገ፡፡

በአጠቃላይ በሌሎችም የከፍተኛ ት/ት ተቋማት ያለው ነግር ተመሳሳይ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት የት/ት ስርዓትና ሂደት በኢትዮጵያ ምን ዓይነት ትውልድ እየፈራ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፣በመጨረሻም ለዚህ ስርዓት ባለስልጣናት መጽሐፍ ቅዱሰ መጽኀፈ ምሳሌ ላይ ባለ አንድ ጥቅስ አንድ ጥያቄ ልጠይቃቸው፣- እናንተ ብስለት የሌላችሁ፣ ማስተዋል የሌለበት መንገዳችሁን እስከ መቼ ትወዱታላችሁ?


ዮናስ መብራህቱ ከጀርመን
write2yoni@yahoo.com
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com



February 5, 2015

No comments:

Post a Comment