Thursday, January 14, 2016



ለውጥ ግድ ይላል!


ብሩህ ቦጋለ፣ ኖርወይ
ሁሌም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብዙ ህጎች በሚቀርቡበት ወቅት ውዝግብ የሚነሳባቸው ነበሩ፡፡ ገዢው ፓርቲ "ሕጎቹ ዲሞክራሲና ልማት የሚያሣልጡ ናቸው" እያለ ሲዘምር በምክር ቤት የሚገኙ አባላት ደግሞ "ሕጎቹ የገዢውን ስልጣን ለማራዘም ዜጎችን ለማጥቃት የተዘጋጁ መሣሪያዎች ናቸው" በማለት በተገደበች ደቂቃቸው ይሟገቱ ነበር፡፡ ከእዚህ ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ የፀረ-ሽብርተኛነት ሕግ አንዱ ነው፡፡
ይህ አዋጅ ከነሀሴ 22/2007 ፀድቆ ሥራውን ከምርጫ 2002 ማግዕስት ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ጀመረ፡፡ ይህን ተከትሎ አዋጁ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የመብት ተቋማት እና ምዕራባዊ መንግስታት ዘንድ እጅግ ከፍተኛ ተቃውሞ ይደርስበት ጀመር፡፡ በወቅቱ "አዋጁ ከሕገ መንግስቱ ጋር ይጋጫል" በማለት ምሁራኑም ተቹ፣ ይሁን እንጂ "ሽብርተኛነት፣ ጋዜጠኛነት፣ ተቃዋሚነት፣ ፋኖነት፣ ጦማሪነትየተባሉ ጉዳዮችን አንድ በማድረግ ሁሉንም በመደዳ ማጥቃቱን ግን አልተወም ነበር፡፡ ይባስ ብሎም በመንግስታዊ የመገናኛ ብዙሃን አዋጁን "ለመከላከል" ከየትኛውም ሕግ በላይ በዛ ያሉ ዶክመንተሪዎች ተሰሩለት/አዲስ ግንባር ጅሃዳዊ ሀራካት፣ አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ) የሚሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡


አዋጁ ለፀጥታ ተቋማት (ለደህንነትና ፖሊስ) ሰፊ መብት የሚሰጥ በመሆኑ አዋጁን መሰረት በማድረግ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ስቃይና ድብደባ እደረሰባቸው ለእስር ተዳረጉ፡፡ ወትሮም የፀደቀበት ዓላማ ይህ በመሆኑ አዋጁ ያልነካው/ የማይነካው የስራ ዘርፍም ሆነ ግለሰብ የለም፡፡ በአጠቃላይ የኢፌድሪ መንግስት ከተቋቋመበት 1987 ጀምሮ ባሉት ዓመታት ውስጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካፀደቃቸው ዘጠኝ መቶ የሚጠጉ አዋጆች ውስጥ እንደ አዋጅ ቁጥር 652/2001 አስፈሪ አዋጅ አለ ለማለት ይከብዳል፡፡

ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ክብርን የማያውቀው ኢህአዴግ ለእስክሪብቶ ታንክ ማዘዝ የጀመረው፡፡ ሀሳብን በሀሳብ የመመከት አቅም ማጣት፣ ሀሳብን በማፈን ሌሎችን መቀጣጫ በማድረግ፣ የአሸባሪነት ወይም ሌላ ታርጋ እየለጠፈ ዜጎችን በማሳቀቅ ህጋዊ እውቀትን በተሰጠበት ሀገር ሀሳበን በነፃነት ማራመድና መነጋገነር የተገደበና ከባድ ያደረገው፡፡ እንደኔ እንደኔ ተናግሮ መተማመን የማይችል ወይም ዱላ የሚቀናው አንድም ሀሳብ የለውም አሊያም ደግሞ አለኝ የሚለው ሀሳብ እንደማያሳምን ራሱም ቢሆን ጠንቅቆ ስለሚረዳው ይመስለኛል፡፡

