ይቺ ናት ጨዋታ!
ዳኛው ያለ ፊሽካ ጨዋታ አስጀመረ፤
የመሀሉ አጥቂ አታሎ በረረ፤
በረጅሙ መታ... ወደ ጎል ሞከረ፤
ወይኔ! ፎሪ ወጣች...ማንም አለነበረ።
በረኛው ኳስ ሳይዝ...ሳያነጥር ለጋ፤
ለግራ ከንፍ ደርሶት...ጣለበት አደጋ።
ግን ለጥቂት ሳተ...አዎን በአናት ወጣች፤
እሪ ብሎ ጮኸ...ደጋፊ ተመልካች።
አጥቂ፤ ተከላካይ ...ግብ ጠባቂው ፈዞ፤
አይቶ መቀባበል...የለም ቦታ ይዞ።
የየቡድኑ አሰልጣኝ...ሌት ከቀን ሲለፋ፤
በባዶ ሜዳ ላይ...ግብ አስገቢ ጠፋ።
ቅንዝንዙ አጥቂ...በቀይ ካርድ ወጣ፤
ያም ቀዥቃዣ ገፊ ...ኦፍሳይት ተቀጣ።
ፈጣኑ የቀኝ ከንፍ... አጉል ተቀየረ፤
ዝነኛው ተጫዋች...እግሩ ተሰበረ።
ማህል አከፋፋይ...በሪዘርቭ ተተካ፤
ፔናሊቲ ክልል...አውቆ ማኖ ነካ።
ሌላው በራሱ ላይ...ግብን አስቆጠረ፤
አራጋቢ አውጥቶ...በአድሎ ተሻረ።
ኮከቡ ግብ አግቢ..ተጠልፎ ወደቀ፤
የፍዱም ቅጣት ምት... ተስቶ አለቀ።
ካርድ ሰጪ ዳኛ...ጠፍቶ የሚያረጋጋ፤
አምበል፤ተጫዋቹ... ኳስ አበደች ለጋ፤
ባለሙያ አዋቂ...ሁሉም አፉን ዘጋ፤
አየህልኝ? ብሎ... ዝም አይነቅዝም ጮጋ፤
ተዋርዶ መሸነፍ...ያስከፍላል ዋጋ።
ውጤቱ እንዳየነው፤
ባዶ ለባዶ ነው።
ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ፤
ኳስ በዓየር ተመታ፤
ይቺ ነች ጨዋታ፤
የለም...የሚረታ፤
በል እስክስታ ምታ።
እባክህ ኮርኩረኝ፤
የእውነት ሳቅ አማረኝ፤
እንዳታሳፍረኝ፤
እንደ አሁኑ ትውልድ..."ላሽ" በል አትበለኝ፤
ሙያ በልብ ነው... የድሮ አራዳ ነኝ፤
አጫውተኝ፤ ላጫውትህ...የአባ ሃና ልጅ ነኝ።
ሸመልስ ተሊላ።
መጋቢት 1 2008 ዓ.ም።
ኢትዮሚድያ
No comments:
Post a Comment