መንግስታችን እሱን ሲያሻው ካልሆነ በስተቀር የማያከብረውን ሕገ-መንግስት "መብት አላችሁ" ብሎ ማሳመን ከባድ ስራ ይመስለኛል፡፡ ከህገ መንግሰቱ ባሸገር ሀገራችን የተፈራረመችው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ስምምነቶች መብቶቻችንን ያስታውሱናል፡፡ እኛም ወግ ደረሰን ብለን ስንጠቀምባቸው ድንገት ከበስተኋላችን የማናውቀው ታርጋ ተለጥፎብን እንገኛለን፡፡ በዚህ ጊዜ አይደለሁም! ብንልም ጌቶች ነህ ብለዋልና "መግባት ወይም መውጣት" አሊያም" ጥምር አገልጋይ" የሚባል ቁርጥ ምርጫ ይሰጠናል፡፡

በሌላ መልኩ "ቀዩ መስመር" በጨቋኝ እና በተጨቋኝ በኩል ሲታይ ፍፁም ለየቅል ነው፡፡ ለጨቋኝ፣ ስልጣኑ፣ ገመናው፣ ባዶነቱ፣ ሙስናው የሚሳበቅበት፣ ይህም ስራውን ተዓማኒነት አሳጥቶ ስልጣን የሚነሳው መስሎ ከታየውና ያገባኛል ባዮች ተደማጭነትን ካገኙ ያ "ቀይ መስመርን" ማለፍ ነው፡፡

ለተጨቋኝ (ለህዝብ) ደግሞ፣ መብቱ ህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠለት፣ ገዳቢ፣ አገሩ እንጂ ባለስልጣን ወይም ፓርቲ አይደለም የሀገሩን ጥቅም አሳልፎ አይሰጥም፡፡ በዚህም የሀገራችን ህጎች ሆነ ተብለው ለብዙ ትርጉም ተጋላጭ እንዲሆኑ ተደርጓል፤ በስህተት ያልተተረጎሙ ካሉም በስህተት እንዲተረጎሙ ይደረጋል እንጂ ጋዜጠኞችንም ይሁን ተቃዋሚዎችን ከማስከሰስ አይመለሱም፡፡ ይህ ደግሞ ሆን ተብሎ ለሰልጣን ጥብቅና ሲባል የተደረገ እንጂ የቃላት ድህነት ኖሮብን የተፈጠረ የሚመስለን ካለን እውነትም ያልነቃን አለን፡፡

እ.ኤ.አ በ1984 ድሬዝ እና ሴን የተባሉ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥናት ነፃ መገናኛ ብዙሀን ባሉበት ሀገር ከፍተኛ ድህነት እና ረሀብ ተከስቶ እንደማያውቅ ይጠቁማሉ፡፡ ይህንንም ሲደግፉ ነፃ የሆነ የመረጃ ፍሰት ባለባቸው ሀገራት መንግሰታትን (ዲሞክራሲያዊ ባይሆኑም እንኳን) ከህዝቡ የሚመጣ ግፊት ጫና ውስጥ ስለሚከታቸው እና ይህንንም ለማስወገድ ሲሉ ቀድመው የህዝብን ጥያቄ የሚመልስ እርምጃ ስለሚወስዱ እንደሆነ ይተነትናሉ፡፡ ግለሰባዊ ነፃነቶች (ሀሳብን በነፃነት መግለፅን ጨምሮ) ማክበር በመንግሰት ቁጥጥር ሥር የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችን ምጣኔ ሀብታዊ እድገት እስከ 20% ድረስ ይጨምራሉ፡፡

እንደ በመንግስት የሚተዳደሩ ፕሮጀክቶች ባይሆንም በግል ባለሀብቶች እና ተቋማት የሚካሄዱ ንግዶች ሀሳብን በነፃነት መግለፅ በሚቻልበት ሀገር ለገበያ የሚያቀርቧቸው ዕቃዎችና አገልግሎቶች የህብረተሰቡን ደህንነት ወይም ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥል ዕቃ ወይም አገልግሎት ቢያቀርቡ ነፃ መገናኛ ብዙህን ሁኔታውን በማጋለጥ ህብረተሰቡን ከጉዳት ይጠብቃሉ፡፡

እንደ ህውሀት/ኤህአዴግ ያሉ የሀሳብ ብዝሀነትን በመቆጣጠር ህዝብ እነሱ የሚሉትን ብቻ እየሰማ እንዲነዳ የሚፈልጉ መንግስታት ግን ሀሳብን ለማፈን ብዙ ርቀት ይጓዛሉ፡፡ የአይን መረብን ማጥለል፣ ጦማሮችን እንደ ከብት ማገድ፣ ዜጎችን መሰለል፣ ጋዜጠኞችን ማዋከብ፣ ማስፈራራትና ማሰር፣ በሳተላይት የሚተላለፉ የሬድዮና የቲቪ ስርጭት ሞገዶችን ማገድ የሚጠቀሱ የአፈና መሣሪያዎቻቸው ናቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ መንግስት በዜጎች ላይ እያደረገ ያለው ስለላ መጠን ረቀቅ ያለ እና ዘመናዊ ሆኗል፡፡ ፊንፊሸር የተባለ ኢንተርኔትን በመጠቀም ዜጎች ላይ ስለላ ለማድረግ የሚያስችል የረቀቀ ቴክኖሎጂን ከሚጠቀሙ 10 ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆናለች፡፡ ይህን ቴክኖሎጂ ለመግዛት ከ350 ሺህ በላይ የአሜሪካን ዶላር ይጠይቃል፡፡ ታዲያ ቁጥር አንድ ጠላቷ ድህነት ለሆነ ሀገር ህገ-መንግስቱን ጥሶ ዜጎችን ለመሰለል ሲባል ብቻ ይህን ያህል ወጪ ማውጣት እውነትም አሀዳዊ ተረክ ለመፍጠር ምን ያህል ርቀት እንደሚኬድ ማሣያ ነው፡፡ ምናልባትም በሳተላይት የሚተላለፉ ሬድዮ እና የቴሌቭዥን ስርጭትን ለማደናቀፍ ምን ያህል የተወሳሰበ ቴክኖሎጂ እንደሚያስፈልግና ለዚህም ሲባል ከፍ ያለ ወጪ እንደሚያስወጣ መገመት ቀላል ነው፡፡

በእርግጥ ማንኛውም መንግሰት (ፓርቲ) የሀሳብ የበላይነት እንዲኖረው ይጥራል፡፡ ኢህአዴግም የሀሳብ የበላይነትን ለማረጋገጥና ለመጎናፀፍ መከጀሉ የሚስተቸው አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ጥያቄ የሚስነሳበትና ለትችት የሚጋበዝበት ሁነኛ ችግሩ ማግኘት አለብኝ ብሎ የሚያስበውን የሀሳብ የበላይነት ለመቀናጀት የተሰማራበት የእኔ አውቅልሀለሁ መንገድ ነው፡፡ ይህም የመገናኛ ብዙሃንን፣ በሙሉ በመቆጣጠር ለራሱ ፍፁማዊ ጥቅም ለማግኘት ፕሮፓጋንዳ ይጠቀምበታል፡፡ በሌላ አነጋገር ማንኛውንም ዓይነት የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም ፉክክር እንዲኖር አይፈቅድም፡፡
ኢትዮጵያዊ ማንነት እየጠፋ ኢህአዴጋዊ ቀለም እየተውለበለበ የሚታሰረው ታስሮ፣ የሚሰደደውም በሰው ሀገር ተሸሽጎ ደግሞ ሌላው የቀረው ዜጋ በፍርሀት ዝምታ አጎንብሶ አሊያም አወድሶ የሚኖረው ይኖራል፣ የሚያኗኑረውም "አንድ ቀን …….? እያለ ሰርክ አዲስ ቀን ይናፍቃል፡፡


በመጨረሻ ምናልባት በእኔ እምነት ኢህአዴግ ህገ-መንግሰትን አርቅቆ ህገመንግስታዊነትን ሳይሆን በሁሉም ውስጥ ፍፁማዊ የበላይነትን የተጎነፀፈ ሰርዓት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ይህች አገር ለውጥ የግድ ያስፈልጋታል፡፡ ሁሉንም የማይጠቅም ቢሆን እንኳን ለብዙሀኑ ሲባል ለውጥ/ አዲስ ነገር የግድ መምጣት አለበት፡፡ የለውጥ ፍርሀትን እና ተቃውሞን እንደ ችግር ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት አይቻልም፡፡ ነገር ግን በቂ ዝግጀት በማድረግ በተገቢው መንገድ መቀነስ ይቻላል፡፡ የለውጥ ፍርሀትን እና ተቃውሞን ሳይቀንሱ ግን ለውጥን መጠበቅ ዘበት ነው፡፡

የፈረንሳይ የፍርሀት ዘመን አንድ ዓመት ሳይዘልቅ በሞቀ አብዮት ተገፍፏል፡፡ አብዮት አብዮትን እየወለደ ከአራት አብዮት በኋላ የዛሬዋ ፈረንሳይ የበለፀገችና ዲሞክራዊያዊ ሆነ ተወለደች፡፡ ለእኛም ይህ የፍርሀት ዘመን ተገፍፎ ብልፅግና ዲሞክራሲ እንዲመጣ ፍርሃታችንን ለመጋፈጥ መቁረት አለብን፡፡ "መፍራት ካለብን ፍርሀትን ራሱ ነው" እንዲሉ ፈራንክሊን ሩዝቬልት ምናልበት እሰው ሀገር በስደት መኖሬን ከቅንጦት ቆጥረው ይህን ሀሳብ
ፃፍክ በማለት "አመፅን ናፋቂ፣ ግንቦት ሰባት፣ አሸባሪው! አሊያም በኢአህዴጋዊ ቋንቋ አንዳንድ የውጪ ኃይሎች…….." የሚሉ ታፔላዎቸን በመለጠፍ ሀሳቤን የሚያጨናግፉ! አሊያም ከኢአህዴግ ጋር የሚተጋገዙብኝ አይጠፉም ይሆናል፡፡ ግድየለም ያሉትን ይበሉ፣


ግን እናንተዬ፣ "የፕሬስ ነፃነት አለ" ያለን እኮ ራሱ ኢአህዴግ ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው? እሱን አምኖ የፃፈ፣ በነፃነት አቋሙን ያንፀባረቀ ሁሉ ልክ እንደ እኔ ከመንግስት ጋር ይኳረፋል፡፡ ለምን ባልኩ ዛቻ፣ ስድብና እንግልት የሰርክ ቀለቤ ሆነ ሀገሬ የኔ አልመሰልህ አለችኝ፣ እናም ተሰደድኩ፡፡ አሁንም ግን ኢትዮጵያዊነቴን ማንም አይነጥቀኝም፡፡

ለዚህ ሀሳብ መነሻ ሆኖ አሳዝኖ ያስቆጨኝ ኢህአዴጋዊው መንግሰት ከትናንት በባሰ መልኩ ዛሬም የሀሳብ ነፃነት ያፍናል፣ ጋዜጠኞችን እያደነ እስር ቤት ማጎሩን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ለዚህም ነው ለውጥ የግድ የሚለው ለማለት የተገደድኩት፡፡
ብሩህ ቦጋለ - biruhbogale5@gmail.com

ስዊዘርላንድ
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com



January 10, 2016

No comments:

Post a Comment